ስለ እመቤታችን ልደት (ለሕፃናትና ዠማሪዎች)

ስለ እመቤታችን ልደት (ለሕፃናትና ዠማሪዎች)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች እንዴት ሰነበታችኁ? እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነን አላችኁ? አሜን፡፡ እኔም በጣም ደኅና ነኝ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
ልጆች! ባለፈው ጊዜ ስለምን እንደተማማርን ታስታውሳላችኁ? አቤል እና ቃየን ስለሚባሉ ኹለት ወንድማማቾች አይደል? ጐበዞች! ትክክል ናችኁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ኹላችንም ስለምንወዳት ስለ እናታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት እነግራችኋለኹ፡፡ ለመስማት ዝግጁ ናችኁ አይደል? ጐበዞች፡፡ እግዚአብሔር ዕውቀቱን ይግለጥልን፡፡ አሜን!!!

የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አባት ኢያቄም ይባላል፡፡ እናቷ ደግሞ ሐና ትባላለች፡፡ ኢያቄምና ሐና እግዚአብሔርን በጣም የሚወዱትና በሕጉ የሚኖሩ ደጋጐች ነበሩ፡፡ ነገር ግን ሐና መካን ስለነበረች ኹለቱም ወደ ቤተ እግዚአብሔር ዕለት ዕለት በመኼድ ለዐይናቸው ማረፊያ ለልባቸው ተስፋ የሚኾን ልጅ እንዲሰጣቸው ይለምኑ ነበር፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀንም ሲያዝኑና ሲጸልዩ ውለው ወደ ቤታቸው እየተመለሱ ሳለ ርግቦች ከልጆቻቸው ጋር ደስ ብሏቸው ሲጫወቱ አዩ፡፡ ሐናም፡- “ጌታዬ! ለእንስሳ እንኳን ልጅ የሰጠኽ አምላክ ምነው ለኔ ልጅ ከለከልከኝ” ብላ ምርር ብላ አለቀሰች፡፡ እግዚአብሔርም ጸሎታቸውንና ሐዘናቸውን አየና ልጅ እንደሚወልዱ በሕልም ነገራቸው፡፡ ኢያቄምና ሐናም “ወንድ ልጅ ከወለድን ለቤተ እግዚአብሔር አገልጋይ ይኾናል፤ ሴትም ብንወልድ ለቤተ እግዚአብሔር መጋረጃ ፈትላ ትኖራለች” ብለው ለእግዚአብሔር ቃል ገቡ፡፡ ከዚያ በኋላ ነሐሴ ሰባት ቀን ሐና እመቤታችንን አረገዘች፡፡
ከስድስት ወርም በኋላ የሐና ፅንሷ እየታወቀ መጣ፡፡ ጎረቤቶቿ መፅነሷን ሰምተው ተደነቁ፡፡ እየመጡም ማሕፀኗን ይዳስሱ ነበር፡፡ አንድ ቀንም ዐይኗ የማያይ ሴት መጣችና የሐናን ማሕፀን ዳስሳ ዐይኗን ብትነካው በራላት፡፡ በጣምም ተደሰተች፡፡ ከዚኽ በኋላ ብዙ የታመሙ ሰዎች እየመጡ የሐናን ማሕፀን እየዳሰሱ ይድኑ ነበር፡፡ በእጅጉ የሚደንቀው ደግሞ ሳሚናስ የሚባል ልጅ ከአጐቱ ቤት ሔዶ ሞተ፡፡ እመቤታችንን ያረገዘችው ሐናም የአልጋውን ጫፍ ይዛ እየዞረች እያለቀሰች ነበር፡፡ ትንሽ ቆይቶ ግን የሞተው ልጅ ተነሣ፡፡ እዚያ ቦታ የነበሩ ሰዎች ግን እግዚአብሔርን ከማመስገን ይልቅ ቅናት ያዛቸውና ሐናንና ኢያቄምን በድንጋይ ደብድበው ሊገድልዋቸው ተማከሩ፡፡
ከዚኽ በኋላ ቅዱስ ገብርኤል ለኢያቄም ተገለጸና ሐናን ሊባኖስ ወደሚባል ተራራ እንዲወስዳት ነገረው፡፡ እመቤታችንንም በዚያ በሊባኖስ ተራራ ግንቦት አንድ ቀን ወለደቻት /መኃልየ መኃልይ ዘሰሎሞን 4፡8/፡፡ ሐናና ኢያቄምም በእጅጉ ተደስተው በተወለደች በ8 ቀኗ ስሟን ማርያም ብለው ሰየሟት፡፡

ልጆች! የእመቤታችን ልደት ለእኛ ለሰዎች ትልቅ ደስታ ነው፡፡ ለምን እንደኾነ ታውቃላችኁ? ባለፈው ጊዜ እንደነገርኳችኁ አዳምና ሔዋን ለእግዚአብሔር ሳይታዘዙ ሲቀሩ ከገነት ተባረው ነበር፡፡ ከገነት የተባረሩት ግን እመቤታችን እስክትወለድ ነው እንጂ ወጥተው በዚያ እንዲቀሩ አልነበረም፡፡ ገነት እንደገና የተከፈተልን በእመቤታችን ምክንያት ነው፡፡ ለዚኽ ነው ማርያምን በጣም የምንወዳት፡፡ እናንተስ ማርያምን ትወዷታላችኁ? እስኪ መውደዳችኁን በምንድነው የምትገልጹት? እመቤታችንን እንደምንወዳት የምንገልጸው ውዳሴ ማርያምን በማንበብ፣ ስለ እመቤታችን በመዘመር፣ ሥዕሏን በመሳም፣ እንድታማልደን በመለመን፣ ስሟን ጠርተው ለሚለምኑን ሰዎች ብር ወይም ልብስ ወይም ደግሞ የሚበላ ነገር ስንሰጥ ነው እሺ ልጆች፡፡
ልጆች! ይሔ ጥቅስ በቃላችኁ ያዙት፡፡ “ስለ ሔዋን የገነት ደጅ ተዘጋ፤ ዳግመኛም ስለ ድንግል ማርያም ተከፈተልን” /የሐሙስ ውዳሴ ማርያም/፡፡

በሉ በቀጣይ ጊዜ እስከምንገናኝ ድረስ ደኅና ሰንብቱ፡፡ እመቤታችን በምልጃዋ ትጠብቃችኁ፡፡ አሜን!!!

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *