ስለ ደብራችን

የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን  መሰረቱ ቀደም ሲል በፊንላንድ ሀገር በተለይም በሄልሲንኪ ከተማ ይኖሩ የነበሩ አባቶች፣ እናቶች፣ ወንድሞችና እህቶች ከቀደሙት አባቶቻቸዉ የተላለፈላቸውንና በትምህርተ ሃይማኖት የተረከቡትን ነገረ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ስነምግባር ሊረሳ ከማይገባዉ ታሪክ፣ ባህልና ቋንቋቸው ጋር ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሲሉ ረድኤተ እግዚአብሔርን መከታ በማድረግ በቅዱሳን ጸሎትና ተራዳኢነት በማመን በ 1985 ዓ.ም በማህበር ደረጃ በሄልሲንኪ ከተማ የመሰረቱት ’’በፊንላንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማህበረ ምእመናን’’ ነው።

በዚህ ሁኔታ የተመሰረተው ማህበረ ምእመናን በየጊዜዉ የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች በእግዚአብሔር ረድኤትና አጋዥነት እንዲሁም በአባላት ከፍተኛ የሆነ መደጋገፍና ጥረት በማለፍ የአባላትን ሃይማኖታቸውን እያፀናና ምግባራቸዉን እያቀና እስከ 2003 ዓ.ም  ደርሷል፡፡ለሁሉም ጊዜ አለው’’ እንዳለው ጠቢቡ ሰሎሞን ሰኔ 5፣ 2003 ዓ.ም. በልዑል እግዚአብሔር መልካም ፈቃድ የሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ እንጦስ በሄልሲንኪ ከተማ ተገኝተው ማህበሩን  ወደ ቤተ ክርስቲያንነት እንዲያድግ ፈቅደዋል፡፡ በዚህም መሰረት እጣ በማውጣት ቤተ ክርስቲያኑ በአቡነ ተክለሃይማኖት ስም ተሰይሟል::

የፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አዉሮፓ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ጽህፈት ቤት ስር የተቋቋመ አጥቢያ ነው፡፡  ቤተ ክርስቲያኑ በአሁን ሰዓት ህጋዊ መስፈርቶችን አሟልቷ በፊንላንድ ሃገር ሕጋዊ እውቅና አግኝታለች።


የአቡነ ተክለሃይማኖት ንግስ በዓል


የደብሩ አስተዳዳሪ

መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ

የደብሩ አስተዳዳሪ

የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ብሎም በፊንላንድ ውስጥ የመጀመሪያው ቋሚ ካህን ናቸው፡፡ አገልግሎታቸውንም በኅዳር 4 ቀን 2008 ዓ.ም. (November 14, 2015) ጀምረዋል፡፡