ሰማዕትነት

ሰማዕትነት

ሰማዕት ‹‹ሰምዐ›› ከሚል የግእዝ ቃል የተወሰደ ሲሆን፤ ትርጉሙም ያየነውን፣ የሰማነውን መመስክር መቻል እንደሆነ የኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ስዋስወ ወግስ መዝገበ ቃላት ገጽ 671 ይነግረናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ‹‹እኔ ለእውነት ለመመስከር መጥቻለሁ›› በማለት እውነትን እንድንመሰክር አብነት ሆኖናል /ዮሐ.18፥37/፡፡

ሰማዕትነት በሃይማኖታዊ ትርጉሙ ስንመለከተው ስለ እግዚአብሔር፣ ስለቅድስት ቤተክርስቲያን፣ ስለ ሃይማኖታቸው በእውነት በመመስከራቸው ጀርባቸውን ለግርፋት፣ ሰውነታቸውን ለእሳት፣ እግራቸውን ለሰንሰለት፣ አንገታቸውን ለስለት አሳልፈው ለሰጡ፤ በድንጊያ ተወግረው በመንኮራኩር ተፈጭተው በጦር ተወግተው አልያም በግዞትና በስደት በዱር በገደል ተንከራተው ለዐረፉ ቅዱሳን አባቶችና ቅዱሳት እናቶች የሚሰጥና ተጋድሎአቸውን ጠቅለል አድርጎ የሚገልጽ ቃል ነው፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊው እመቤታችንን ባመሰገነበት ድርሳኑ “ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ፤ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ፤ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ” በማለት የሰማዕታት ተጋድሎአቸው መራራ እንደሆነ ገልጿል፡፡ (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ)

ጌታችን ‹‹በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፡፡ በሰው ፊት የሚክደኝን ሁሉ ደግሞ በሰማያት ባለው አባቴ ፊት እክደዋለሁ›› ሲል ስለ ሃይማኖታችን የምንመሰክረው ከሰማዕትነት ጋር ያለውን ቁርኝት ነግሮናል፡፡ /ማቴ.10፥32-33/፡፡ ከዚህ አንጻር ያለ ክርስትና ሰማዕትነት ያለ ሰማዕትነት ክርስትና የለም ማለት ነው፡፡

ሰማዕትነት መመስከር ከሆነ እንዴት ነውየምንመሰክረው  የሚል ጥያቄ ማንሳታችን አይቀርም፡፡ ለዚህ ጥያቄያችን መልስ የምናገኝባቸው ሦስት የመመስከሪያ መንገዶች አሉ፡፡ እነሱም፡-

  • በአንደበታችን

እግዚአብሔር አምላካችን አንደበት የሰጠን እውነትን በመመስከር ለክብር እንድንበቃበት እንጂ ውሸት በመናገር አምላካችንን እንድናሳዝንበት አይደለም፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ በመልእክቱ ‹‹አንደበቱን ሳይገታ ልቡን እያሳተ እግዚአብሔርን የሚያመልክ የሚመስለው ማንም ቢኖር የእርሱ አምልኮ ከንቱ ነው›› በማለት በአንደበታችን እውነትን እንድንመሰክርበት ይመክረናል /ያዕ. 1$26/፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉ መስክሮም ይድናልና›› እያለ እውነትን መመስከር ለመጽደቅና ለመዳን ወሳኝ ጉዳይ ነው ይለናል /ሮሜ 10፥10/፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ወንጌልን በዓለም ዞረው ያስተማሩት በአንደበት መመስከር ያለውን ሰማያዊ ዋጋ ስለተረዱ ነው፡፡ አንደበታችን እውነትን በመመስከር ለሰማዕትነት የሚያበቃን መሆኑን ተገንዝበን አንደበታችን ሰዎችን ከማማት፤ ያለሥራቸው ስም ከመስጠት ሊቆጠብ ይገባዋል፡፡

  • በሕይወታችን

በሕይወት መመስከር ያላመኑትን ወደ ማመን የሚያመጣ ትልቅ መሣሪያ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት መመሪያችን ነው፡፡ በሕይወት መመስከር ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተቀመጡትን ሕግጋትና ትእዛዛት በተግባር ለውጦ ማሳየት መቻል ነው፡፡ ለስም አጠራሩ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተራራ ላይ ስብከቱ ያስተማረን ‹‹መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ›› በማለት ነው /ማቴ.5፥16/፡፡ በቅዱሳን የሕይወት ምስክርነት እግዚአብሔር ታይቷል፡፡ በእኛ ሕይወት እግዚአብሔር ታይቷል ወይ ብለን ሁላችን ራሳችንን ልንመረምር ያስፈልጋል፡፡

  • በአላውያን ፊት

ከባዱና ታላቁ ሰማዕትነት በአላውያን ነገሥታትና እግዚአብሔርን በማያምኑ ሰዎች ፊት ያመኑትን እምነት ሳይፈሩ መመስከር መቻል ነው፡፡ አላውያን ነገሥታት የእግዚአብሔርን አምላክነትና ፈጣሪነት ስለማያምኑ ሰማዕታትን ያሰቃያሉ፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሰማዕት የሚሆኑት ክርስቲያኖች የሚያገኙትን ሰማያዊ ክብር ስለሚያስቡ ወደ እሳት ቢጣሉ፣ በሰይፍ ቢቆረጡ፣ በድንጋይ ቢወገሩ ምንም አይመስላቸውም፡፡ በዘመነ ሰማዕታት የኖሩ ክርስቲያን ወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው ግፍና ስቃይ ለዚህ አባባላችን መሳያ ነው፡፡ ቀዳሜ ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስ እውነትን በሐሰት ለውጠው የእግዚአብሔርን አምላክነት በመካድ በሥልጣናቸው ተመክተው ለነበሩ አይሁድ ያላንዳች ፍርሃት ስለ እግዚአብሔር የባሕርይ አምላክነት  በመመስከሩ በድንጋይ ሲወግሩት፣ ዓይናቸው በኃጢአት ለታወረ አይሁድ ‹‹ጌታ ሆይ ይህን ኃጢአት አትቁጠርባቸው›› በማለት ለወጋሪዎቹ ምሕረትን ለምኗል /የሐዋ. ሥራ 7፥60/፡፡

የሰማዕትነት ዓይነቶች

የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት የሰማዕትነት ዓይነቶች ሁለት ናቸው ይሉናል፤ ሲተነትኑትም ሰማዕት ዘእንበለ ደም (ደማቸውን ሳያፈሱ ሰማዕት የሆኑ) እና ደመ ሰማዕታት (ደማቸውን በማፍሰስ ሰማዕት የሆኑ) በማለት በሁለት አበይት ክፍሎች መድበውታል፡፡ እነዚህ ብያኔዎች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ሰማዕትነትን ከአፈጻጸም አንጻር በሦስት መሠረታዊ ቀለሞች ይመስሉታል፡፡ (ማኅበረ ቅዱሳን፤ ሐመረ ተዋሕዶ፤ ገጽ 130 ነሐሴ 2002 ዓ.ም.)

  • አረንጓዴ ሰማዕትነት

እንደማንኛውም ሰው በከተማ እየኖሩ ዓለምን ለማሸነፍ የሚጥሩ ከራሳቸው ጋር ታግለው ዲያብሎስን ድል ማድረግ የቻሉ አረንጓዴ ሰማዕታት ይባላሉ፡፡ የሚበላ፣ የሚጠጣ ሳያጡ ሁሉን የሰጣቸውን ፈጣሪ እያመሰገኑ ራሳቸውን በጾምና በጸሎት በመወሰን ያጡ የተቸገሩ ወገኖቻቸውን ለመርዳት የማይሰለቹ የጽድቅ ሥራ በመሥራት የሚያገኙትን ሰማያዊ ጸጋ በማሰብ የሚደሰቱ ናቸው፡፡ ከዚህ መልካም ሥራቸው የተነሣ ስድብ፣ ነቀፌታ፣ ስደት፣ እስራት ሲደርስባቸው መከራውን ሁሉ በአኮቴት (በምስጋና) ተቀብለው ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑ ናቸው፡፡

  • ነጭ ሰማዕትነት

ይህን ዓለም አሸንፈው ግርማ ሌሊትን ጸብአ አጋንንትን ታግሰው በዱር በገደል የኖሩ አባቶቻችን ሕይወት የምናይበት ነው፡፡ ጌታችን ‹‹ማንም ከእናንተ መካከል ያለውን ሁሉ ትቶ የማይከተለኝ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም›› ብሎ የተናገረውን ቃል በተግባር ያሳዩትን የሚወክል ነው /ሉቃ 14$27/፡፡ ይህ የሰማዕትነት ጥሪ ለሁላችንም የቀረበ እንደሆነ እንድንረዳው ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› ብሎናል /ማቴ. 16፥24/፡፡ ስለሆነም ራሳችንን ከውስጣዊ ፈተና ለማዳንና ከልቦና ኃጢአት ለመጠበቅ በጾም፣ በጸሎት፣ በትኅርምት በትሕትና ጸንተን በመዓልትና በሌሊት እግዚአብሔርን እያመሰገን ልንኖር ያስፈልጋል፡፡

  • ቀይ ሰማዕትነት

ይህ ሰማዕትነት በደም የሚመጣ የሰማዕትነት ዓይነት ነው፡፡ እግዚአብሔርን በማምለካችን፣ ቅዱሳንን በማክበራችን፣ ማተብ በማሠራችንና በአጠቃላይ ክርስቲያን በመሆናችን የሚመጣብንን መከራና ስቃይ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር በመታገስ በሰይፍ ተቀልተን፤ በመንኮራኩር ተፈጭተን፤ ወደ እቶን እሳት ተጥለን የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል የምናገኘው ክብር ነው፡፡ ይሔ ሰማዕትነት የመጨረሻ ደረጃ ነው፡፡ (ያረጋል አበጋዝና አሉላ ጥላሁን፤ ነገረ ቅዱሳን፤ ገጽ 26-30፤ 1997 ዓ.ም.)

ኢትዮጵያውን ሰማዕታት

በቀዩ የሰማዕትነት መንገድ በሀገራችን በኢትዮጵያ ሰማዕትነት የተቀበሉ ክርስቲያን ኢትዮጵያውያን በርካቶች ናቸው፡፡ በአምስቱ የመከራ ዘመናት ማለት በ9ኛው መቶ ክ/ዘመን በዮዲት ጉዲት፤ በ16ኛውመቶ ክ/ዘመን  በአህመድ ግራኝ፤ በ17ኛው መቶ ክ/ዘመን  በሱስንዮስ፤ በ19ኛው መቶ ክ/ዘመን በደርቡሾች እና በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በፋሺስት ኢጣሊያ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች በሰማዕትነት አልፋዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በርካታ የቤተ ክርስቲያናችን ቅርሶች ተዘርፈዋል፤ መተኪያ የሌላቸው ገዳማቶቻችን ፈራርሰዋል፤ በቅድስና ሕይወታቸው ምሳሌ የነበሩ ሊቃውንቶቻችንም ተሰውተዋል፡፡

በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወደ ተከሰተውን ቀይ ሰማዕትነት ስናይ ደግሞ በዓለማችንም ሆነ በአገራችን በሰማዕትነት ያለፉ ክርስቲያን ወገኖቻችን በርካቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ራሱን አይሲስ እያለ የሚጠራው አሸባሪ ቡድን የተሻለ እንጀራ ፍለጋ ከሀገራቸው ተሰደው የሊቢያን በረሃ ሲያቋርጡ የነበሩ ክርስቲያን ኢትጵያውያንን ይዟቸው ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ ቢያስገድዳቸውም ለፈጣሪያቸውና ለሃይማኖታቸው ታማኝ በመሆን በሰማዕትነት አልፈዋል፡፡ እነዚህና ወደፊት በእግዚአብሔር ፈቃድ ሰማዕት የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን በሰማያዊው መዝገብ ውስጥ ለዘላለም ስማቸው በሰማዕትነት ተጽፎ ይኖራል፡፡

ውድ ክርስቲያኖች፣ ሰማዕትነት ባለፉት ዘመናት ብቻ የሚዘከር አይደለም፡፡ ትውልድ እስካለ ድረስ የሚቀጥል እንጂ፤ እስከ ዛሬ ድረስ በሰማዕትነት ካለፉ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን የምንማረው የሚያምኑትን የሚመሰክሩ የሚመሰክሩትን የሚኖሩ ክርስቲያኖች መሆናቸውን ነው፡፡ በሰማዕትነት በመጽናታቸው ለክብር በቁ፤ ስማቸው ከመቃብር በላይ ሕያው ሆነ፤ለዘለዓለምም ሕያው ሆኖ ይኖራል፡፡

በዓለም ስንኖር በተለያ ሁኔታም ቢሆን ከሰማዕትነት ዓይነቶች አንዱ ለክርስቲያኖች የማይቀር መሆኑን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ሲያስታውሰን ‹‹ዓለም ቢጠላችሁ ከእናንተ በፊት እኔን እንደጠላኝ እወቁ፡፡ ከዓለም ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል›› ብሎ ዓለም ስለእኛ ያለውን አመለካከት አስረግጦ ነግሮን፣ ከዓለም ለሚመጣው ሰማዕትነት እንድንዘጋጅና ሁል ጊዜ በንስሐ ሕይወት ተዘጋጅተን እንድንጠብቀው አስጠንቅቆናል /ዮሐ. 15፥18-20/፡፡ ይህ የአምላካችን መልእክትም ከምድራዊው ተድላና ደስታ ይልቅ ነፍሳችንን በማትረፍ የሰማዩን መንግሥት እንድንናፍቅ ያደርገናል፡፡ «ሰው ዓለሙን ሁሉ ቢያተርፍ ነፍሱን ቢያጎድል ምን ይጠቅመዋል?» /ማቴ 16፥26/፡፡

በቅርቡም በአላውያን ፊት ሰማዕትነትን በደም የተቀበሉ ወንድሞቻችን ዓለምና በውስጧ ያለው ሁሉ ጠፊ፣ ከንቱ ፣የከንቱ ከንቱ እንደሆነ አስበው፣ ነፍሳቸው እንዳትጎድል ወስነው፣ሰማዕትነትን ሊቀበሉ ባሉበት ቅጽበት በሕሊናቸው ከሚመጣው የቤተሰብ፣ የጓደኛና ሀብት ንብረት ከማፍራት ጉዳይ በላይ ሰማያዊውን መንግሥት አስበው የጭንቀት መልክ እንኳ ሳታይባቸው ለታደሉት ብቻ የምትሰጠውን የሰማዕትነት ጽዋ ተጎነጩ፡፡ እኒህ ወንድሞቻችን ክርስቲያናዊ በሆነ መንፈሳዊ ዐይን ሲታዩ እንዴት ያስቀናሉ<? እኛም በአጸደ ሥጋ ያለን ክርስቲያኖች ከእነዚህ ሰማዕታት ወንድሞቻችን ስለ ሃይማኖታችን በሰይፍ ፊት ሆነ በየትም ቦታ መመስከር እንዳለብን በንግግር ሳይሆን በተግባር ተምረናል፡፡ በእውነት በዚህ ዘመን እግዚአብሔር ለሰማዕትነት የሚመርጣቸው እንዳሉም ተረድተናል፡፡ አዎ! ስለ እግዚአብሔር ራሳችንን፣ ጊዜያችንን፣ ሀብታችንን ለመስጠት ወደ ኋላ የምንል በዘመናችን ለክርስትናቸው አንገታቸውን የሚሰጡ እንዳሉ ስናይ ምን ተምረን ይሆን?

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *