ምሥጢረ ሥላሴ – ክፍል ፩

ምሥጢረ ሥላሴ - ክፍል ፩

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረ፤ ያለና የሚኖር አንድ አምላክ መኖሩን ታምናለች፡፡ ይኸውም አንድ አምላክ፤ በአካል፤ በስም፣ በግብር ሦስት፤ በመለኮት አንድ የሆነ አንድ እግዚአብሔር አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ መሆኑን አምና ታሳምናለች፤ ተምራ ታስተምራለች፡፡ ስለ እግዚአብሔር አንድነትና ሦስትነት፤ ፈጣሪነትና መጋቢነት… የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባላት ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ መሰረት ከአምስቱ አእማደ ምሥጢር አንደኛውን ክፍል ምሥጢረ ሥላሴን እንመለከታለን፡፡

ሥላሴ ማለት ሠለሰ ሦስት አደረገ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተወሰደ ሲሆን ትርጓሜውም ሦስት ሦስትነት ማለት ነው፡፡ ሥሉስ ቅዱስ ማለት ደግሞ ልዩ ሦስት ማለት ነው፡፡ ልዩነቱም የአካል ሦስትነት ካላቸው የህልውና አንድነት ከሌላቸው ከአብርሃም፣ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ሦስትነት የተለየ በመሆኑ ነው፡፡

ሥሉስ ቅዱስ (ሥላሴ) የተባሉም አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ናቸው፡፡ በዓይን የማይታይ በእጅ የማይጨበጥ በፍጹም ልቡና ብቻ አምነው የሚያመልኩት ቅድመ ዓለም የነበረ በማዕከለ ዓለም ያለ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ዓለምን ፈጥሮ የሚመግብ አንድ አምላክ የሆነ የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስ ባሕርይ የፍጡራን አእምሮ ተመራምሮ የማይደርስበት በመለኮት አንድ ሲሆን በአካል በስም በግብር ሦስት ነው ማለት ረቂቅ ነውና የሥላሴን አንድነትና ሦስትነት የሚናገረው ክፍለ መጽሐፍ ምሥጢረ ሥላሴ ተብሏል፡፡

ሥሉስ ቅዱስ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፤አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ልዩ ሦስት ነው፤ ልዩ ሦስት የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ማቴ. 28፡19 ቅዱስ ባስልዮስ በሥርዓተ ቅዳሴ (ሃይ አበው ዘጎርጎርዮስ) አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ነው፤ አንድ እግዚአብሔር የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አንሰ ሶበ እቤ እግዚአብሔር እብል በእንተ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ እስመ አሐዱ ውእቱ መለኮተ ሥላሴ ወሠለስቲሆሙ አሐዱ በመለኮት፡፡ እኔ እግዚአብሔር ባልሁ ጊዜ ስለ አብ፣ ስለ ወልድና ስለ መንፈስ ቅዱስ እናገራለሁ፤ የሦስቱ መለኮት አንድ ነውና ሦስቱም በመለኮት አንድ ናቸውና፡፡ (ቅዱስ ባስልዮስ ዘአንጾኪያ፡ ሃይ. አበው ም. 96፡6)

አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ነው፤ አንድ አምላክ የሆነ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ግዕዝ፡- አብ አምላክ ወልድ አምላክ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ወኢይትበሃሉ ሠለስተ አማልክተ አላ አሐዱ አምላክ፡፡ ትርጓሜ፡- አብ አምላክ ነው ፤ ወልድ አምላክ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ አምላክ ነው ነገር ግን አንድ አምላክ ይባላል እንጂ ሦስት አማልክት አይባልም፡፡ (ሐዋርያዊ አትናቴዎስ ሃይ. አበው ም. 24 ቁ. 4) አንድ አምላክ የሆኑ አብ ወልድና መንፈስ ቅዱስ፤ በአካል በስም በግብር ሦስት ሲሆኑ በመለኮት፤ በባሕርይ፤ በህልውና፤ በፈቃድ፤ በመንግሥትና በሥልጣን … አንድ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከሥጋችን ጋራ ተዋሕዳ ያለች የነፍሳችን /የራሳችን/ ባሕርይ ተመራምረን አካሏንና መጠኗን ባሕርይዋንና ሁኔታዋን ተፈላስፈን ማወቅ የማንችል እኛ የፍጡራን አእምሮ ተመሯምሮ የማይደርስበት የፈላስፎችም ፍልስፍና ተፈላስፎ የማያገኘው ምሉዕና ስፉሕ፤ ረቂቅና ምጡቅ፤ ኃያልና ግሩም… የሆነ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ቅዱሳት መጻሕፍት ከነገሩን /ካስነበቡን/ አበው ሊቃውንት ካስተማሩን ከሚገባን አልፈን መመራመር እንደማይገባን፤ የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት ስንኳ ተመሯምሮ ያልደረሰበት ጥልቅ (ረቂቅ) ባሕርዩን ለመመራመር አንራቀቅ ሲል አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው አስረድቶናል፡፡ 318ቱ ሊቃውንትም “ንእመን ዘእንበለ ተሐሥሦ” በአምላክነቱ፣ በፈጣሪነቱና በመጋቢነቱ ያለ መመራመርና ያለ መጠራጠር እንመን በማለት ያለመጠራጠር በእግዚአብሔር አምነን በአምልኮቱ ጸንተን እንድንኖር አስተምረውናል፡፡ (ሃይ አበው ዘሠለስቱ ምዕት)

የባሕርይ ምስጋና

አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ዓለም ሳይፈጠር እንደዛሬው ሁሉ በአንድነት በሦስትነት ይሠለሱ፤ ይቀደሱ (ይመሰገኑ) ነበር፡፡ ፍጡራን ሳይኖሩ ማን ያመሰግናቸው ነበር? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒችን ኢየሱስ ክርስቶስ “አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ከአንተ ዘንድ በነበረ ክብሬ (ጌትነቴ) አክብረኝ” ሲል ቅድመ ዓለም ክብርና ምስጋና እንደነበረው አስረድቶናል። (ዮሐ. 8፡54 ፤ 12-27፤ 17፡5 ) ግዕዝ፡- “አኮ ዘንጽሕቅ ስብሐተ እምኀበ ዘፈጠርነ ስብሐቲነሰ እምኀቤነ ውእቱ” ትርጉም፡- ከፈጠርነው ፍጥረት ምስጋና የምንሻ አይደለንም ምስጋናችን የባሕርያችን ነው እንጂ በማለት ከፍጡራን ምስጋናን የማይሹ ምስጋና የባሕርያቸው መሆኑን ሥላሴ አስረድተውናል /መጽሐፈ ቀሌምንጦስ ይመልከቱ፡፡ ይህንንም ይዞ ሊቁ ዮሐንስ አፈወርቅ በቅዳሴው፤ ንባብ፡- “ስብሐቲሁ ዘእምኀቤሁ ወውዳሴሁ እምዚአሁ ምሉዕ ወፍጹም ብዕለ ጸጋሁ እምኀበ አቡሁ ተሰብሐ ወእምኔሁ ተቀደሰ” ትርጉም፡- ክብሩ ከርሱ የተገኘ ነው ምስጋናውም ከርሱ የተገኘ ነው የጸጋውም ብዕል ምሉዕና ፍጹም ነው ከአባቱ ዘንድ ተመሰገነ ከራሱም ከበረ (ተመሰገነ) በማለት ምስጋና የባሕርዩ መሆኑን አስረድቷል፡፡ (ቅዳሴ ዮሐ. አፈ. ቁ.13 እና 30 ወንጌል ዮሐንስ 12፡27) ምስጋና የባሕርያቸው ስለሆነ እኛ ዛሬ ሥላሴን ማመስገን አይገባንም ማለት እንዳልሆነ መረዳት ያስፈልጋል፡፡ እኛ ዛሬ የምናመሰግነው ምስጋና አምልኮቱን ለመግለጽ ነው፤ ይህም ማለት የእግዚአብሔርን አምላክነቱንና ፈጣሪነቱን፤ ከሃሊነቱንና መጋቢነቱን አምነን ከእርሱ በረከተ ሥጋንና ነፍስን አግኝተን ከመከራ ሥጋ እና ከመከራ ነፍስ ድነን ስሙን እየቀደስን ክብሩን ወርሰን እንድንኖር ነው እንጂ እኛ ብናመሰግነው ክብር የሚጨመርለት እኛ ባናመሰግነው ክብሩ የሚቀነስበት ሆኖ አይደለም፡፡

የሥላሴ አንድነትና ሦስትነት

ሥላሴ (ሥሉስ ቅዱስ) በአካል በስም በግብር እና በኩነት ሦስት ሲሆኑ፣ በመለኮት በባሕርይ በህልውና በፈቃድ በመንግሥትና በሥልጣን …. በመሳሰለው አምላካዊ አንድነት ሁሉ አንድ ናቸው፡፡

ሀ/ የአካል ሦስትነት

የአካል ሦስትነታቸው እንደምን ነው ብትል? ለአብ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክእ አለው፤ ለወልድም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክእ አለው፤ ለመንፈስ ቅዱስም ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክእ አለው፡፡ ማስረጃ፤ አብ በአካሉ በገጹ በመልኩ ፍጹም ነው፡፡ ወልድም በአካሉ በገጹ በመልኩም ፍጹም ነው፤ መንፈስ ቅዱስም በአካሉ በገጹ በመልኩም ፍጹም ነው ሲል አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት አስረድቶናል። ( ሃይ አበ ዘአትናቴዎስ)

ለ/ የሦስትነት ስማቸው

በሦስትነት ስማቸው፡- አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ስማቸው ወላዲ ተወላዲ ሠራጺ ልብ ቃል እስተንፋስ ይባላሉ፡፡

ሐ/ የስም ሦስትነት

የስም ሦስትነታቸው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ በአካል ተለያይተው በሦስትነት የሚጠሩበት የአካል ስማቸው ነው፡፡ ( ማቴ. 28፡19) ይህ ስማቸው በዚህ ጊዜ ተገኘ የማይባል አካላቸው ሲኖር የነበረ ያለ እና የሚኖር አካላዊ ስማቸው ነው፡፡ “ወአቃኒመ እግዚአብሔርሰ እሙንቱ አስማት ወአስማትኒ እሙንቱ አቃኒም እስመ ትርጓሜሁ ለአቃኒም አካላት ጽኑዓን ወቀዋምያን ፍጹማነ ገጽ ወመልክዕ ብሂል ወሥሉስ ቅዱስ ይሰመዩ አስማተ ጽኑዓነ” ትርጉም፡- የእግዚአብሔር አቃኒም አስማት (ስሞች) ናቸው፡፡ አስማትም /ስሞችም/ አቃኒም ናቸው፡፡ የአቃኒም ትርጓሜም በመልክ በገጽ ፍጹማን ሁነው ጸንተው የሚኖሩ አካላት ማለት ነውና ልዩ ሦስት የሚሆኑ አካላትም ጸንተው በሚኖሩ በኒህ ስሞች ይጠራሉ በማለት አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አካላቸው ሲኖር የነበረ ያለና የሚኖር አካላዊ ስማቸው መሆኑን ቅዱስ ጎርጎርዮስ አስረድተናል፡፡ (ሃይ አበው ም. 13 ቁ 4-6)

ይህም ስማቸው አይፋለስም አይለወጥም በየስማቸው ጸንተው ሲመሰገኑ ይኖራሉ እንጂ ማለት “አብ አብ ይባላል እንጂ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፤ ወልድም ወልድ ይባላል እንጂ አብ መንፈስ ቅዱስ አይባልም፤ መንፈስ ቅዱስም መንፈስ ቅዱስ ይባላል እንጂ አብ ወልድ አይባልም ሲል የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳስ አግናጥዮስ አስረድቶናል”፡፡ (ሃይ አበው ዘአግናጥዮስ ክፍል አንድ) በሦስትነት ስማቸው አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ የተባሉትም በአንድነት ስማቸው አንድ እግዚአብሔር ይባላሉ፡፡ ግዕዝ፡- ሠለስቱ ስም አሐዱ እግዚአብሔር ትርጉም፡- ሦስት ስም አንድ እግዚአብሔር (አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው)

መ/ የግብር ሦስነትነት

የግብር ሦስትነት እንደምን ነው? ብትል ወላዲ፣ ተወላዲ፣ ሠራጺ ነው ይህም ማለት የአብ ግብሩ መውለድ የወልድ ግብሩ መወለድ የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ማለት ነው፡፡ የግብር ሦስትነት ስማቸው የግብር ሦስትነት ስማቸው፣ ወላዲ ተወላዲ ሠራጺ በግብር ተለያይተው በሦስትነት የሚጠሩበት የግብር ስማቸው ነው፡፡ ይህም ከነባለቤቱና ከነቅጽሉ ሲገለጽ አብ ወላዲ፣ ወልድ ተወላዲ መንፈስ ቅዱስ ሠራጺ ማለት ነው፡፡ አብ ወልድን ቢወልድ መንፈስ ቅዱስን ቢያሠርጽ እንጅ እንደ ወልድ አይወለድም እንደ መንፈስ ቅዱስ አይሠርጽም ወልድም፤ ቢወለድ እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርጽም እንደ መንፈስ ቅዱስም አይሠርጽም፤ መንፈስ ቅዱስም ቢሠርጽ እንጂ እንደ አብ አይወልድም አያሠርጽም እንደ ወልድም አይወለድም፡፡ ማስረጃ፡- አብ አልተወለደም ዓለም ሳይፈጠር ወልድን ወለደ እንጂ ወልድም ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር አብ ተወለደ መንፈስ ቅዱስም ዓለም ሳይፈጠር ከእግዚአብሔር አብ ሠረጸ ሲል ሦስቱ አካላት በግብር የተለያዩ እንደሆኑ እና በግብር ተለያይተው የሚጠሩባቸው ሦስት የግብር ስሞች እንዳሏቸው ቅዱስ አትናቴዎስ ሊቀ ጳጳሳት አስረድቷል፡፡ (ሃይ አበው ዘአትናቴዎስ ክፍል 4)

ሠ/ የከዊን ሦስትነት

የከዊን ሦስትነት ከዊነ ልብ ከዊነ ቃል ከዊነ እስትንፋስ ነው፡፡ የከዊን ሦስትነት ስማቸው ልብ፣ ቃል ፣ እስትንፋስ ነው፤ ልብ ቃል እስትንፋስ በከዊን ተለያይተው በሕልውና ተገናዝበው በሦስትነት የሚጠሩበት የከዊን ስማቸው ነው፤ ይኸውም አብ አካላዊ ልብ ወልድ አካላዊ ቃል መንፈስ ቅዱስ አካላዊ እስትንፋስ ማለት ነው፡፡ በሌላ አገላለጽ፡- ልብ አብ ለራሱ ለባዊ (አዋቂ) ሆኖ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልቡና (እውቀት) መሆኑን የሚያመለክት የከዊን ስሙ ነው፡፡ ቃል ወልድም ለራሱ ነባቢ (ተናጋሪ) ሆኖ ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ንባብ (መናገሪያ) መሆኑን የሚገልጽ የከዊን ስሙ ነው፡፡ እስትንፋስ (ሕይወት) መንፈስ ቅዱስም ለራሱ ሕያው ሆኖ ለአብና ለወልድ ሕይወት የመሆን የከዊን ስሙ ነው፡፡ ስለዚህ በአብ ለባውያን በወልድ ነባብያን በመንፈስ ቅዱስ ሕያዋን ሁነው ይኖራሉ፤ ይህም ማለት በአብ ልብነት ሦስቱም ያስባሉ፤ በወልድ ቃልነት ሦስቱም ይናገራሉ፤ በመንፈስ ቅዱስ እስትንፋስነት ሦስቱም ሕያዋን ሁነው ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ ማስረጃ፡-አብ ለወልድና ለመንፈስ ቅዱስ ልባቸው ነው (ያስቡበታል)፡፡ ወልድም ለአብና ለመንፈስ ቅዱስ ቃላቸው ነው (ይናገሩበታል፤) መንፈስ ቅዱስም ለአብና ለወልድ ሕይወታቸው ነው (ሕያዋን ሁነው ይኖሩበታል) ሲል አቡሊዲስ ዘሮሜ መስክሯል፡፡(ሃይ አበ ዘአቡሊዲስ ኀበ በርደጊስ ክፍል 2)

ወስብሐት ለእግዚአብሔር ለዘበቅዱሳኒሁ ይሴባሕ ይእዜኒ ወዘልፈኒ ወለዓለመ ዓለም አሜን ወአሜን ለይኩን ለይኩን፡፡ አነሳስቶ ያስጀመረኝ አስጀምሮ ያስጨረሰኝ የቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ ይክበር ይመስገን ፡፡አሜን !!!!!!

ይቀጥላል

ከመ/ር ዮሐንስ ለማ

share

Comments

  1. DAMTEW MULUGETA DEREBEW : May 14, 2021 at 10:02 am

    Thank you.

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *