ዳግም ምጽአት

ዳግም ምጽአት

ዳግም ምጽአት ‹‹ደገመ›› እና ‹‹መጽአ›› ከሚሉ ሁለት የግዕዝ ግሦች የተዋቀረ ሐረግ ነው፡፡ የጌታችንንና የአምላካችንን ለሁለተኛ ጊዜ ወደዚህች ዓለም መምጣት ያመለክታል፡፡ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዳግምነቱ ለልደቱ ነው፡፡ ማለትም ልደቱን ‹‹ቀዳማዊ ምጽአት›› ካልን ዘንድ ለፍርድ መምጣቱን ‹‹ዳግም ምጽአት›› እንላለን፡፡

‹‹ዳግም›› የሚለውን ቃል አንድ ነገር ያለ ምንም ለውጥ ወይም ልዩነት ሲደገም የምንጠቀምበት ከሆነ ‹‹የተካከለ ዳግም›› እንለዋለን፡፡ ያ ነገር መሠረታዊ ጭብጡን ሳይለቅ ነገር ግን በበርካታ ለውጦች ታጅቦ ከተደገመ ወይም ከቀደመው ጋር ሲነጻጸር ተደገመ የሚያሰኝ ምሥጢራዊ አካሄድ ካለው ‹‹ያልተካከለ ዳግም›› ይባላል፡፡ ፍጹም የሆነ መመሳሰል የሌለው መደገም እንደማለት ነው፡፡ ዳግም ምጽአት፣ ዳግም ልደት፣ ዳግም ትንሣኤ ወዘተ ‹‹ያልተካከለ ዳግም›› ላልነው እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ቀደም ሲል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚች ዓለም ሰው በመሆን መጥቷል፡፡ ለሁለተኛ ጊዜ ደግሞ ለፍርድ እንደሚመጣ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ የቀድሞ አመጣጡንና ወደፊት ለፍርድ መመጣቱን ስናስተያያቸው በዓላማቸውም ሆነ በይዘታቸው በጣም ከፍተኛ ልዩነት አላቸው፡፡ የሚመሳሰሉት ወደዚህ ዓለም መምጣት በሚለው ጽንሰ ሐሳብ ብቻ ነው፡፡ ሰው ለመሆንም ሆነ ለፍርድ ቢመጣ ሁለቱም ጊዜ መምጣት ነውና፡፡

‹‹ምጽአት›› መጣ የሚል ፍቺ ካለውና ‹‹መጽአ›› ከሚለው ግሥ የተገኘ ሲሆን ትርጉሙ ‹‹መምጣት፤ አመጣጥ›› የሚል ነው፡፡ ‹‹መምጣት›› የሚለውን ቃል እንኳን ለእግዚአብሔር ይቅርና ለሰው ስንጠቀምበትም የተለያየ አገባብና ትርጉም የሚሰጥ ነው፡፡ ለምሳሌ ‹‹እገሌ ሄደ ወይም መጣ›› ብንል የተጠቀሰው ሰው በአካል መሄድና መምጣቱን ያሳያል፡፡ ይህ አንዱ ዓይነት አገባብ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ሰው በሐሳብ፣ በፈቃድ፣ በልብና በመንፈስ ሄደ፤ መጣ ሊባል ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የቃሉ አገባብ በአካል ወዲህና ወዲያ ማለትን አያመለክትም፡፡

ስለ እግዚአብሔር ወልድ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ዓለም መምጣት ስንናገር ከላይ ስለተጠቀሰው ዓይነት የቃሉ ፍቺና አገባብ በትኩረት ማሰብና ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ክብር ይግባውና ፈጣሪን ሳናውቅ ልንሰድበው እንችላለን፡፡ እንዴት ቢባል ፈጣሪን እንደፍጡር ወዲህና ወዲያ ይላል ማለት መስደብ ነውና፡፡ ታዲያ ኢየሱስ ክርስቶስ በሰውነት መጥቷል፤ ዳግመኛም ለፍርድ ይመጣል ሲባል እንዴት ነው?

ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔር በሁሉም ቦታ መልቶ የሚገኝ ምሉዕ በኩለሄ መሆኑን ማወቅና ማመን ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ በቦታ ተወስነው እንደሚሩ እንደፍጡራን ሄደ፤ መጣ እየተባለ ለባሕርይው አይነገርም፡፡ ስለእግዚአብሔር መምጣት ስንናገር ሦስት ዓይነት መንገዶችን ለይተን ማወቅ አለብን፡፡ እነርሱም በግብር መምጣት፣ በዘፈቀደ መገለጥ (መምጣት)፣ በኩነት መምጣት የሚሉት ናቸው፡፡

1ኛ. በግብር መምጣት፡-ማለት በሥራ መምጣት ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔር ሥራ ሲሠራ መጣ ይባላል፡፡ በቦታ መልቶ የሚገኝ ነፋስ ሲነፍስና ሣር ቅጠሉን ሲያነዋውጽ ‹‹ነፋስ መጣ›› እንደሚባል ሁሉ እግዚአብሔርም አምላካዊ ሥራውን በመሥራት ሲገለጥ ‹‹መጣ›› ይባላል፡፡ በግብር መምጣት በሌላ መንገድ የ‹‹ረድኤት አመጣጥ›› ይባላል፡፡

‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል›› የሚለው ዐረፍተ ነገር እግዚአብሔር ሥራ ሲሠራ መጣ እንደሚባል ማስረጃ ነው፡፡ ቀድሞም ቢሆን መንፈስ ቅዱስ ድንግል ማርያምን ርቋት አያውቅም፡፡ ነገር ግን በታላቅ ሥራ በእርሷ ሲገለጥ ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል›› ተብሎ እንደ አዲስ ተነገረ፡፡ ይህን የመሰለ በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ፡- ‹‹በኤልሳቤጥም መንፈስ ቅዱስ ሞላባት››… ወዘተ፡፡ (ሉቃ1.35፤ 1.42)

እግዚአብሔር እንደ ሦስትነቱ በአብርሃም ቤት ተገኝቶ ለአብርሃም ‹‹የዛሬ ዓመት እንደዛሬው ጊዜ ወደ አንተ በእውነት እመለሳለሁ፤ ሚስትህ ሣራም ልጅን ታገኛለች›› ብሎታል፡፡ ነገር ግን በተስፋው መሠረት ፈጣሪ ተመልሶ ወደ አብርሃም ሲመጣ አናነብም፡፡ ከዚህ ይልቅ የምናነበው ‹‹እግዚአብሔርም እንደተናገረው ሣራን አሰበ፤ እግዚአብሔርም እንደተናገረው ለሣራ አደረገላት፡፡ ሣራም ጸነሰች፡፡›› የሚል ነው፡፡ (ዘፍ18.10፤ 21.1) ምእመናን! እግዚአብሔር ለሣራ የሚያደርግላትን ለመግለጽ ‹‹ወደ ቤትህ እመለሳለሁ›› ማለቱን አያችሁን? ለሣራ ማድረጉ ወደ አብርሃም ቤት ተመልሶ እንደ መምጣት ይቆጠራልና፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የእግዚአብሔር መምጣት የ‹‹ግብር ምጽአት›› ወይም የእግዚአብሔር በሥራ መምጣት ይባላል፡፡

2ኛ. በዘፈቀደ መምጣት፡- እግዚአብሔር በወደደው ጊዜ በወደደው ኅብርና አምሳል ለሰዎች ራሱን ይገለጣል፡፡ ይህን ሲያደርግ ‹‹መጣ›› ይባላል፡፡ አመጣጡም የ‹‹በዘፈቀደ አመጣጥ›› ይባላል፡፡ እንደ ወደደው መገለጥና መምጣት ማለት ነው፡፡

የሰው ልጅ ሊያየው ሊሰማውና በአጠቃላይ ሊረደው በሚችለው መጠንና አምሳል ፈጣሪ ራሱን ይገልጣል፡፡ ይህም በሥጋዊና በደማዊ ወይም በሌላ ፍጡር አምሳል ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡- መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ተገልጧል፡፡ እግዚአብሔር በእሳት፣ በብሩኅ ደመና፣ በጨለማ፣ በጭጋግ፣ በጢስና በብርሃን አምሳል ሊገለጥ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር መጣ ይባላል፡፡ (ማቴ3.16፤ ዘጸ19.9) ይሁን እንጂ በእነዚህ ነገሮች አምሳል ስለመጣ የተጠቀሱት ነገሮች እግዚአብሔር ናቸው ወይም እርሱ እነርሱን ሆኗል ማለት አይደለም፡፡ ለጊዜው በእነርሱ አምሳል ተገለጠ እንጂ፡፡

3ኛ. የኩነት አመጣጥ፡- ሐዋርያው ‹‹ክርስቶስ በሥጋ እንደመጣ›› እንዳለው በመምሰል ብቻ ሳይሆን በመሆን መምጣት አለ፡፡ የኩነት አመጣጥ በመሆን መምጣት ማለት ሲሆን ከዘፈቀደ አመጣጥ የሚለየውም በዚህ ነው፡፡ እግዚአበሔር ለጊዜው በሰው አምሳል ተገለጠ ማለትና ሰው ሆነ ማለት በጣም የተራራቁ ነገሮች ናቸው፡፡ ቀድሞ በሰው አምሳል ለአበው በዘፈቀደ ይገለጥ የነበረ እግዚአብሔር በማዕከለ ዘመን ከቅድስት ድንግል ማርያም ሰው ሆነ፡፡ ማለትም በኩነተ ሥጋ ወደዚህች ዓለም መጣ፡፡ ስለዚህ ለኩነት አመጣጥ የሚቀርበው ዋና ምሳሌ የክርስቶስ ልደት ነው፡፡ ልደቱ ምጽአት ሲሆን ነገር ግን የኩነት ምጽአት ነው፡፡

የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ዓይነት ምጽአቶች የሚለይበት ነገር አለ፡፡ ከግብር ወይም ከረድኤት አመጣጥ የሚለየው በረቂቅ ሳይሆን በግልጥ በመምጣቱ ነው፡፡ ከድንግል ማርያም በነሣው ሥጋ፣ በክበበ ትሥብዕት፣ በግርማ መለኮት ተገልጦ ዓለም ሁሉ ስለሚመለከተው በዘፈቀደ ከመገለጥም ይለያል፡፡ ክርስቶስ ሰው የሆነ አምላክ በመሆኑ ዳግም ምጽአት ለኩነት ከመጣበት አመጣጥ ማለትም ከልደቱም የተለየ አመጣጥ ነው፡፡ የሚመጣው ለፍርድ እንጂ ሰው ለመሆን አይደለምና፡፡

ቃል ሥጋ የሆነው በተዐቅቦ ነው፡፡ ይህም ሥጋ ሥጋነቱን እንደጠበቀ ግዙፍ የነበረው ወደ ረቂቅነት ሳይለወጥ፤ ውሱን የነበረው ወደ ምሉዕነት ሳይለወጥ ማለት ነው፡፡ እንደዚሁም ቃልም ረቂቅነቱንና ምሉዕነቱን ሳይተው ሥጋና ቃል ተዋሐዱ ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቶስ ስንል ሥግው ቃል ማለታችን ነው፡፡ ክርስቶስ ይመጣል ስንልም ሥጋን የተዋሐደው ቃል ለፍርድ ይመጣል እያልን ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር ቃል ግዙፍና ውሱን ሥጋን ባለበት ሁኔታ ሳይለውጠው ተዋሕዷል ብለን እስካመንን ድረስ ‹‹መጣ፣ ሄደ(ዐረገ)፣ ይመጣል›› ማለት በተዋሕዶተ ቃል ለሚያምኑ ሁሉ የሚስማማ ንግግር ነው፡፡

ለፍርድ የሚመጣው ከሦስቱ አካል አንዱ ወልድ ነው፡፡ የሚመጣውም ለፍርድ ስለሆነ እጅግ በጣም በሚስፈራ ግርማ ነው፡፡ እንደ ሐኪም መምጣትና እንደ ዳኛ መምጣት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ አምላካችን ክርስቶስ አስቀድሞ የመጣው እንደ ሐኪም ነበር፡፡ ስለሆነም ሰዎች ብዙ የማይገባ ነገር ሲናገሩበትና ሲያደርጉበት ባለመድኃኒት (ሐኪም) የበሽተኛውን ቁጣና ስድብ እንደሚታገሥ እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታግሦ አሳልፏል፡፡ ለፍርድ ሲመጣ ግን እንደዚያ ዓይነት ትሕትናና ትዕግሥት መጠበቅ የለብንም፡፡ የዳኛ ሥራ እንደ ሕጉ መዳኘት ነው እንጂ ማባበል፣ መምከርና ማስተማር አይደለምና፡፡ ስለዚህ ሀብታሙ፣ ደሀው፣ ወንዱ፣ ሴቷ፣ ሕፃኑ ሽማግሌው፣ ጳጳሱ ምእመኑ ሁሉ በፊቱ ይቆማል፡፡ የሁሉም ሥራ ይገለጣል፡፡ ሁሉም ስለ ክፉ ሥራው በፊቱ ዋይ ይላል! የማይጠቅም ዋይታ ነው፡፡

የፍርድ ቤት ቀጠሮ ያለበት ሰው ምን ማድረግ እንዳለበት አስቅድሞ ያስባል እንጂ ችላ ብሎ አይቀመጥም፡፡ እኛም እንዲሁ እንድናስብበትና ተዘጋጅተን እንድንጠብቀው ዕለተ ፍትሕ፣ ዕለተ ኩነኔ (ዳግም ምጽአት) እንዳለ አምላካችን አስቀድሞ ነግሮናል፡፡ ቅዱስ ወንጌል ‹‹እንዳትሰናከሉ ይህን አስቀድሜ ነገርኳችሁ››፤ ‹‹ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ፡፡›› ይለናል፡፡ ቀኑ መቅረቡን የምናውቅበት ምልክቶችንም ዘርዝሮልናል፡፡ አብዛኞቹ ምልክቶች ተፈጽመዋል፡፡ ሌሎቹም እየተፈጸሙ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹም ጥቂቶች ምልክቶች ከደጅ መድረሳቸው የኮቴአቸው ድምጽ ይጠቁማል፡፡ (ማቴ24.1-51) የምጽአት ዋዜማ ምልክቶችን ዝርዝርና ምሥጢር በሌላ ጊዜ እንመለስበታለን፡፡

የክርስቶስ መምጣት ለሙታን ትንሣኤ እንደ ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ሙታን የሚነሡት እርሱ ሲመጣ ነውና፡፡ ስለዚህ ዳግም ምጽአት ከአምስቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዋነኛ በሆነው በምሥጢረ ትንሣኤ ሙታን ትምህርት ውስጥ ሰፊ ቦታ ተሰጥቶት ይብራራል፡፡ ይቆየን!

በዲያቆን ኅብረት የሺጥላ

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *