መልካም ጓደኛ

መልካም ጓደኛ

ስለ መልካም ጓደኛ ስናነሳ አስቀድመን የምንመለከተዉ

1ኛ/ የዳዊትንና የዮናታንን ጓደኝነት ይሆናል (1ኛ ሳሙ 20፡42)

ዮናታን ማለት ቅዱስ ዳዊትን ሊገድለዉ ያሳድደዉ የነበረ የእስራኤል የመጀመሪያዉ ንጉስ የሳኦል ልጅ ነዉ። ንጉስ ሳኦልን እግዚአብሔር ለእስራኤል ንጉስነት የቀባዉ ከምንም ነገር ከአህያ ጠባቂነት አንስቶ በእግዚአብሔር ወዳጅ በነብዩ ሳሙኤል አማካኝነት ነበር። 1ኛ ሳሙ 9 እና 10. ነገር ግን ንጉስ ሳኦል ከእግዚአብሔር ያገኘዉን የንግስና ክብርና ሞገስ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ባለመጠበቅና ከምንም አንስቶ ከፍ ከፍ ያደረገዉን እግዚአብሔርን ከመከተል ፈቀቅ በማለት የስጋ ፍላጎቱንና የአይን አምሮቱን መከተል ጀመረ። እንደ ትእዛዙም ባለመሄድ የተሰጠዉን ጸጋ አቃለለ 1ኛ ሳሙ 13፡14 እና 1ኛ ሳሙ 15፡10-12። እኛም የስጋ ፍላጎታችንን እና የአይን አምሮታችንን ብቻ ከተከተልን የእግዚአብሔርን ጸጋ እንደምናጣ የሳኦል ታሪክ ያጠይቀናል። እንዲያዉም እግዚአብሔር አምላክ ሳኦልን ለእስራኤላዊያን በማንገሱ እስከመፀፀት እንደደረሰ በዚህ የመጽሐፍ ክፍል ዉስጥ እናያለን። በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርም ጸጋና ሀይል ንጉስ ሳኦልን ስለተለየዉ እርኩስ መንፈስ በላዩ ላይ ስልጥኖበት በየጊዜዉ ያስጨንቀዉ ነበር። ይህም ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክ ብላቴናዉን ዳዊትን ከበግ እረኝነት አንስቶ ለእስራኤል ንጉስ አድርጎ በመቀባት ስላነገሰዉ ንጉስ ሳኦል በቅናት ተነሳስቶ እግዚአብሔር አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ያሳደረበትን ብላቴናዉን ንጉስ ዳዊትን ሊገድለዉ ያሳድደዉ ነበር። ከዚህ እንደምንረዳዉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያደረባቸዉን ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያምንና ቅዱሳንን የሚያሳድዱ ሁሉ እርኩስ መንፈስ ያደረባቸዉ ሰዎች እንደሆኑ እናያለን። ይሁን እንጅ የንጉስ ሳኦል ልጅ ዮናታን አባቱ ሊገድለዉ ከሚያሳድደዉ ከዳዊት ጋር የልብ ወዳጅና ጓደኛሞችም ስለነበሩ ይለናል። እንዲያዉም ዮናታን አባቱ ሳኦል ቅዱስ ዳዊትን ለመግደል የሚያወጣዉን እቅድ በሙሉ ቀድሞ እያወጣ እንደ ነፍስ ይወደዉ ለነበረዉ ለጓደኛዉ ለዳዊት በጎን መልዕክት እየላከና ምልክት እያሳየ የቅዱስ ዳዊትን ነፍስ ከሞት ይታደግለት ነበር።

መልካም ጓደኛ እንደ ዳዊትና እንደ ዮናታን ነዉ ስንል መቼም በምንኖርባት አለም ብዙዎቻችን ከማንናኛዉም ነገር በላይ ለስጋችንና ለዘራችን እናደላለን። ከዚህም የተነሳ ሰዎች በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ዘርን ስንቆጥሩ፤ የዝምድና ሀረግንና የጋብቻ ትስስራቸዉን እየመዘዙ ፍትህን ስያዛቡ፤ የተቸገሩትን ሲገፉ እንደሚገኙ ሀገር ያወቀዉና ፀሐይ የሞቀዉ ጉዳይ ነዉ። በተመሳሳይም ማናችንም ብንሆን እድሉን ብናገኝ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አንልም። በሌላም መልኩ በጓደኝነትና በትዉዉቅ የምንሰራቸዉ ብዙ ጥፋቶችም አሉ። ይሁን እንጅ በዚህ መልኩ እንደመከታ የገነባናቸዉ ዘመድ አዝማድና ጓደኞቻችን ማንነታችንን የሚፈታተንና ሰብዕናችንን የሚገዳደር ችግርና ፈተና ሲገጥመን በደህና ቀን ባስቀመጥናቸዉ የከፍታ ማማ ላይ ሳይገኙ ወዲያዉኑ ሸርተት በማለት ፊታቸዉን ሲያዞሩብንና በራቸዉን ጥርቅም አድርገዉ ሲዘጉብን ስንመከት ደግሞ ችግራችንና ሀዘናችንን የበለጠ የከፋ ያደርገዋል። ዮናታን ግን ንጉስ ዳዊትን በችግሩ ጊዜ አልካደዉም፤ በችግሩ ጊዜ አልተንሸራተተበትም፤ በችግሩ ጊዜም አልተለወጠበትም። እንዲያዉም ምንድን ነበር ያለዉ? ወዳጄ ዳዊት ሆይ አባቴ እንደሚያሳድድህ አዉቃለሁ፤ በአባቴም እጅ ብትወድቅ እደሚገድልህ አዉቃለሁ፤ አለና እኔ ግን «አልክድህም አልለወጥብህምም» በማለት ቃል ኪዳኑን የበለጠ አፀናለት። እንዲያዉም አስቀድሞ አባቱ ንጉስ ሳኦል የሚያወጣዉን እቅድ ለንጉስ ዳዊት እየላከ ጓደኛዉ ዳዊት ከሞት የሚያመልጥበትን መንገድ ያመቻች ነበር። መልካም ጓደኛ ማለት ከጥፋት የምንርቅበትንና ከሞት የምናመልጥበትን መንገድ እንደ ዮናታን የሚያመቻችልንና የሚመክረን መሆን አለበት። ቂም በቀልህን ተዉ፤ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ሂድ፤ ቅዱስ ቃሉን ስማ፤ ንስሀ ግባ ቅዱስ ስጋዉን ክቡር ደሙን ተቀበል እያለ እንደ ዮናታን ከሞት እንድናመልጥ የሚመክረን ጓደኛ መሆን አለበት። ምክንያቱም በሀጢያት መኖር ሞት ነዉ፤ የሀጢያት ደሞዝ ደግሞ ሞት ነዉ። ለዚያዉም የዘላለም ሞት። ስለሆነም የምንይዘዉ ጓደኛ እንደ ዮናታን ከሞት ወደ ህይዎት የሚመልሰን መሆን አለበት።

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *