ልደተ ክርስቶስ (ገና)

ልደተ ክርስቶስ (ገና)
እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳቹ!!!
ከጌታችን ከልደቱ ያገኘነው ምንድን ነው?
ዳግም ልደት
በአዳም በደል ምክንያት አጥተነው የነበረው ልጅነታችንን ክርስቶስ በልደቱ ዳግመኛ እንደመለሰልን ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።” ዮሐ 1፥12 በማለት ገልጾታል።
ሰላም
በጌታችን ልደት ለዓለም ሁሉ የሚሆን ዘላለማዊ ሰላም ተገኝቷል። ይህም “ክብር እግዚአብሔር በሰማያት ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጐ ፈቃድ” እያሉ ቅዱሳን መላእክት በመዘመራቸው ተረጋግጧል። ሉቃ 2፥14። ስለዚህ በክርስቶስ ያገኘነው እውነተኛ ሰላም በእኛ ጸንቶ እንዲኖር ዘወትር በጾምና በጸሎት እየተጋን ስለሰላም የምንማፀን ሆነን ልንገኝ ይገባል። ሰላም የክርስትና መታወቂያ አርማ ነውና።
ብርሃን
“በጨለማ የሄደ ሕዝብ ብርሃንን አየ፤ በሞት ጥላ አገርም ለኖሩ ብርሃን ወጣላቸው።” ኢሳ 9፥2። ለአምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ያህል በዲያብሎስ ቁራኝነት ተይዞ የነበረው አዳም ወደሚደነቀው ብርሃን የተሸጋገረው በክርስቶስ ልደት ነው። እኛም በልደቱ ያገኘነውን የጽድቅ ብርሃን ጠብቀን ለመኖር (ብርሃነ ወንጌልን) ፈጽመን ከኃጢአት ርቀን በጽድቅ ሥራ ተወስነን ብርሃን ሆነን ልንኖር ይገባል።
ነጻነት
“በነጻነት እንኖር ዘንድ ክርስቶስ ነጻ አወጣን። ከእንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገና በባርነት ቀንበር አትያዙ”። ገላ 5፥1። የሰው ልጅ እግዚአብሔርን በነጻነት እያመሰገነ ይኖር ዘንድ ተፈጥሯልና። ኃጢአት በመሥራት የዲያብሎስ ባርያ ሳንሆን በተሰጠን ነጻነት በመጠቀም የጽድቅ አገልጋዮች ሆነን ልንመላለስ ይገባል።
ይቅርታ
በአዳም በደል ምክንያት ከአብራኩ የተከፈሉ በሙሉ በደለኛ ሆነው የነበሩበትን ዘመን ለውጦ አዳምንና የልጅ ልጆቹን በደል ደምስሶ ፍቅርን ይመሠርት ዘንድ ጌታ ተወለደ። በምድርና በሰማይ ላሉት ፍቅርን መሠረተ። እርሱ የሰው ልጆችን በደል ሳይቆጥር ሁሉን ይቅር እንዳለ ክርስቲያንም የበደሉትን ሁሉ ይቅር ይል ዘንድ የፈጣሪው ትዕዛዝ ነውና ዘወትር ሊፈጽማት የምትገባ ከእግዚአብሔር ጸጋ የምታስደምር የልደቱን ብርሃን ለማየት እንደበቁ በዚህም ደስ እንደተሰኙ እንደ ቅዱሳን መላእክት ለእውነተኛ ምስጋና የምታደርስ የጽድቅ መሠረት የበረከት በር ናት። ማቴ 18፥21-23፣ ማቴ 5፥23-25። መባህን ትተህ ሂድ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ የሚለው አምላካዊ ቃል ይቅርታ የክርስትና ሕይወት መመሪያ መሆኑን ያሳያልና ዘወትር ልንፈጽማት ይገባል።
ፍቅር
ፍቅር ሰሃቦ ለወልድ ኃያል እም መንበሩ ወአብጽሖ እስከለሞት /ፍቅር ኃያል ወልድን ከዙፋኑ አወረደው እስከ ሞትም አደረሰው።/ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረው እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጅን በደል ሳይቆጥር በዙፋኑ ሆኖ ምሬሃለሁ ማለት ሲችል ፍቅሩን ይገለጽ ዘንድ በከብቶች በረት ተወለደ። እውነተኛ ፍቅሩ ለክርስትናችን መሠረት ለጽድቃችን ፋና እንደሆነ መጻሕፍት ያረጋግጣሉ።እንግዲህ በልደቱ ያገኘነውን ሰላም፣ ነጻነት፣ ይቅርታ፣ ብርሃንና ፍቅር ዋጋ የተከፈለበት ጸጋ የወረስንበት በመሆኑ ዘወትር በድንቅ ፍቅሩ የሚታደገን አምላካችን እግዚአብሔር በሰጠን ጸጋ እስከ መጨረሻው ድረስ ጸንተን እንድንኖር ክብራችንንና ጸጋችንን አስተውለን ከኃጢአት ርቀን በንሰሐ ታጥበን እራሳችንን ለክርስቶስ የተወደደ መስዋዕት አድርገን እንድናቀርብ የእግዚአብሔር ቸርነት የድንግል ማርያም አማላጅነት የቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት አይለየን።አሜን።
share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *