እናትና አባትህን አክብር (ለሕፃናት)
by ግንኙነት ክፍል
እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች ደህና ናችሁ በዛሬው የመጀመሪያ ጽሑፋችን እናትና አባትን ስለማክበር እንማማራለን ስለዚህ በደንብ ተከታተሉን፡፡ ከነብየ እግዚአብሔር ሙሴ የኦሪት መጻህፍት መካከል አንዱ በሆነው በኦሪት ዘዳግም 5÷16 ላይ እናትና አባትን ስለማክበር እንድህ በማለት ተናተናግሯል ፡-
“እግዚአብሔር አምላክህ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም፣ መልካምም እንዲሆንልህ እናትና አባትህን አክብር፡፡” ዘዳግም 5÷16
ልጆች ከአሥርቱ ትዕዛዛት መካከል አንዱ እናትና አባትህን አክብር የሚለው ነው፡፡ እግዚአብሔር እናትና አባታችንን ካከበርን በምድር ላይ ስንኖር ዕድሜያችን ረዥም እንደሚሆንና፤ በዚህ ዕድሜያችንም መልካም የሆነ ነገር እንደሚያደርግልን ቃል ገብቶልናል፡፡ ለእናትና ለአባታችን ስንታዘዝ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚደሰትና እድሜያችንን እንደሚያረዝምልን ሁሉ ካልታዘዝን ደግሞ ያዝንብናል፡፡ እናትና አባቱን የማያከብር፣ ስድብ የሚሳደብ፣ በትዕቢት ዐይን እናትና አባቱን የሚመለከት ልጅ እግዚአብሔር ደስ አይሰኝበትም፡፡ስለዚህ ልጆች እናትና አባታችን ማክበር ይገባል ማለት ነው፡፡ እናትና አባታችን ማክበር እንዳለብን ካወቅን እንዴት ነው የምናከብራቸው ለሚለው?
- የሚያዝኑን ሁሉ በመፈጸም እና ምክራቸውን በመስማት “ልጄ ሆይ የአባትህን ምክር ስማ የእናትህንም ትእዛዝ ቸል አትበል፡፡” ምሳ.1÷8
- ጥሩ እና ለእናትና አባታችን እንድሁም ለታላላቆቻችን አክብሮት የምንሰጥ ልጅ በመሆን
- እናትና አባታችን በመውደድ
እንግዲህ ልጆች እናትና አባትን ማክበር ከእግዚአብሔር ዘንድ ሽልማት የሚያሰጥ መልካም ሥራ ነውና እናትና አባታችንን ልናከብር ይገባል ማለት ነው፡፡ ጌታችን ራሱ እናቱ ድንግል ማርያምን ያከብር ነበር፤ ይታዘዛትም ነበር፡፡ እኛም እርሱን ምሳሌ አድርገን ልናከብራቸውና ልንታዘዛቸው ይገባል፡፡ እርሱም እኛን ይወደናል፡፡
ምንጭ : romekidistmariam.com
Recommended Posts
ስለ አቤልና ቃየን (ለሕፃናት)
December 27, 2017
ስለ እመቤታችን ልደት (ለሕፃናትና ዠማሪዎች)
December 26, 2017
ልደተ ክርስቶስ /የገና በዓል/ – ለሕጻናት
January 07, 2017