እኛንም ያድነናል (ለሕፃናት)

እኛንም ያድነናል (ለሕፃናት)

እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች ? ደህና ናችሁ? እረፍት እንዴት ነው? የዚህ በሁለት ወር ክረምት እረፍታችሁን እንዴት እያሳለፋችሁ ነው? ልጆች ቤተሰባችሁን በመላላክ ሥራ በማገዝ እያገለገላችሁ ነው? በተለይ ደግሞ በቤተክርስቲያን ተገኝታችሁ ትምህርት ቃለ እግዚአብሄርን በመማር በዝማሬ እግዚአብሄርን እያመሰገናችሁ ነው? እንደዚህ ከሆነ በርቱ እሺ እግዚአብሔር የሚወደው እንደዚህ አይነቱን ነው፡፡

እሺ ልጆች ዛሬ ያቀረብንላችሁ ሐምሌ 19 የሚከበረውን ቅዱስ ገብርኤል ስላዳናቸው አንድ እናትና አንድ ልጅ ታሪክ አዘጋጅተንላችኋል በትዕግስት ተከታተሉን እሺ፡፡ የሕፃኑ ስም ቅዱስ ቂርቆስ ሲሆን የእናቱ ስም ደግሞ ቅድስት ኢየሉጣ ትባላለች አባቱ ቆዝሞስ ይባላል፡፡ ሐገሩ ሮም አንጌቤ ነው፡፡ ዲዮቅልጥያኖስ የተባለ ንጉሥ በነገሠበት ጊዜ በ303 ዓ.ም. አብያተ ክርስቲያናትን ማፈራረስ ጀመረ ፡፡ በዚህ ጊዜ ሕዝቡ መሰደድ ጀመሩ፡፡ ከእነዚህም መሐል የ3ዓመት ሕፃን የያዘች እናት ነበረች እናትየዋም ልጂን ይዛ ወደ ኢቆንዮን ወደተባለ ሐገር ሸሸች የሐገሩ መሪ ባለሥልጣኑ እለእስክንድሮስ ክርስቶስን ካጂ ለጣዖት ስገጂ አላት እናትየውም ዓይን እያለው ለማያይ ጆሮ እያለው ለማይሰማ በቃልህ አዘህ በእጅህ ሠርተህ ላቆምከው ምስል አልሰግድም አለች፡፡ አይሆንም ካልሽማ በሰይፍ ትቀጪያለሽ ብሎ አስፈራራት ሕፃኑን ወርቅ እሰጥሃለሁ በዚህ ጣዖት ስገድ አለው፡፡ ልጆች እስቲ እናንተን ወርቅ እሰጣችኋለሁ ክርስቶስን ካዱ ብትባሉ ምንድነው መልሳችሁ? እሺ ብሎ መስገድ እና ወርቅ መውሰድ ነው ? አይደለም አይደል፡፡

ወርቅን የፈጠረው ማነው? ወርቅን ብቻ ሳይሆን ይህንን ዓለም የፈጠረ ማን ነው? ክርስቶስ ወይም እግዚአብሔር አይደል፡፡ ልጆች የሦስት ዓመት ሕፃኑ የመለሰለትን መልስ እንመልከት፡፡ መንፈስ ቅዱስም አድሮበት ስለነበር ራሳቸውን አንኩዋ ማዳን ለማይችሉ ርኩሳት ጣዖታት አልሰግድም አለው ይህ ሕፃን የተናገረው መንፈስ ቅዱስ ስላደረበት ነው፡፡ እኛም መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርብን በቤተክርስቲያን ቃለ እግዚአብሔር መስማት መዘመር ታላላቆቻችንን ማክበር ለወላጆቻችን መታዘዝ ያስፈልጋል እሺ ልጆች፡፡ የፈላው ውኃ እንደ ክረምት ነጐድጓድ ይሰማ ነበር፡፡ ሊከቷቸው ሲወስዷቸው እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ ልቧ በፍርሐት ታወከ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ ግን ፍርሃቷን አርቆላት እያለ ይፀልይላት ነበር፡፡ ልጆች አያችሁ እግዚአብሔር የሕፃን የትልቅ የወጣት የሴት የወንድ አይልም በአንድ መንፈስ በቅን ልቡና በተሰበ ልብ ሆነው ቢጸልዩ ይቀበላል፡፡ እናንተም ስለቤተሰባችሁ ስለሐገራችሁ ልትጸልዩ ይገባል እሺ፡፡ እንደውም ሕፃኑ እናቱን አትፍሪ አናንያ አዛርያ ሚሳኤልን ያዳነ እኛንም ያድነናል እያለ እያበረታታ ልብሷን እየጐተተ እሷም ጨክና ተበረታታ በእሳት በፈላው ውሃ ውስጥ ገብተዋል፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ በበትረ መስቀሉ እሳቱን እጥፍቶ የፈላውን ውሃ አቀዝቅዞ አውጥቷቸዋል፡፡ በወጡም ጊዜ ልብሳቸው ሳይለበለብ ሰውነታቸው ሳይሸበሸብ ምንም የፈላ ውሃ ውስጥ የገቡ ሳይመስሉ ወጥተዋል፡፡ ከአሕዛብ የሚያምኑ ከነበሩ ብዙዎች በእግዚአብሔር አምነው ተጠምቀዋል፡፡

ከቅዱስ ቂርቆስ እና ከእናቱ ከቅድስት ኢየሉጣ ረድኤትና በረከት ያሳትፈን፡፡

በማስተዋል እንዳነበባችሁ ለማወቅ እስቲ ጥያቄ እንጠይቃችሁ?

1. ሕፃኑ ቂርቆስ ሐገሩ የት ነው ?

2. መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርብን ምን እናድርግ?

3. ቅዱስ ገብርኤል ከፈላው ውሃ ያዳናቸው መቼ ነው?

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ: stgeorgessc.org

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *