መልካም ጓደኛ

ሁላችንም እንደምናዉቀዉ በጎ ጓደኛ እንዳለ ሁሉ ክፉ ጓደኛ ይኖራል። እነዲሁም ክፉ ጓደኛ እነዳለ ሁሉ በጎ ጓደኛም አለ። ከዚህ አንጻር ሀይማኖተኛ ጓደኛ እነዳለ ሁሉ ከሀዲ ጓደኛም ይኖራል፤ ወደ ህይዎት የሚመራ ጓደኛ እንዳለ ሁሉ ወደ ሞት የሚመራ ጓደኛም አለ፤ ወደ ብርሃን የሚመራ ጓደኛ እነዳለ ሁሉ ወደ ጨለማ የሚመራ ጓደኛም አለ። ስለሆነም ጓደኛ ከመያዛችን በፊት ሁላችንም ጓደኞቻችን ስለሚሆኑ ሰዎች አስቀድመን ልንመረምር ይገባናል። ልበ አምላክ ዳዊት በመዝሙሩ እንደከተበዉ በመዝሙር 17፡25 ላይ «ከቸር ሰዉ ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ፤ ከቅን ሰዉ ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ፤ ከንፁሕ ሰዉ ጋር ንፁሕ ሆነህ ትገኛለህ፤ ከጠማማ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ» ይለናልና። በዚህም ቅዱስ ዳዊት ከምን አይነት ሰዉ ጋር ዉለን ምን አይነት ሰዉ ልንሆን  እንደምንችል ይነግረናል። ምክንያቱም ሰዉ የሚመስለዉ ከጓደኛዉ ጋር ከሚኖረዉ መልካምም ይሁን መጥፎ በተላበሰዉ ባህሪ ነዉና።

እንግዲህ ልበ አምላክ ዳዊት በመዝሙሩ ከቸር ሰዉ ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ ሲል፤ ንጽሐ ስጋን ከንጽሐ ነፍስ ጋር አንድ አድርጎ ከያዘ፤ በልቡናዉ ቅን ከሆነና የሰማዩን መንገድ እያሰበ፤ ዕለት ዕለት ምግባርና ትሩፋትን ገንዘቡ በማድረግ ከሀጢያትና ከበደል ከራቀ ሰዉ ጋር ከዋልላችሁ እነዚህን ሀብታት በሙሉ እናንተም በመተግበር በምግባር ትመስሉታላችሁ ሲለን ነዉ። በሌላ አነጋገርም ከቸር ሰዉ ጋር ቸር ሆነህ ትገኛለህ ሲል ንጽሐ ስጋን ገንዘባቸዉ አድርገዉ ምንም እንኳን በህሊናቸዉ የተለያየ ሀጢያት ቢመላለስም በትዕግስት ጸንተዉና ታግሰዉ ሁልጊዜም ረድኤተ እግዚአብሔርን እያሰቡ በህሊናቸዉ እየመጣ የሚያስጨንቃቸዉን ሀጢያት በገቢር ባለመፈጸም ሰይጣንን ድል ከሚያደርጉት ሰዎች ጋር ከዋላችሁ እናንተም ይህንን ጸጋ የማግኘት እድል ይኖራችኋል ማለቱ ነዉ። ከዚህ በተቃራኒዉ ደግሞ ሁልጊዜ ሀጢያትንና በደልን ከሚፈጽም ሰዉ ጋር ጓደኝነት መስርተን ብንኖር ነገ ከነገ ወዲያ እኛም ሀጢአትንና በደልን የምንፈጽም እንሆናለን ማለቱ ነዉ። ሌላዉ ደግሞ ከንጹሕ ሰዉ ጋር ንጹህ ሆነህ ትገኛለህ ማለቱ ነፍሱን ሳያቆሽሽ በንጽህና ጸንቶና ንጽህናዉን ጠብቆ ከሚኖር ጋር ጓደኝነትን ብትመሰርቱ የእርሱን አርአያ ምሳሌ ወስዳችሁ እንደሱ ንጽህናን ሀብታችሁ ታደርጋላችሁ፤ እናንተም ነፍሳችሁን በበደልና በክፋት ሳታረክሱ ብትኖሩ የዚያን ሰዉ ንጸሀ ነፍስ አብነት አድርጋችሁ ከንጽሀ ነፍስ ማዕረግ ትደርሳላችሁ ማለቱ ነዉ። እንደገናም ከቅን ሰዉ ጋር ቅን ሆነህ ትገኛለህ ሲል ንጽሐ ልቡና ካለዉና ልቡናዉን ቀድሶና ከሀሳብ ሀጢያት ተለይቶ ክፉ ምኞት ከጠፋለት ሰዉ ጋር  ጓደኝነትን ብትመሰርቱ ከእርሱ ምሳሌን በመዉሰድ ቀስ በቀስ በመንፈሳዊ ህይዎት በማደግ እንደሱና እንደሷ ንጽሐ ልቡናን ገንዘባችሁ ታደርጋላችሁ ማለቱ ነዉ። ንጽሐ ልቡና ላይ መድረስ እጅግ ታላቅ ብቃት ነዉ። ምክንያቱም ንጹህ ልቡና ያላቸዉ ሰዎች  እግዚአብሔርን ማየት ይችላሉና ነዉ። ጌታችንና አምላካችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ላይ ስብከቱ ስለ አንቀጸ ብጹአን ሲያስተምር «ልበ ንጹሆች ብጹአን ናቸዉ እግዚአብሔርን ያዩታልና » ማቴ 5 ብሎናልና። ሌላዉና የመጨረሻዉ ከጠማማ ሰዉ ጋር ጠማማ ሆነህ ትገኛለህ ማለት ከከሀዲ ሰዉ ጋራ ጓደኝነት ከመሰረታችሁ ነገ ከነገ ወዲያ እናንተም ከሀዲ ትሆናላችሁ፤ ከተጠራጣሪ ሰዉ ጋር አብራችሁ ከዋላችሁ እናንተም በእኩይ ምግባሩ ተስባችሁ ተጠራጣሪና መናፍቅ ትሆናላችሁ፤ መንፈሳዊ ነገር ሲነገር ከሚቀልድና ቧልት ከሚያወራ ሰዉ ጋር ጓደኛ ከሆናችሁ እናንተም ነገ ከነገ ወዲያ በእግዚአብሔር ቃል የምትቀልዱ፤ በሀይማኖት የምትቀልዱ፤ በቤተክርስቲያን ስርዓት የምትቀልዱ፤ በቅዱስ ታቦቱና በቅዱስ ስዕላቱ የምትቀልዱና ቧልተኞች ትሆናላችሁ ሲለን ነዉ። እንግዲህ ከነብዬ እግዚአብሔር ከልበ አምላክ ዳዊት የምክር ቃል እንደምንረዳዉ የሰዉ ልጅ ከዕለት ዉሎዉ በመነሳት በመልካም ወይም በክፉ የጓደኛ ተጽእኖ ስር ሊወድቅ እንደሚችል ነዉ። ከዚህም በመነሳት ባጠቃላይ ከላይ ከዘረዘርናቸዉ የጓደኛ ተጽእኖዎች በመነሳት ጓደኝነትን በሁለት ከፍለን ይሄዉም መልካም ጓደኛ እና ክፉ ጓደኛ ብለን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አንድምታና ዋቢ አድርገን እንመልከታለን።

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *