መልካም ጓደኛ
መልካም ጓደኛ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን
በዚህ በምንኖርበት አለም ይብዛም ይነስም አንድ ወይም ከዚያ በላይ ጓደኛ ይኖረናል። በእርግጥ በዚህ ጽሁፍ ዉስጥ ለመግለጽ የተፈለገዉ የወንድ ወይም የሴትን የተቃራኒ ፆታ የፍቅር ጓደኝነትን ሳይሆን መልካም የልብ ጓደኛ ማለት ምን ማለት ነዉ? የሚለዉን ለማየት ሲሆን ምናልባትም ብዙዎቻችን በተለምዶ እገሌ እኮ የእገሌ የልብ ጓደኛዉ ነዉ፤ እገሊትም ለእገሊት የልብ ጓደኛዋ ናት ስንልም እንሰማለን። በአንጻሩ ደግሞ አንዳንድ ሰዎች እገሌ ወይም እገሊት እኮ ጓደኛ አይወጣለትም ወይም አይወጣላትም እንዲያዉ ምክንያቱ ምን ይሆን? በማለት አስተያየት እንሰጣለን። ይሁን እንጅ የልብ ጓደኛ ብለን ስንናገር መለኪያችን ከምን አንጻር እንደሆነ መገንዘቡ የበለጠ የመልካም ጓደኛን ትርጉም እንድንረዳ ይረዳናል። ምክንያቱም ብዙ ሰዎች ጓደኛ የሚመርጡበትን መመዘኛ ካለማወቅ የተነሳ እንዲሁ ራሳቸዉ በቀመሩት የጓደኝነት መመዘኛ ቀመር አኳያ ብቻ ስለሚሆን በሆነ አጋጣሚ ካስቀመጡት ቀመር በተቃራኒ ኢምንት በሆነና እዚህ ግባ በማይባል ምክንያት በመካከላቸዉ የግጭት ፀሐይ ሲገባ የሚፈጠረዉ እሳትና ትርምስ አይድረስ ሲያስብል ይታያልና ነዉ። በቃ ነገሩ በሙሉ ይበላሻል፤ አብረዉ ያሳለፏቸዉ የደስታና የሀዘን ጊዜያቶች ከመቅጽበት በዜሮ ተባዝተዉ ባህር ዉስጥ እንደገባ ጨዉ ድራሻቸዉ ይጠፋና አይንህ ለአፈር አይንሽ ለአፈር ሲባባሉ ማየትና መስማት የተለመደ ነዉ። እንዲያዉም በጓደኛሞች መካከል የገባ ጸብ በቀላሉ አይበርድም፤ በቀላሉም አንዱ ለአንዱ ለይቅርታ እጁን አይዘረጋም። ምክንያቱም ሁለቱም ካላቸዉ ቀረቤታ አንጻር አንዱ የአንዱን፤ ሌላዋም የሌላይቱን ምስጢር ልቅምና ጥንቅቅ አድርገዉ ስለሚያዉቁት እሰራለታለሁ፤ እሰራላታለሁ፤ ደግሞ እርሱ፤ ደግሞ እርሷ ቆይ ቀን ያገናኘን ልኩን አሳየዋለሁ፤ ቆይ ልኳን አሳያታለሁ መባባል ሁሌም የሚታይ ገሀዳዊ ትዕይንት ነዉ።
እኛ ክርስቲያኖች ጓደኛ ስንመረጥ ከመንፈሳዊ ህይዎት አንጻር ምን መሆን አለበት? የሚለዉን ጥያቄ አስቀድመን ልንጠይቅ ይገባል። ምክንያቱም ስለ ጓደኛ ስናነሳ ጓደኛ በሰዎች ባህሪ ላይ ሊኖረዉ የሚችለዉን ጥሩም ይሁን መጥፎ፤ አሉታዊና አዎንታዊ ተጽኖዎችን መመልከቱ ከሁሉም በላይ አጽንኦት ልንሰጠዉ የሚገባን ጉዳይ ስለሆነ ነዉ። ከዚህ አንጻር ብዙ ጊዜ ሰዎች የአንድን ሰዉ ባህሪና ማንነት ለመረዳት ሲፈልጉ አብሮት የሚዉለዉን ሰዉ ወይም ዉሎዉ ከማን ጋር እንደሆነ ካወቁ በኋላ በቀላሉ ወደ ራሳቸዉ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አይቸገሩም። ምክንያቱም አንድ አባባል አለ «ጓደኛህን ንገረኝና ማንነትህን እነግርሃለሁ» የሚል። ስለሆነም አብረን የምንዉለዉ ጓደኛችን ዕለት ዕለት ለምናንጸባርቀዉ የባህርይ ለዉጥ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል ማለት ነዉ። ስለዚህ ሁላችንም የተጠራነዉ በእግዚአብሔር ድንቅ አጠራሩ ለመንፈሳዊ ህይዎት፤ ጉዟችንም ወደ መንግስተ ሰማያት ለመድረስ እስከሆነ ድረስ መመሪያችንና አስተማሪያችን መጽሐፍ ቅዱስ ነዉና እርሱን ዋቢ አድርገን የጓደኛን ምንነትና ጥቅምና ጉዳቱን በእግዚአብሔር ቅዱስ ቃል እየፈተሽን የጓደኝነት ህይዎታችን ምን እንደሚመስል እንመለከታለን።
Recommended Posts
አዲሱ ዓመት (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው)
September 09, 2018
ልደተ ክርስቶስ (ገና)
January 07, 2017
ጾመ ፍልሰታ
August 05, 2016