ጾመ ፍልሰታ

ጾመ ፍልሰታ

ጾመ ፍልሰታ

ፍልሰታ የሚለውን ቃል ትርጉም ስናነሣ ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የወጣ /የተገኘ/ ሲሆን በጥሬ ትርጉሙ ከምድር ከመቃብር መለየት፣ ማረግ፤ ወደ ላይ መውጣት የሚለውን ትርጉም ያመለክታል፡፡ በዚህ መሠረት ጾመ ፍልሰታ በአጠቃላይ የእመቤታችን ድንግል ማርያም የሥጋዋን ከመቃብር መለየትና ወደ ገነት ማረጉን የሚያመለክት ሲሆን ቅድስት ቤተክርስቲያን ምዕመናን እንዲጾሙት ከምታዘው ሰባቱ አጽዋማት አንዱና ለዓመቱ ደግሞ የመጨረሻው ጾም ነው፡፡  ይህ ጾመ ፍልሰታ በሌላ አጠራር ጾመ ማርያምም በመባል ይታወቃል፡፡ በዚህ ወቅት በብዛት የሚወሳው /የሚነገረው/ ቃለ እግዚአብሔር በአብዛኛው ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል
ማርያም ጋር የተያያዘ በመሆኑና የእርስዋ የሥጋዋ ፍልሰት መታሰቢያ በመሆኑ ጾመ ማርያም ተባለ፡፡ ነገር ከስሩ ውኃ ከጥሩ እንዲሉ አበው ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ይህንን የእመቤታችንን ጾም ለምን እንደምታከብር ለመዘርዘር እንወዳለን፡፡
እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህች የሰው ልጆች መኖሪያ በሆነችዋ ምድር ከእናቷ ማህፀንና ከአባቷ አብራክ ተከፍላ ከተወለደችበት ጊዜ አንስቶ እስከ መጨረሻዋ የዕረፍት ዘመን በምድር ላይ ስልሳ አራት ዓመታትን ማለትም ከእናት ከአባቷ ቤት ሦስት ዓመት ከሰባት ወር፣ በቤተመቅደስ 12ዓመት፣ በቤተ ዮሴፍ 34ዓመት ከሦስት ወር፣ ከጌታ ዕርገት በኋላ ከወንጌላዊው ዮሐንስ ጋር 14ዓመት ኖራለች፡፡ ከዚህ በኋላ እርሷም የአዳም ዘር ናትና ጥር 21ቀን ዐርፋለች፡፡
አበው”ሞትኪሰ ማርያም ይመስል ከብካበ”ማርያም ሆይ ሞትሽ ሠርግን ይመስላል ” እንዳሉት የእመቤታችን ዕረፍት እንባ መራጨት፣ ጠጉር መንጨት፣ ደረት መድቃት እንዳለበት የሰው ሞት አልነበረም፡፡ ይልቁንም አንደ ሠርግ ቤት መላዕክት በውዳሴ፤ በማህሌት፣ በዝማሬ፣ በምስጋና ወደ ሰማይ ሸኟት፡፡ እንጂ ቅዱስ ያሬድም”ተለዐለት እምድር ወበህየ ነበረት ዘምስለ ወልዳ በየማነ አብ ወመንፈስ ቅዱስ” እመቤታችን ድንግል ማርያም ከምድር ወደ ሰማይ ከፍ ከፍ አለች፡፡ በዚያም ከልጇ ጋር በአብና በመንፈስ ቅዱስ ቀኝ ተቀመጠች በማለትም ዘምሯል፡፡ የእመቤታችን ሥጋዋ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱን አስቀድሞ አባቷ ቅዱስ ዳዊት በትንቢት ሲናገር “ተንሥእ እግዚኦ ውስተ እረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ” አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት በማለት ተንብዮዋል፡፡ መዝ. 131፡8
የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍት ጥር 21 ሲሆን እረፍቷና ዕርገቷ ብዙ መንፈሳዊ ተአምራትና አስደናቂ ምስጢር የተገለጠበት በመሆኑ ሞት በጥር በነሐሴ መቃብር የተባለበትም ምክንያት ከዚህ በመነሣት ነው፡፡
የእመቤታችን ዕረፍት በሆነበት እለት አይሁድ በአስከሬኗ ጥፋት ለማድረስ ብዙ ጥረዋል፡፡ እነ ታውፋንያም እጁን በመቆረጥ ተአምር ተደርጎበታል፡፡ በዚህ ጊዜ ብዙ ንውጽውጽታ ስለነበር ሐዋርያትም በሀዘን ከጌቴሴማኒ ተመለሱ፡፡ በዚህ ሀዘንም እያሉ ሐዋርያው ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ሲመጣ እመቤታችንን መላእክት ሲያሳርጓት አየ፡፡ ሰገደላት፣ አመሰገናትም እርሷም ባርካው ተለያዩ፡፡ ለሐዋርያው ቶማስም የእመቤታችንን መቀበር ደቀ መዛሙርት አስረዱት፡፡ ቶማስም ሥጋዋን እስከማይ አላምንም አላቸው፡፡ ሥጋዋን ያሣዩት ዘንድ ወደ መቃብርዋ በአደረሱት ጊዜ በመቃብር ውስጥ ሥጋዋን አላገኙም ደንግጠውም አደነቁ ያን ጊዜ ከመላእክት ጋር ወደ ሰማይ ስታርግ እመቤታችንን እንዳገኛት ቶማስ ነገራቸው፡፡ በዚህም ሥጋዋ ሲያርግ ባለማየታቸው አንድ ቀን እንደሚያሳያቸው ጌታችን ተገልጦ ቃል ገባላቸው፡፡ ከዚህ በኋላ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ከሚያስተምርበት ሀገረ እስያ ወደ ሰማይ ተነጥቆ የእመቤታችን ሥጋ ያለበትን ስፍራ አየ፡፡ ሐዋርያትም ይህን በሰሙ ጊዜ ዮሐንስ እንዳየና እንደሰማ ባለማየታቸውና ባለመስማታቸው እጅግ አዘኑ፡፡ ሐዋርያትም ዓመት ሙሉ ቆይተው ነሐሴ በባተ በመጀመሪያው ቀን በጾም በጸሎት ሱባዔ ያዙ፡፡ ነሐሴ14ቀን ሁለት ሱባዔ ሲጨርሱ ሥጋዋን አምጥቶ  ሰጣቸው በጥር ወር የእረፍት ጊዜ ተወስኖ በነበረው ቦታ በጌቴሴማኒ ቀበሯት፡፡ ነሐሴ 16ቀን በሆነ ጊዜ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉንም ሐዋርያት ወደ ሰማይ አወጣቸው፡፡ በታላቅ ክብር በተወደደ ልጅዋ ቀኝ ተቀምጣ ከሥጋዋ ተዋሕዳ ተነሥታ እመቤታችንን አዩዋት፡፡ እጆችዋንም ዘርግታ ሐዋርያትንም ባረከቻቸው በእልልታ በደስታ ወደ ሰማይ ዐረገች፡፡ ሐዋርያትም በልባቸው ደስ አላቸው፡፡ እንግዲህ ከላይ ለማስነበብ እንደሞከርነው ጾመ ፍልሰታ እንደወንዝ ፈሳሽ እንደ እንግዳ ደራሽ የሆነ ታሪክ ሳይሆን ልብን የሚነካ መንፈሳዊ ታሪክ ነው፡፡
ለዚህም ነው ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነስ አንተና የመቅደስህ ታቦት” ያለው፡፡ አንተ ያለው ጌታችንን ሲሆን የመቅደስህ ታቦት ያለው ጌታ ለዘለዓለም አድሮባት የኖረባትን እናቱ ድንግል ማርያምን ነው፡፡ ጌታ በገዛ ፈቃዱ ሞትን ድል አድርጎ በሦስተኛው ቀን እንደተነሣ እርሷም በልጅዋ ቸርነት ከሦስት ቀን በኋላ ከሞት ተነሳች፡፡
ስለዚህም ነው ምእመናን ነሐሴ አንድ ቀን የምትገባዋን ጾመ ማርያም ሱባዔ ለመያዝ ሕፃናቱ ተማሪው የክረምት ዕረፍት በመሆኑ፣ ሠራተኛው የዓመት ፈቃዱን ወስዶ ሌሊት በሰዓታት፣ ቀን በትርጓሜና በቅዳሴ የሚያሳልፈው፡፡ እግዚአብሔር አብርሃምን “የሚባርኩህን እባርካለሁ፣ የሚረግሙህን እረግማለሁ” እንዳለው፡፡ ዘፍ.12፡3የአብርሃም ዘር የሆነች ድንግል ማርያምን የሚያመሰግን ትውልድ ይባረካል፡፡ ለዚህም ነው እመቤታችንም “ትውልድ ሁሉ ብጽእት ይሉኛል” በማለት የተናገረችው፡፡ ይህ የሱባዔ ወቅትም እመቤታችንን እንደ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ደስ ይበልሽ ብለን አመስግነን፣ እንደ ቅዱሳን አባቶች ሰአሊ ለነ ቅድስት በማለት ለምነን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ የምናገኝበት ልዩ ወቅት ነው፡፡
በብዙዎቻችን ዘንድ የዚህ ሱባዔ ወቅት የማይረሳ ልዩ ትዝታም አለው፡፡ ስለሆነም በተለይ በአሁኑ ጊዜ በቤተክርስቲያን የሚታየውን ፈተና ለመቋቋም በርትተን “ጸልዮ በእንተ ሰላመ ቤተክርስቲያን” እንዲል ስለቤተክርስቲያን ሰላም መፀለይ ይገባናል፡፡ ክፉ የተባሉ ቀናት አይቻልም የሚባሉ ችግሮች በጸሎት ኃይል እንደሚሸነፉ የመጽሐፍ ቅዱሳን ምስክርነት ማየት ይበቃል፡፡ ሐዋ. 12፡5፡፡
የጾመ ፍልሰታ ልዩ ገጽታ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሰባት ያህል አጽዋማትን በአዋጅ ታጾማለች፡፡ ነገር ግን የጾመ ፍልሰታ ልዩ ገጽታን ለማየት ያህል፤
1. ከዚህ በፊት በተለየ መልኩ ሙሉ ጊዜ /ቀንም ሆነ ሌሊት/ ያልተቋረጠ የቤተክርስቲያን አገልግሎት ማለትም የአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የሰዓታት ድርሰት፣ የቅዱስ ያሬድ ዜማ፣ የቅዱስ ኤፍሬም የውዳሴ ማርያም ትርጓሜ፣ የአባ ሕርያቆስ ቅዳሴ ማርያም በስፋትና በጥልቀት የሚሰማበት መሆኑ ከፍተኛ የመንፈስ እርካታን ይሰጣል፡፡
2. በትምህርት ጊዜ ሲባዝኑ የነበሩ ሕጻናትና ተማሪዎች፣ ወጣት፣ አረጋውያኑ ለመቁረብ ነጠላ ለብሰው በጊዜ ቤተክርስቲያን ገብተው ሲያስቀድሱ ማየት የኅብረት የተሰጥኦ ዜማቸውን መስማት አንዱ ልዩ ገጽታ ነው፤
3. ጊዜው ሁለት ሱባዔ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በፍቅር የምትጾም መሆኗም ከሌሎቹ የአጽዋማት ጊዜ ልዩ የጾመ ማርያም ገጽታ ነው፡፡
እንግዲህ ምዕመናን በሩቅም በቅርብም ከሀገር ውጭም በውስጥም ያለን ስለአንድነታችን፣ ስለሰላማችን ስለ ሀገራችን እየጸለይን ልዩ መንፈሳዊ በረከት ከእመቤታችን እንድናገኝ ልንተጋ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር
በመምህር ንዋይ ካሳሁን የቀረበ

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *