ሰሙነ ሕማማት ሰኞ – አንጾሖተ ቤተ መቅደስ እና መርገመ በለስ

ሰሙነ ሕማማት ሰኞ - አንጾሖተ ቤተ መቅደስ  እና መርገመ በለስ

በቅዱስ ማርቆስ ወንጌል እንደተገለጠልን ጌታችን የሆሣዕና ዕለት ቢታንያ በምትባል መንደር ያድርና በማግስቱም ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ተራበ ፡፡/ማር. 11.11-14/ ቅጠል ያላትን በለስ ከሩቅ አይቶ ወደ በለሲቱ ቀረበ፣ ነገር ግን ከቅጠል በቀር አንዳች ፍሬ አላገኘባትም፡፡ ከአሁን ጀምሮ ማንም ከአንቺ ፍሬ አይብላ ብሎ ረገማት፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ ዕለት መርገመ በለስ የተፈጸመበት ሰኞ ይባላል፡፡

ትርጓሜ፤- በለስ የተባለች ቤተ እስ ራኤል ናት፤ ፍሬ የተባለች፣ ሃይማኖትና ምግባር ናት፡፡ ከእስራኤል ፍቅርን፣ ሃይማኖትን፣ ምግባርን ፈለገ አላገኘም፡፡ እስራኤልን ሕዝበ እግዚአብሔር መባ ልን እንጂ፣ ነቢይነት፣ ካህንነት፣ መሥ ዋዕት አይገኝብሽ ብሎ ረገማት፡፡ በመርገሙ ምክንያት ትንቢት ክህነት መሥዋዕት ከቤተ እስራኤል ጠፉ፡፡

በለስ ኦሪት ናት፡- ኦሪትን በዚህ ዓለም ሰፍና ቢያገኛት ኦሪትና ነቢያትን ልሽር አልመጣሁም ልፈጽም እንጂ በማለት ፈጸማት፤ ሕገ ኦሪትን ከመፈጸም በቀር በእርሷ ድኅነት አላደረገባትምና ፍሬ ባንቺ አይሁን አላት፤ ድኅነት በአንቺ አይደረግብሽ ብሏታልና እንደመድረቅ ፈጥና አለፈች፡፡ በአዲስ ኪዳን የድኅነት ዘመንም ተተካች፡፡

በለስ ኃጢአት ናት፡፡ የበለስ ቅጠል ሰፊ እንደሆነች ሁሉ ኃጢአት በዚህ ዓለም ሰፍታ ሰፍና አገኛት፡፡ በለስ ሲበሉት ይጣፍጣል ቆይቶ ግን ይመራል፤ ኃጢአትም ሲሠሩት ደስ ደስ ያሰኛል ኋላ ግን ያሳዝናል፡፡ በአንቺ ፍሬ አይ ገኝ የሚለውም፤ በኃጢአት ፍዳ ተይዞ የሚቀር አይኑር ለማለት ነው፡፡ በለሷም ስትረገም ፈጥና መድረቋ፣ በአዳም ምክንያት ያገኘችን ዕዳ በደል በእርሱ እንደጠፋችልን ለመግለጽ ነው፡፡

ከዚህ ቀጥሎ ወደ ቤተ መቅደስ ሔደ፤ ቤተ መቅደስ ቤተ ጸሎት፣ ቤተ መሥዋዕት መሆኑ ቀርቶ ቤተ ምሥያጥ /የንግድ ቤት/ ሆኖ ቢያገኘው፤ «ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች… እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት» ማቴ. 21፤13 ብሎ የሚሸጡበትን ሁሉ ገለበጠባቸዉ፣ ገርፎም አስወጣቸዉ፣ ይህም የሚያሳየዉ ማደሪያው ቤቱ የነበርን እኛ የአዳም ልጆች ኃጢአት ሰፍኖብን ስንኖር ቢያገኘን ኃጢአታ ችንን ሁሉ እንዳራቀልን የሚገልጽ ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ አንጽሖተ ቤተ መቅደስ የተፈጸመበት ሰኞም ይባላል፡፡

ለብርሃነ ትንሣኤው አምላካችን በሰላም ያድርሰን፡፡
ይቆየን፡፡

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *