ዓሣ አጥማጁ ስምዖን(ለሕፃናት)

ዓሣ አጥማጁ ስምዖን(ለሕፃናት)

በአንድ ወቅት ምን ሆነ መሰላችሁ ጌታችን በባህር ዳር ቆሞ ሕዝብን ያስተምር ነበር ሕዝቡም ጌታችን የሚያስተምረውን ትምህርት በደንብ ይከታተሉት ነበር፡፡ ጌታችንም ድምጹ ለብዙ ሰዎች እንዲሰማ ወደ ስምዖን ታንኳ ላይ ወጣ፡፡ በታንኳይቱም ውስጥ ተቀምጦ ሕዝቡን አስተማራቸው፡፡

ትምህርቱንም ሲጨርስ ሁሉም ሰው ወደ ቤቱ ሄደ፡፡ ሲማሩ ከነበሩት መካከል አንዱ ስምዖን ነበር፡፡ ቀኑን ሙሉ ሌሊቱን ሁሉ ምንም ዓሣ ስላላጠመደ ተጨንቆ ነበር፡፡ ለምን መሰላችሁ ልጆች የስምዖን ቤተሰቦች ስምዖን የሚያመጣውን ዓሣ ይጠባበቁ ስለነበረ ነው፡፡ ስምዖን ዓሣ ሳይዝ ወደ ቤቱ ከገባ ቤተሰብ ሁሉ ሳይበላ ነው የሚያድረው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ልጆች እግዚአብሔር የስምዖን ቤተ ሰቦች ተርበው እንዲያድሩ አላደረጋቸውም፡፡

ሌላው ደግሞ ልጆች ስምዖን ታንኳውን ጌታችን እንዲያስተምርበት ትቶለት ነበር፡፡ በጣም ታዛዥ ስለነበር እግዚአብሔር ዝም አላለውም፡፡ ጌታችን ስምዖንን መረብህን ጣልና ዓሣ አጥምድ አለው፡፡ ስምዖንም “መምህር ሌሊቱን ሁሉ ደክሜያለሁ ነገር ግን ምንም ዓሣ አልያዝኩም አንተ ስላዘዝከኝ ግን መረቤን እጥላለሁ” አለው፡፡ ስምዖን ምንም እንኳን ይሆናል ብሎ ባያምንም ለጌታችን ግን ታዘዘው፡፡ እንዳዘዘውም ባደረገ ጊዜ መረብ እስኪቀደድ ዓሣ ያዘ፡፡ ስምዖንም ይህን አይቶ ለጌታችን ሰገደለት፡፡ ከስምዖን ጋር የነበሩት ሰዎች ሁሉ በአዩት ነገር ተደነቁ፡፡

አያችሁ ልጆች ስምዖን ጌታችን ያለውን ነገር ሁሉ ስላደረገ ሌሊቱን ሙሉ ማጥመድ ያቃተውን ዓሣ መረብ እስኪቀደድ ድረስ ማጥመድ ቻለ፡፡ እኛም እግዚአብሔር አምላክ የሚያዘውን ነገር ብንሠራ ከምንፈልገው በላይ ይሰጠናል፡፡

ልጆች በመጨረሻም ዓሣ አጥማጅ የነበሩት ስምዖን ያዕቆብና ዮሐንስ ዓሣ ማጥመዳቸውን ትተው ጌታችንን ተከተሉት፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *