በፊንላንድ ሄልሲንኪ የጥምቀት በዓል በታላቅ ድምቀት ተከበረ

በፊንላንድ ሄልሲንኪ የጥምቀት በዓል  በታላቅ  ድምቀት ተከበረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ ጥር  11 /አሥራ አንድ የሚከበረው የጌታችን የአምላካችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ጥምቀት በሄልሲንኪ ደብረ አሚን ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን  በተለየ  ሃይማኖታዊ ድምቀት ተከብሯል። የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡን ተከትሎ  ዘንድሮ  ሥርዓቱን በጠበቀና በደመቀ  መልኩ   ታቦተ ሕጉ በምእመናን ታጅቦ ከበዓሉ ዋዜማ  በሚከበረው የከተራ በዓል ጊዜያዊ ማረፊያው ጉዞ አድርጎል::

ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ድምቀት የተጀመረው የጥምቀት በዓሉ ሌሊቱን በካህናቱ አገልግሎት አድሮ ከሌሊቱ 10 /አሥር ሰዓት/ ጀምሮ የቅዳሴ ሥነ ሥርዓቱ ቀጥሏል። የቅዳሴው ሥርዓት ከተፈፀመ በኋላ ባሕረ ጥምቀቱ ተባርኮ ሕዝበ ክርስቲያኑም ጠበል ተረጭቷል።

የደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ  ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ   በአሉን አስመልክቶ  በተሰጠው ትምህርት ህዝበ ክርስቲያኑ የጥምቀት በዓልን ሲያከብር ለአገር  እና ስለ ምንኖርበት አገር መጸለ እንደሚገባው  አሳስበዋል::

በዕለቱ ተጋብዘው በእንግድነት የተገኙት ቀሲስ ሲሳይ በበኩላቸው በሰጡት ትምህርት

”እየሱስ ክርስቶስ ዮሐንስን አጥምቀኝ ማለቱ ለእኛ አብነት ለመሆንና ለቤተ ክርስቲያን ሥርዓትን ለመመሥረት ሲል ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ፡፡ ዮሐንስ ወደ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሔዶ አጥምቆት ቢሆን ኖሮ ምእመናን ቀሳውስቱን እቤታችን ድረስ መጥታችሁ አጥመቁን እንጂ ወደ ቤተ ክርስቲያን አንሔድም ባሉ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሌላት እንዳትሆን ሥርዓትን ለማስተማር ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ባሕር፤ በዮሐንስ እጅ ተጠመቀ” ብለዋል፡፡

ከከተራ የዋዜማ ዕለት ጀምሮ የደብሩ የጽጌ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤቶት መዘምራንም በዓሉን በተመለከተ ያሬዳዊ ዜማ በማቅረብ በዓሉን አድምቀውታል፡፡ ምንም እንኳን በፊንላንድ ወቅቱ ከፍተኛ የቅዝቃዜ ቢሆንም ያንን ሁሉ አስቸጋሪ የአየር ፀባይ በመቋቋም በዓሉ በተለየ ድምቀት ተከብሯል።

የጠበል መርጨት ሥነሥርዓት ከተከናወነ በኋላ ታቦተ ሕጉ በምእመናኑ ታጅቦ ወደ ደብሩ ተሸኝቷል።

በዚሁ የጥምቀት በዓል ላይ ቁጥራቸው በርከት  ያሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ  ኦርቶዶክስ  ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ምእመናን  ተገናኝተዋል::

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *