ዕለተ ዓርብ(ስቅለት)

ዕለተ ዓርብ(ስቅለት)

“አንዱ ስለሁሉ ሞተ” (2ቆሮ 5÷14)

የስሞነ ሕማማት ዕለተ ዓርብ በቤተክርስቲያናችን ልዩ ቀን ነው፡፡ ይህ ቀን ልዩ ነው፣ የማይታመመው ታሞ የዋለበት፣ የወደቁትን ከተረሱበት ከትቢያ የሚያነሳ እሱ ሲወድቅ ሲነሣ የዋለበት፣ ሕመምተኞችን የሚፈውስ እሱ ሲያቃስት የዋለበት፣ ከሲኦል የዲያብሎስ ግርፋት ነፃ የሚያወጣ ሲገረፍ የዋለበት ወልደ እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ድኅነት በመስዋዕትነት ሙሽራ የሆነበት የደስታ ቀን የዓመፃ መዝገባችን መገልበጡ እርግጥ የሆነበት ፣ አሳዳጃችን አሳሪያችን ዲያብሎስ ከነወጥመዱ ድል የተነሳበት ቀን ነውና፣ ከዚህም የተነሳ በቤተክርስቲያን የተለያየ ምስጢራዊ ስያሜዎች ተሰጥቶታል፡፡

የስቅለት ዓርብ ይባላል
የዓለም ሁሉ መድኀኒት የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመልዕልተ መስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ድኅነት መስዋዕት ሆኖ የዋለበት ዕለት በመሆኑ የስቅለት ዓርብ ተብሏል (ማቴ 27፡35)

መልካሙ ዓርብ (GOOD FRIDAY) ይባላል
ይህም የሚያስገነዝበን ከስቅለተ ክርስቶስ በፊት ማንም ሰው ስያጠፋ በመስቀል ተሰቅሎ እንዲሞት ይደረግ ነበር፡፡ በተለይ በሮማውያንና በፈሪሳውያን ሕግ መስቀል የወንጀለኞች መቅጫ ነበረ፣ በዚህ ዕለት ግን ታሪክን የሚቀይረው፣ ነገርን የሚገለብጠው አምላክ የወንጀለኞች መቅጫ ምልክት የነበረውን መስቀል በደሙ ቀድሶ የምህረት ምልክት፣ የሕይወት አርማ፣ የዲያብሎስ ድል መንሻ ፣ የቤተክርስቲያን ጌጥ፣ የገዳማት ዘውድ፣ ስለአደረገውና በዕለተ ዓርብም በሞቱ ሕይወትን ስለአገኘን መልካሙ ዓርብ ተብሏል፡፡

ነፍሳት ከሲኦል የወጡ መቼ ነው?
ነፍሳት ከሲኦል የወጡ ዓርብ በሠርክ ነው፡፡ ሐዋርያው ጴጥሮስ “ነጻነት አወጃላቸው” ይላል፡፡ ጌታ በአካለ ነፍስ ወደ ሲኦል ወርዶ “ሰላም ለኵልክሙ” “ሰላም ለእናንተ ይሁን” እንዴት ሰነበታችሁ? አስታረቋችሁ ሲላቸው ነው፡፡ አዳም የተቀጠረች የድኅነት ዕለት ዛሬ ናት ተንሥኡ ለጸሎት ሲል ነፍሳትም ምስለ መንፈስከ አሉ፡፡ጌታም “በጽልመት ውስጥ ያላችሁ ውጡ፣ በሲኦል ያላችሁ ተገለጡ ብርሃንም አዩ” ብሎ እልፍ ፀሐይ ቢገባበት የማይለቅ የሲኦልንም ጨለማ ብርሃነ መለኮቱን ነዛበት ያኔ ጨለማው ለቀቀ የዚያን ጊዜ ወጐዩ ዓቀበተ ሥጋ መናፍስት /አጋንንት/ በዚህ ጊዜ ነፍሳትን የተቆራኙ አጋንንት ሸሹ፣ እለ ውስተ ሲኦል ጻኡ፤ ወእለ ውስተ ጽልመት ተከሠቱ ብሎ ባሕረ እሳትን ከፍሎ ወደ ገነት አገባቸው፡፡

በዕለተ ዓርብ ስንት ታምራት ታይቷል?

ጌታ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ቅድስት ነፍሱን ከቅድስት ስጋው በራሱፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ የታዩ ተአምራት የሚከተሉት ናቸው፤
በሰማይ፤ /ማቴ 24፦29 እና 27፦45/
1. ፀሐይ ጨለመች
2. ጨረቃ ደም ሆነች
3. ከዋክብት ረገፉ

በምድር፤/ማቴ 27፦51_53/
4. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይእስከ ታች ተቀደደ
5. ምድር ተናወጠች
6. መቃብሮች ተከፈቱ
7. ሙታን ተነሱ

ለምን 400 ጊዜ እግዚኦ ይባላል?
በዚሁ ዕለት በአራት መዓዘን እየዞርን 400 ጊዜ ምሕላ እናደርጋለን፣ ምሕላ የምናደርገውም አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን የአዳም ልጆች በሲኦል ሆነው አቤቱ ይቅር በለን ብለው የለመኑትን ለማስታወስ ነው ከምሕላው በኋላ በወይራ እየተጠበጠቡ የንስሐ ስግደት እንደየ አቅሙ ይሰጣል፡፡ ከምን የተነሣ ነው ቢባል የክርስቶስን መከራ እንቀበላለን፡፡ በክርስቶስ ክርስቲያን ተብለናልና፡፡ የኛን መከራ ተቀብሎ እንዳዳነን እሱ የተቀበለውን መከራ እንቀበላለን፣ እንገረፋለን፣ አላውያን ነግሥታት፣ አላውያን መኳንንት፣ ሃይማኖታችሁን ካዱ ቢሉን ቢገርፉን እንገረፋለን በሰይፍ ቢመቱን፣ ቢሰቅሉን፣ መከራውን በጸጋ እንቀበላለን ለማለት ነው፡፡ እሱ የተቀበለው መከራ ተቀበሉ ተብሎ ታዟልና፡፡

በዕለተ ዓርብ ንሴበሖ ለእግዚአብሔር የሚባለው ለምንድነው?
በስቅለት፣ ዓርብ ማታ ከእግዚኦታ /ምሕላ/ በኋላ ንሴብሖ ይባላል፡፡ ምክንያቱም እስራኤል በምድረ ግብጽ 215 ዘመን በባርነት ቀንበር ሲገዙ ከነበሩ በኋላ በሙሴ መሪነት የኤርትራን ባሕር ስላሻገራቸው “ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ስቡሐ ዘተሰብሐ” እያሉ አመስግነውታል፡፡ እኛ ደግሞ ከአጋንንት አገዛዝ ነጻ አውጥቶ ባሕረ እሳትን ከፍሎ ወደ ገነት ስለአገባን “ንሴብሖ” እያልን እናመሰግነዋለን፡፡ንሴብሖ ለእግዚአብሔር ከተባለ በኋላ እግዚአብሔር ይፍታህ ይባላል፡፡ እግዚአብሔር ይፍታህ የሚባልበት ምክንያትም ካሣ ከተፈጸመ ወዲያ፣ ልጅነት የተመለሰ፣ ነጻነት የተገኘ ነፍሳት ከሲኦል የወጡ ስለሆነ ነው፡፡

በዓመት አንድ ጊዜ የምናገኘው ይህ ዕለት ቀራንዮን የምናስብበት ነገረ መስቀሉን የምናስተውልበት እንጂ ስለምድራዊ ኑሮአችን ስንባክን ኃጢዓት ስንሰራ የምንውልበት ሊሆን አይገባም፡፡

ለብርሃነ ትንሣኤው አምላካችን በሰላም ያድርሰን፡፡

share

Comments

  1. Yirsaw demissie : April 30, 2021 at 3:17 pm

    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን መልካም ቀን ይሁን እንደለተ ዓርብ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *