ምሥጢረ ሥላሴ – ክፍል ፪

ምሥጢረ ሥላሴ - ክፍል ፪

ሐዋርያዊት የሆነች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ክርስቲያናዊ ትውፊታዋንና ኀይማኖታዊ አስተምህሮዋን ጠብቃ የኖረች ናት ። ከአስተምህሮዋም አንዱና ዋንኛው ምሥጢረ ሥላሴ ነው ። ምሥጢረ ሥላሴ ( የእግዚአብሔር ባሕርይ ) ምሉዕና ስፉሕ ረቂቅና ምጡቅ የሆነ ተመጣጣኝ ምሳሌ የማይገኝለት ቢሆንም ፣ ቅዱሳን ነቢያትና ቅዱሳን ሐዋርያት በመንፈሰ እግዚአብሔር እየተመሩ የጻፏቸውን መጻሕፍተ ብሉያትንና መጻሕፍተ ሐዲሳትን ምስክር በማድረግ አበው ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እንደ አስተማሩን ፣ (በምሳሌ ዘየሐጽጽ) ደካማው አዕምሯችን በሚረዳው ዕኛ በምናውቀው ለሥላሴ ተመጣጣኝ ባልሆነ በአነስተኛ ምሳሌ እየመሰልን የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት በዕርሱ አጋዥነትና ረዳትነት ለመጻፍ እጀምራለሑ ፡፡

ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር

ነቢይ ሙሴ በጻፈው በመጀመሪያው የሥነ ፍጥረት መጽሐፍ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ . . . . እያለ የአምስቱን ቀን ሥነ ፍጥረት የሃያ አንዱን ፍጥረታት ተፈጥሮ እየዘረዘረ ከሄደ በኋላ፣ በስድስተኛው ቀን ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር አለ እግዚአብሔር (ዘፍጥ.1-26 ይልና ምዕ .1 ቁ. 26 -27 ) ላይ ሰውን በአርዓያ እግዚአብሔር ፈጠረው ይላል፡፡ (ሰውን) እንፍጠር ብሎ ሦስትነቱን አርዓያችን ብሎ አንድነቱን ሲያስረዳን ነው፡፡ መልክ ማለት ከራስ ፀጉር እስከ እግር ጥፍር፣ ድረስ ያለው አካል ነው፡፡ ለሰው እጅ፣ እግር፣ ዓይን፣ ጀሮ፣ አፍ ፣ አፍንጫ…….. ሌሎችም አካላት እንደ አሉት ሁሉ ለእግዚአብሔርም እጅ፣ እግር፣ ዓይን፣ ጆሮ፣ አፍ ፣ አፍንጫ …….የቀሩትም አካላት (መልክአት) ሁሉ አሉትና በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር ብሎ በአርዓያውና በአምሳሉ ሰውን ፈጠረ፡፡

እንደ ሰው ሁሉ ለእግዚአብሔርም አካላት እንዳሉት ነቢያት መስክረዋል፡፡ “የእግዚአብሔር ዓይኖቹ ወደ ጻድቃን ጆሮዎቹም ወደ ልመናቸው ነው፣ የእግዚአብሔር ገጸ መዓቱ ግን ክፉ ወደሚያደርጉ ሰዎች ነው ” ( መዝ . 33:15 -18 ) ፡፡ ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት የምትሠሩልኝ ቤት ምን ዓይነት ነው፣? የማድርበትስ ስፍራ ምንድን ነው፣? ይህ ሁሉ የእጄ ሥራ ነው፡፡ (ኢሳ . 66:1 ፣ 1ኛ ጴጥ . 3:12 ፣ ዳን . 7:9-14 ፣ ራዕ. ዮሐ . 11:3-16)

ለሰው ያለው ሙሉ አካል ሁሉ ለእግዚአብሔርም እንዳለው ነቢያትና ሐዋርያት በብሉያትና በሐዲሳት በርካታ መረጃዎችን ጽፈውልናል፡፡ ነቢያትና ሐዋርያት የጻፏቸውን ብሉያትንና ሐዲሳትን መረጃ ምስክር በማድረግ “ዓይኖችና ጆሮዎች፣ እጆችና እግሮች….. የቀሩትም አካላት ሁሉ ለእግዚአብሔር እንደ አሉት እናምናለን ” ሲሉ ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንት አስረድተዋል፡፡ (ሃይ. አበው ምዕ.19 ቁ.33) ስለሆነም ሰው በአርአያ እግዚአብሔር ይፈጠር እንጂ፣ የሰው አካል፣ ውሱን፣ ጠባብ፣ ግዙፍ፣ ድኩም፣ አጭር፣ ቀጭን፣ ፈራሽ፣ በስባሽ በመሆኑ፣ ምሉዕና ስፉሕ፣ ረቂቅና ምጡቅ፣ ኃያልና ግሩም ለሆነው ለእግዚአብሔር አካል ምሳሌነት እንጂ እኩልነት እንደሌለው መረዳት ያስፈልጋል፡፡

ሰማይ ዙፋኔ ነው ምድርም የእግሬ መረገጫ ናት ማለቱ አካላተ እግዚአብሔር በሰማይና በምድር የመሉ ሰማይን ከነግሡ ምድርን ከነልብሱ በመሐል እጁ የያዘ መሆኑን የሚያስረዳ ነው፡፡ ( ኢሳ . 66:1 ) “ አኃዜ ዓለም በእራኁ ፣ ዓለምን በመሐል እጁ (በመዳፉ) የያዘ ነው፡፡(አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ) “ኩሉ እኁዝ ውስተ እዴሁ በከመ አርአዮ ለጴጥሮስ” ትርጉም፡- ለጴጥሮስ እንደአሳየው ሁሉ በዕጁ የተያዘ ነው (ቅዳሴ ሕርያቆስ ) ነቢይ ሙሴ “ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበዓምሳሊነ”፣ ሰውን በአርዓያችን እንፍጠር ያለውን ” አርዓያ እግዚአብሔር የተባለች ነፍስ እንደሆነች፣ ” በአርዓያ እግዚአብሔር የተፈጠረች ነፍስ አለችን” እያሉ ቅዱሳን ሐዋርያትና ሌሎችም ሊቃውንት መስክረዋል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ” ወብነ ነፍስ እንተ ኢትመውት ወኢትማስን በህላዌሃ፣ በባሕርይዋ የማትሞት የማትፈርስ የማትበሰብስ ነፍስ አለችን” ብለዋል፡፡ (አመክንዮ ዘሐዋርያት) ” ዛ ይዕቲ አርዓያ ገጹ ለእግዚአብሔር ወአምሳሊሁ ኰናኒተ ሥጋ ወኃይሉ ፤ የእግዚአብሔር መታወቂያው የምትመስለውም ሥጋን የምትገዛው የሥጋ ዕውቀቱ ነፍስ ናት “ በማለት አሞንዮስና አውሳብዮስ የተባሉ ሊቃውንት በመቅድመ ወንጌል ጽፈዋል፡፡ ቅዱስ ኤጲፋንዮስም “ወብነ ነፍስ እንተ ኢትመውት ወኢትማስን በህላዌሃ ይዕቲኬ ርቱዕ ትሰመይ አርዓያ እግዚአብሕር ፤ የማትሞት፣ የማትፈርስ የማትበሰብስ ነፍስ አለችን ይህችውም አርዓያ እግዚአብሔር ልትባል ይገባል” ሲል አክሲማሮስ በተሰኘው መጽሐፉ መስክሯል፡፡

ሀ.የነፍስ ከዊን

ስለዚህ ነፍስ ጥንት ቢኖራትም ፍጻሜ የሌላት በመሆንዋ፣ በርቀቷ፣ የማትፈርስ፣ የማትበሰብስ በመሆንዋ እና አንድ አካል ሦስት ኩነታት ያሏት በመሆንዋ ለሥላሴ አንድነትና ሦስትነት ከአካለ ሥጋ ምሳሌነት ይልቅ የአካለ ነፍስ ምሳሌነት የጎላ የተረዳ ነው፡፡ አንድ አካል ሦስት ኩነታት (ሁኔታዎች) ያሏት ነፍስ በመለኮት አንድ በአካል በስም በግብር በኩነታት ሦስት የሆነ እግዚአብሔርን ስለምትመስል አርዓያ እግዚአብሔር እንደተባለች ምሳሌነቷን (አርዓያ እግዚአብሔር መሆንዋን) አንድ በአንድ እንመልክት ። “በስመ እግዚአብሔር ዋህድ በመለኮት ዘይሤለስ በአካላት ወኩነታት” በመለኮት አንድ በአካላትና በኩነታት ሦስት በሚሆን በእግዚአብሔር ስም እናምናለን፡፡(መጽሐፈ ሥርዓት) ሥላሴ በአካልና በኩነታት ሦስት ናቸው ነገር ግን የኩነታት ሦስትነት እንደ አካላት ሦስትነት አይደለም፡፡ አካላት መጠቅለልና መቀላቀል ሳይኖርባቸው በተከፍሎ በተፈልጦ በፍጹም መልክ በፍጹም ገጽ በየራሳቸው የቆሙ ናቸው፡፡ ኩነታት ግን ተፈልጦ ተከፍሎ (መለየት መከፈል) ሳይኖርባቸው በተዋሕዶና በተጋብኦ በአንድነት አካላትን በህልውና (በአኗኗር) እያገናዘቡ በአንድ መለኮት የነበሩ፣ ያሉና የሚኖሩ ናቸው፡፡እኒህም ከዊነ ልብ፣ ከዊነ ቃል ከዊነ እስትንፋስ ናቸው፡፡

ከዊነ ልብ

ከዊነ ልብ በአብ (በራሱ) መሠረትነት አካላዊ ልብ አብ ለራሱ ለባዊ (አዋቂ) ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልቡና እውቀት (ማወቂያ) መሆን ነው፡፡

ከዊነ ቃል

ከዊነ ቃል አካላዊ ቃል ወልድ በአብ መሠረትነት ለራሱ ነባቢ (ተናጋሪ) ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ (መናገሪያ) መሆን ነው፡፡

ከዊነ እስትንፋስ

ከዊነ እስትንፋስ አካላዊ እስትንፋስ መንፈስ ቅዱስም በአብ መሠረትነት ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወት መሆን ነው፡፡ የኩነታት ሦስትነት ይህ ነው ። “ንግበር ሰብአ በአርዓያነ ወበአምሳሊነ” ሰውን በአርዓያችንና በአምሳላችን እንፍጠር ብሎ በአርዓያውና በአምሳሉ ሰውን በመፍጠሩ የአንድነቱንና የሦስትነቱን ምሥጢር አንድ አካል ሦስት ኩነታት (ሁኔታዎች) ባሏት በነፍስ ከዊን ባለቤቱ አስተምሮናል ( ዘፍ . 1-26 ) ።

የነፍስ አካልዋ አንድ ሲሆን በባሕርይዋ ሦስት ከዊን አላት፡፡

ይኸውም ልብ ቃል እስትንፋስ ነው፣ ነፍስ በባሕርይዋ ሦስት ከዊን ያላት መሆንዋ አካሏን ከሦስት አይከፈለውም፡፡ ነፍስ በአካል ከሦስት ሳትከፈል የልብነቷ ከዊን (ልብ የመሆንዋ) ከቃልዋና ከእስትንፋስዋ ከዊን ሳይለይ በራሱ ከዊን ከሥጋ ልብ ጋር ይዋሐዳል፡፡ የቃልነትዋም ከዊን (የቃሏ ከዊን) ከልብነቷ ከዊንና ከእስትንፋስዋ ከዊን ሳይለይ በራሱ ከዊን ከሥጋ አንደበት ጋር ይዋሐዳል፡፡ የእስትንፋስዋም ከዊን (ሕይወት የመሆኗ) ከልብነቷ ከዊን እና ከቃልዋ ከዊን ሳይለይ በራሱ ከዊን ከሥጋ እስትንፋስ ጋር ይዋሓዳል፡፡

በዚህ ምክንያት ሰው ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡ ሦስት ኩነታት ያሏት ነፍስ በአካሏ አንዲት ነፍስ እንጂ ሦስት ነፍሳት እንደማትባል ሁሉ በአካል፣ በስም በግብር፣ በኩነት ሦስት የሆኑ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም፣ በመለኮት አንድ አምላክ ይባላሉ እንጂ ሦስት አማልክት አይባሉም፣ በአካሏ አንዲት የሆነች ነፍስ ሦስት ኩነታት እንደ አሏት በመለኮት አንድ አምላክ የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም ሦስት አካላት ሦስት አስማት ሦስት ግብራት አሉት፡፡ በአካል አንዲት የሆነች ነፍስ በሦስት ኩነታት ለባዊት ነባቢት ሕያዊት ስለሆነች፣ በለባዊነቷ አብ በነባቢነቷ ወልድ በሕያውትነቷ መንፈስ ቅዱስ የሚመሰሉ ስለሆነ ነው ። ሰውን በአርዓያውና በአምሳሉ የፈጠረው (ዘፍጥ.1-27) “ህየንተ ልብ ዘዝየ ነአምሮ ለአብ ወህየንተ ቃል ዘዝየ ነአምሮ ለቃል ዘእግዚአብሔር ወህየንተ እስትንፋስ ዘዝየ ነአምሮ ለመንፈስ ቅዱስ ፤ በእኛ ባለ በልብ አምሳል አብን እናውቀዋለን እንደ አብ እንደ መንፈስ ቅዱስ ባለ በፍጹም ገጽ በፍጹም መልክዕ አካልና ባሕርይ እንደ አለው በእኛ ባለ በቃል አምሳል ቃለ እግዚአብሔር ወልድን እናውቃለን፣ አብን አህሎ (መስሎ) የተወለደ የአብ ልጅ ነውና፡፡ በእኛ በአለው በእስትንፋስ አምሳል መንፈስ ቅዱስን እናውቀዋለን” ብሎ የአብ ልብነት በልብ የወልድ ቃልነት በቃል የመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት በእስትንፋስ መመሰላቸውን አስረድቷል፡፡ (ቅዱስ ቴዎዶጦስ ዘእንቈራ ሃይ.አበ. ምዕ . 53 ቁ.19)

የነፍስ ሦስትነት የአካል አይደለም የከዊን ነው የሥላሴ ሦስትነት ግን የአካል የስም የግብር ነው፡፡ በነፍስ ከዊን የተገለጠው የሥላሴ ከዊን በእሳት፣ በፀሐይ፣ በቀላይ፣ (ባሕር) ……… ከዊን ይመሰላል፡፡

ለ. የእሳት ከዊን

እሳት አንድ ባሕርይ ሲሆን ሦስት ከዊን አለው፡፡ይኸውም ነበልባል፣ ብርሃን ዋዕይ ነው፡፡በነበልባሉ አብ በብርሃኑ ወልድ በዋዕዩ (በሙቀቱ) መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ ይኸውም ተፈልጦ ተከፍሎ ሳይኖርበት በአንድ ህላዌ (አኗኗር) የሚኖር ሲሆን ነበልባሉ ከእንጨት ወይም ከፈትልና ከዘይት ጋር ብርሃኑን እና ሙቀቱን ይሰጣል፡፡ ብርሃን ከነበልባልና ከዋዕይ ተከፍሎ ሳይኖርበት በራሱ ከዊን ከዓይን ብርሃን ጋራ ይዋሐዳል፣ እንደዚህም ወልድ በቃልነቱ ከዊን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ ሥጋ ለበሰ ብርሃነ እሳት ከዓይን ብርሃን ጋራ በተዋሐደ ጊዜ ነበልባልና ዋዕይ እንዳልተዋሐዱ ወልድም ሰው በሆነ ሥጋ በለበሰ ጊዜ በመለኮት አንድ ስለሆነ አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆኑ ሥጋ ለበሱ አያሰኝም፣ ባሕርይ አንድ ሲሆን ከዊን ይለየዋልና፡፡ ይህንም የሚያስረዳ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ቢጠይቀው፣ “አቡየ እሳት ወአነ ብርሃኑ ወመንፈስ ዋዕዩ፣ አባቴ እሳት (ነበልባል)ነው፣ እኔም (ወልድ) ብርሃኑ ነኝ፣ መንፈስ ቅዱስም ዋዕዩ (ሙቀቱ) ነው” ብሎ የአንድነቱንና የሦስትነቱን ህላዌ (አኗኗር)በእሳት መስሎ ነግሮታል፡፡ (መጽሐፈ ቀሌምንጦስ) ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንትም በቅዳሴያቸው፣ “አባቴ እኔና መንፈስ ቅዱስ እሳት፣ ነበልባል ፍሕም ነን” አለ ጌታ ብለው የመጽሐፈ ቀሌምንጦስን ቃል ደግመውታል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “አብ እሳት ነው ወልድ እሳት ነው መንፈስ ቅዱስም እሳት ነው በልዕልና ያለ ሕይወትነት ያለው አንድ እሳት ነው፡፡” በማለት የሥለሴን አንድነትና ሦስትነት በእሳት መስሎ ተናግሯል፡፡
ሦስት ከዊን ያለው እሳት አንድ ባሕርይ ይባላል እንጂ ሦስት ባሕርይ እንዳይባል በአካል በስም በግብር ሦስት የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም አንድ አምላክ ይባላል እንጂ ሦስት አማልክት አይባልም ፡፡

ሐ. የፀሐይ ከዊን

ፀሐይም አንድ ባሕርይ (አንድ አካል) ሲሆን ሦስትነት አለው፣ ይኸውም ክበብ፣ ብርሃን ዋዕይ (ሙቀት) ነው፡፡በክበቡ አብ፣ በብርሃኑ ወልድ በሙቀቱ መንፈስ ቅዱስ ይመሰላሉ፡፡ ብርሃነ ፀሐይ ከክበቡና ከዋዕዩ ተፈልጦ ተከፍሎ (መለየት መከፈል) ሳይኖርበት በራሱ ከዊን ከዓይን ብርሃን ጋር ይዋሐዳል፡፡ እንዲሁም ወልድ በቃልነቱ ከዊን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ሳይለይ በተለየ አካሉ ሰው ሆነ፡፡
ብርሃነ ፀሐይ ከዓይን ብርሃን ጋር በተዋሐደ ጊዜ ክበቡ እና ዋዕዩ እንዳይዋሐዱ ወልድም ሰው በሆነ ጊዜ መለኮት አንድ ስለሆነ አብና መንፈስ ቅዱስ ሰው ሆኑ አያሰኝም፡፡ባለቤቱ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አቡየ ፀሐይ ወአነ ብርሃኑ ወመንፈስ ቅዱስ ዋዕዩ ፣ አባቴ ፀሐይ ነው፣ እኔም ብርሃን ነኝ መንፈስ ቅዱስም ዋዕይ ነው “ ብሎ አንድነቱንና ሦስትነቱን በፀሐይ መስሎ ለቅዱስ ጴጥሮስ አስረድቶታል፡፡ (መጽሐፈ ቀሌምጦስ) ሦስት መቶ አሥራ ስምንቱ ሊቃውንትም በቅዳሴያቸው ንባብ “አቡየ ወአነ ወመንፈስ ቅዱስ ፀሐይ ወብርሃን ወዋዕዩ” በማለት ደግመውታል፡፡ አባ ሕርያቆስም “አብ ፀሐይ ነው፣ ወልድ ፀሐይ ነው መንፈስ ቅዱስም ፀሐይ ነው ከሁሉ በላይ የሆነ አንድ እውነተኛ ፀሐይ ነው” ሲል በፀሐይ መስሎ የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት ተናግሯል፡፡ ይህም ፀሐይ ሦስት ኩነታት ሳሉት አንድ ፀሐይ ይባላል እንጂ፣ ሦስት ፀሐይ እንደማይባል ሁሉ፣ በአካል፣ በስም፣ በግብር በኩነት ሦስት የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስም፣ በመለኮት አንድ አምላክ አንድ መለኮት ይባላል እንጂ ሦስት አማልክት ሦስት መለኮት አይባልም የፀሐይ ሦስትነት የአካል አይደለም የኩነት ነው እንጂ፣ የሥላሴ ሦስትነት ግን የአካል፣ የስም፣ የግብር፣ እና የኩነትም ነው፡፡ ምሳሌነቱን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን ፡፡አሜን:

ከመ/ር ዮሐንስ ለማ

share

Comments

  1. ዘመኑን ዋጁት እንዳልው ይህን በማርጋቸሁ እ/ር ይስጣችሁ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *