ነትገ ማይ አይኅ

ነትገ ማይ አይኅ

”ወበጽርሑሰ ኵሉ ይብል ስብሐት

እግዚአብሔር ያስተጋብኦ ለማየ አይኅ

ሁሉም በመቅደሱ፦ ምስጋና ይላል

እግዚአብሔር የጥፋት ውሃን ሰብስቧልና”

መዝ ፳፰፥፱

ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት በዚህ መዝሙሩ ላይ፦ ምዕመናን ለአምላካቸው የአምልኮ መገለጫ የሆኑትን ምስጋናና ስግደት ሊያደርጉ እንደሚገባቸው በመጀመሪያዎቹ ስንኞች ላይ አስፍሯል፦ ”በቅድስናው ስፍራ ለእግዚአብሔር ስገዱ” – እንዲል። በሚቀጥሉት ስንኞች ደግሞ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ አምላክ እንደሆነ ሰብኳል። ”የክብር አምላክ አንጐደጐደ” በማለት በብዙ ምሳሌ አስተምሯል፤ የሊባኖስ ዝግባን፣ ውሃን፣ እሳትን፣ የቃዴስን ምድረ በዳ እየጠቀሰ ተናግሯል። ይህ ሁሉ የእስራኤላውያን የአምልኮ ታሪክና የእግዚአብሔርን ተአምራት የሚያስታውስ ነው፤ ይህውም በምድረ በዳ እና በመሳፍንት ዘመን ሁሉ የነበረው ነው፦ ውሃውን ያለ ግድብ ሲያቆም፣ ከጭንጫ ሲያፈልቅ፣ ምድረ በዳውን በደመና ሲጋርድ፣ እሳትን ከሰማይ ሲያወርድ፣ ታላላቅ ነገስታትን ድል ሲያደርግ ወዘተ። በመጨረሻዎቹ ስንኞች ደግሞ፦ የጥፋት ውሃን መልሷልና በመቅደስ ያመሰግኑታል እርሱም ንጉሥ ነው ኃይልንም ለህዝቡ ይሰጣል በማለት ያለፈውንም የሚመጣውንም ተናግሯል።

፩- የጥፋት ውሃን ሰብስቧል፦ ሰው በመበደሉ ምክንያት እግዚአብሔርን ስላሳዘነ ምድር በውስጧም ያሉ ፍጡራን ሁሉ በውሃ ሙላት ቀጣ። እግዚአብሔርም ኖህንና ቤተሰቡን ከመርከብ ሊያወጣቸው ወዶ የጥፋትን ውሃ መለሰ ውሃውም ወደቦታው ተመለሰ። ንጉስ ወነቢይ ዳዊት የተናገረው ይህንን ነው። ለእግዚአብሔር ለጌትነቱ ለኃያልነቱ ምስጋና አንክሮ ይገባል።

አዳምና ሔዋን አምላካቸውን በድለው ከሚኖሩባት ገነት ተባረው ዳግመኛም እንዳይገቡባት ጠባቂ ተደርጎባቸው በዚህች ምድር እንዲኖሩ ተፈረደባቸው። የሰውን ዘር ወደቀደመ ቦታው ይመልሰው ዘንድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በደሙ ዋጀን። የጥፋት ውሃ በኖህ ጊዜ እንደተሰበሰበ ጊዜው ሲደርስ ጌታ የሰውን ኃጢአት ይቅር ይል ዘንድ ተገለጸ።

መጽሐፍ፦ ”እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን። እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፤ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ አዘነበለ፤ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ።” ኢሳ፶፥፭ ይላል። በሌላም ስፍራ፦”መጽሐፍ እንደሚል ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፥ ተቀበረም፥ መጽሐፍም እንደሚል በሦስተኛው ቀን ተነስቷል።” ፩ቆሮ፩፭፥፫

አዳም ጠፍቶ እንዳይቀር የወደደ ጌታ ፍጹም ይቅርታን አድርጐ ወደቀደመ ቦታው መለሰው አከበረው ይህን በቀኙ ተሰቅሎ ለነበረው ለጥጦስ፦ ”እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።” ሉቃ ፳፫፥፵፫ በማለት ገልጦታል።

፪- ለሕዝቡም ኃይልን ይሰጣል፦ ”በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፎ፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳያቸው።” ቆላ፪፥፩፬ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ እርኩሳን መናፍስትን ድል ሲያደርግ፣ ለሰዎች ደግሞ ነፃነትንና ስልጣንን ሰጥቶአቸዋል፦ ”እነሆ፥ እባቡንና ጊንጡን ትረግጡ ዘንድ፥ በጠላትም ኃይል ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቻችኋለሁ፥ የሚጐዳችሁም ምንም የለም።”ሉቃ፲፥፩፱

ለሰዎች ልጆች የሰጠው ይህ ኃይል ፍፁም የሆነው በበዓለ ጰራቅሊጦስ ዕለት ነው። እንዲህ ይላልና፦ ”እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ።” ሉቃ፳፬፥፵፱ ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊትም፦ ”ወደ ላይ ዓረግህ፥ ምርኮን ማረክህ፥ ስጦታንም ለሰዎች ሰጠህ፣” መዝ፷፯፥፩፰ ብሏል።

፫- በመቅደሱ ምስጋና ይገባዋል፦ ልዑለ ባህሪይ እግዚአብሔር ዓለምን እንዲሁ ስለወደደ ብቻ አድኖናል።  ”በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ፫፥፩፮ ለዚህ አንክሮ ምስጋና እንጂ ምን ሊደረግ ይችላል!? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፦ ”ስለማይነገር ስጦታው እግዚአብሔር ይመስገን።” ነው ያለው።

እንግዲህ የኃጢአታችንን ብዛት በደሙ ፈሳሽነት ላስወገደልንና ፍፁም ጸጋውን ላደለን ለእርሱ ምስጋና ልናቀርብና ልናገለግለው ይገባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

  በዲን. ብርሃኑ ታደሰ

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *