የልጆች ዓምድ

ለልጆች ማስተማሪያ የሚሆን ታሪኮችና ስነጽሑፎች

ወላጆች ለልጆች

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን ከፈጠረው ጊዜ አንስቶ ለአዳም እና ለልጆቹ ከሰጣቸው ስጦታዎች መካከል ወልደው የሚከብሩባቸው መንፈሳዊ በረከትን የሚስገኙላቸው እግዚአብሔርም ደስ የሚሰኝባቸው የአብራክ ክፋይ የማሕፀን ፍሬዎች ሕፃናት ድንቅ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር ዘንድ ልጆች ለወላጆቻቸው ወደር የሌለው ስጦታ ሆነው ይሰጣሉ ወላጆችም ይህን ልጅ ማግኘትን እና የወላጅነትን ፀጋ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላሉ፡፡ ወላጅነት ከምድር የሚሰጥ በረከት ሳይሆን የልዑል እግዚአብሔር ስጦታ ነው፡፡ በዚህ ሂደት ወላጅ የመሆን እና ልጆችን በስጦታ መልክ ማግኘት ከእግዚአብሔር ዘንድ ሲሰጥ ከነ ሙሉ ኃላፊነቱ ነው፡፡ በስጋ ወልዶ መተው ሳይሆን ይህንን ዓለም ያላየውን አዲሱን ብርቅዬ ፍጡር የነገውን ትልቁን ሰው በእንክብካቤ በማሳደግ መልካሙን መንገድ በማስተማር ሰው የሚሆንበትን መንገድ በማሳየት በጥበብና በሞገስ ከማሳደግ ኃላፊነት ጋር ጭምር ነው፡፡ (ምሳ 1¸8፣ 4¸10) ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት ልጁ ሰሎሞንን “በርታ ሰው ሁን የአምላክህ የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ጠብቅ” 1ኛ ነገ 2፣3 በማለት መክሮታል፡፡
ልጆች በፈሪሃ እግዚአብሔር ተጠብቀው፣ በስነምግባር ታንፀው፣ በጥበብ ሥጋዊ በጥበብ መንፈሳዊ በርትተው ከኃጢአት ርቀው በጽድቅ ስራ ፀንተው አምላካቸውን፣ ራሳቸውን፣ ወላጆቻቸውን፣ ቤተክርስቲያናቸውን፣ ወገናቸው ማገልግል እንዲቻላቸው ማድረግ ይኖርብናል፡፡

በአጠቃላይ ወላጅነት የጥሩ የመልካም ምግባር መምህርነት ነው፡፡ ቤተክርስትያን ደግሞ የቅድስና የእግዚአብሔር የቃሉ መዛግብት ማህደር እውነተኛይቱ የፅድቅ ወዳጅ ናት ምክንያቱም የቤተክርስትያን ራስ ክርስቶስ ነውና፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ደግሞ “እውነትም መንገድም ህይወትም እኔ ነኝ” ይላል ዮሐ 14 ፣ 6 ወደ ቅድስት ቤተክርስትያን በመላክ ወላጆች ለልጆቻቸው መልካም የሆነን የማይጠፋ ህይወትን የእግዚአብሔርን ቃል ማውረስ አለባቸው፡፡ ስለሆነም ልጆች ከእግዚአብሔር የተሰጡን ከፍጡራን የማናገኛቸው ውድ እና ብርቅዬ ስጦታዎቻችን በመሆናቸው እንደ እንቁላል ከዚያም በሚበልጥ እንክብካቤ ልንጠብቃቸው እና ልንንከባከባቸው የሚገቡ ስጦታዎች ናቸው፡፡


ታሪክ ለልጆች

ፎቶዎች