ሀገረ ስብከቱ የ2015 በጀት ዓመት  አፈጻጸም ጠቅላላ ጉባኤውን  አጠናቀቀ

ሀገረ ስብከቱ የ2015 በጀት ዓመት  አፈጻጸም ጠቅላላ ጉባኤውን  አጠናቀቀ

ዜና ሀገረ ስብከት: የስዊድን፣ስካንዲናቪያን እና ግሪክ ሀገሮች  ሀገረ ስብከት ፣ ከነሐሴ 26-27/2015 ዓ.ም በስዊድን ስቶክሆልም ሲያካሂድ የነበረውን የሀገረ ስብከቱን የ2015 በጀት ዓመት  አፈጻጸም ጠቅላላ ጉባኤውን  አጠናቀቀ።

በብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሚመራው የስዊድን፣ስካንዲናቪያን እና ግሪክ ሀገሮች ሀገረ ስብከት በጉባኤው ላይ የ2015 ዓ.ም የበጀት ዓም የሥራ አፈጻጸም የገመገመ ሲሆን  ያጋጠሙ ችግሮችን በማንሳት ውይይት አድርጓል ።በማያያዝም ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚያገለግል ስልታዊ ዕቅድ ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን ቀደም ብሎ በአገልግሎት ላይ ያለውን የሀገረ ስብከቱን መተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ ረቂቅ ሕግም  ለጉባኤው ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል ። በመጨረሻም ጉባኤው በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያናችን ፈተናዎች እና በሀገራችን ኢትዮጵያ እስካሁን ሊቆም ያልቻለው የእርስ በርስ ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ  ልዩነቶችን ሁሉ መንግሥት  በውይይት ብቻ እንዲፈታ የጠየቀ ሲሆን ስለሀገራችን ሰላም ሁሉም ምእመናንም  በጸሎት እንዲተጉ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ አጥብቀው ያሳሰቡ ሲሆን ።
በመጨረሻም የሚከተሉትን  ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶአል።

1. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ጊዜያትና ወቅቶች በውስጥና በውጭ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን የተፈተነች፣ ያጋጠሟትንም ፈተናዎች በጥበብና በፈጣሪ እርዳታ ድል እያደረገች ካለንበት ዘመን ደርሳለች። ይሁን እንጅ በመጠናቀቅ ላይ ባለው የ2015 ዓ.ም. ከአሁን በፊት ከደረሰባት ፈተና እጅግ በከፋ መልኩ በራሷ ልጆች ወይንም አባቶች ብላ በሰየመቻቸው የተፈተነችበትና እየተፈተነች ያለችበት ዓመት ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ብሎ የወሰናቸውን ውሳኔዎች እንደግፋለን፤ ለተግባራዊነቱም ተግተን እንሰራለን።

2. ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሶስት ዓመታት ያክል በማያቋርጥ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የምትገኝ ሲሆን በጦርነቱም በርካታ ኢትዮጵያውያን  እልቀዋል፣ አካል ጉዳተኛም ሆነዋል ፣ ጥንታውያን ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናትም በጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ፣ ከፍ ሲልም ለመፍረስ ተዳርገዋል ።
ስለሆነም መንግሥት ችግሮችን ሁሉ በኃይልና በጦርነት ከመፍታት ይልቅ በውይይትና በስምምነት እንዲፈታ በአጽንኦት እንጠይቃለን።

3. ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነትና ከሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና ጽ/ቤት በተላለፈው መመሪያ መሠረት በሀገረ ስብከታችን ውስጥ ያለ ሊቀ ጳጳሱ ፈቃድ የሚደረጉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለምሳሌ አዳራሽ ተከራይተው ምዕመናንን ሰብስበው በቤተክርስቲያን ስም ይሁን ለሌላ ምክንያት ገንዘብ የሚያሰባስቡ ግለሰቦችን፣እንዱሁም ከሀገረ ስብከቱ እውቅና ውጭ ከተለያየ ቦታ በመምጣት ፈውስ እንሰጣለን፣ አጋንንትን እናስወጣለን የሚሉና ሕዝበ ክርስቲያኑን የሚከፋፍሉ ሕገ ወጦችን የማንተባበርና የምንቃወም መሆናችን እናረጋግጣለን።

4. በጉባዔአችን መክፈቻ ወቅት ለቀረበው የሀገረ ስብከቱ የ፳፻፲፭ ዓም የበጀት ዓ ም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አድናቆታችንን እየገለጽን በቀጣዩ የበጀት ዓመትም ሀገረ ስብከቱ ለሚያከናውናቸው ተግባራትና ለሚያስተላልፋቸው መመሪያዎች ተግባራዊነት ሙሉ ድጋፋችንን የምንሰጥ መሆናችንን እናረጋግጣለን ።

5. በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ኢትዮጵያ በተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነትና የጎሳ ፖለቲካ ባመጠው ችግር ምክንያት በተፈጠረ የህዝብ መፈናቀልና በኑሮ ውድነት በርካታ ኢትዮጵያውን በከፍተኛ ችግር ላይ ይገኛሉ ። ስለሆነም ጋን በጠጠር ይደገፋል እንደሚባለው በብፁዕ አባታችን አቡነ ኤልያስ የሚመራው ዝክረ ነዳያን ዘአበዊነ ሐዋርያት በጎ አድራጎት ድርጅት በሀገረ ስብከታችንና በመላውዓለም ካሉ ክርስቲያኖች በሚገኘው ገቢ በሀገር ቤት ለሚኖሩ ችግረኞች የሚያደርገውን እርዳታ እያደነቅን ወደፊትም ድጋፋችንና አስተዋጽኦችንን አጠናክረን የምንቀጥል መሆናችንን ቃል እንገባለን።

6. ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሀገራችን ኢትዮጵያ በተፈጠረው የፖለቲካ መለያየት ምክንያት በሀገረ ስብከታችን በፖለቲካ እና በጎሳ ብቻ ተደራጅተው ከሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ እውቅና ውጪ ቤተክርስቲያን እንከፍታለን የሚሉትን ቡድኖች አካሄድ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ውጪ በመሆኑ አጥብቀን እንቃወማለን።

7. በሀገረ ስብከቱ አስተባባሪነት በምሁራን ተዘጋጅተው በጉባዔው ላይ ውይይት የተደረገባቸውን የሀገረ ስብከቱን የአምስት ዓምት ስልታዊ ዕቅድና ተሻሽሎ የቀረበው የመተዳደሪያ ደንብ ይህ ጉባዔ የሰጣቸው ሀሳቦች ተካተውበት በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን።

8. በመጨረሻም ይህ ታላቅ ጉባዔ በሰፊው ተወያይቶ ያሳለፋቸውን የተለያዩ ውሳኔዎች በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል በመግባት የአቋም መግለጫ ያወጣ ሲሆን።  በጉባኤው ላይ  ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድን ስካንድናቪያንና የግሪክ ሀገሮች ሀገረ ስብከ ሊቀ ጳጳስ፣ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የጣልያንና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ፣የስተዳደር ጉባኤ አባላት ፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎች ፣ ምክትል ሊቃነ መናብርትና ተጋቤዥ እንግዶች ተሳትፈዋል ።

ነሐሴ ፳፯ ቀን ፳፻፲፭ ዓ ም ስቶክሆልም ስዊድን።

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *