ሆሣዕና ዕለት ከተፈጸሙት ተግባራት ምን እንማራለን?

ሆሣዕና ዕለት ከተፈጸሙት ተግባራት ምን እንማራለን?

ፍጹም ትህትናን
ነብዩ ኢሳይያስ ”እግዚአብሔርን በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ አየሁት፥ የልብሱም ዘርፍ መቅደሱን ሞልቶት ነበር”(ኢሳ 6፥1)። ብሎ የተናገረለት የጌቶች ጌታ የንጉሦች ንጉሥ የሆነ አምላክ ራሱን ዝቅ አድርጎ በአህያ ጀርባ መቀመጡ ፍጹም ትህትናን ያስተምረናል። በከበረ ቃሉ ”ከእኔ ተማሩ፥ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና፥ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ” (ማቴ 11᎓29) እንዳለን የከበረች ትህትናን ከባለቤቱ መማር ይገባናል። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለጌታ ትህትና የተናገረውንም ማስተዋል ይገባል ”እርሱ አምላካችን የሁሉ ፈጣሪና የማይመረመረ ክብር ያለው ንጉሥ ሆኖ ሳለ ለክብሩ በሚገባ ባማረና በተንቆጠቆጠ ቤት አልተወለደም ራሱን ዝቅ አድርጎ በበረት ተገኘ እንጂ። በዚህ ዓለም ባለጠግነትና ብዕል ከተትረፈረፈች እናት አልተወለደም ከደሀይቱ ንጽህት ቅድስት ድንግል ተወለደ እንጂ። የትህትና አባት ነውና ደቀ መዛሙርቱን ሲመርጥ እንኳ እንደ ዓለም ምርጫ ተናጋሪዎችና ጥበበኞች አዋቂዎች የተባሉትን ልምረጥ አላለም ከድሀ ቤተሰብ የተገኙ ድሆችን መረጠ እንጂ። ሊያሰተምር በተጓዘበት ሁሉ ከፍ ያለ ዙፋን ዘርጉልኝ መደገፊያ ትራስ አምጡልኝ አላለም ዝቅ ብሎ በምድር ተቀመጠ እንጂ። በሰው ሁሉ ፊት ሲቆም በዕንቁ የተሰራ ልብስ ልልበስ አላለም ከሰዎች እንደ አንዱ ለብሶ ተገኘ እንጂ። ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝም ፈረስ ጫኑልኝ፣ ልጓም ሳቡልኝ፣ ሰረገላ አዘጋጁልኝ፣ ሠራዊት አቁሙልኝ አላለም ዝቅ ብሎ በአህያ ጀርባ ተቀመጦ ተጓዘ እንጂ” ይህ ግሩም ነገር ነው! ቅዱስ አባ መቃርስም እንዲህ ብሏል ”ጌታ እኛን ስለማዳን እንዲህ ራሱን ዝቅ ካደረገ እኛ ስለራሳችን መዳን ምን ያህል ትህትና ያስፈልገን ይሆን?” የትሁታን አምላክ በቃልም በግብርም ያሰተማረንን የትህትና ግብር ዕለት ዕለት ልናስበው ልንኖረውም ይገባል። ትህትና የተለየው ሕይወት ከእግዚአብሔር መንግሥት ለራቀ ሰው ምልክቱ ነወና።

ክብር እና ምስጋናን
የጌታችን የኢየሩሳሌም ጉዞ በምስጋና እና በክብር የተሞላ ነበር። ደቀ መዘሙርቱ፣ ሕፃናቱ እና እጅግ ብዙ ሕዝብ ደግሞ የለበሱትን አውልቀው መንገድ ላይ እያነጠፉ፣ የዘንባባ ዝንጣፊ እየጎዘጎዙና እያወዛወዙ፣ ሆሣዕና በአርያም እያሉ ዘምረውለታል። ይህ ክብር የካህናት አለቆችን፣ ጻፎችንና ፈሪሳውያንን ደሰ አላሰኘም። እኛስ ዛሬ እንደ ሕፃናቱ በፊቱ የሚቀርብ እርሱም የሚቀበለው የጸሎትና የምስጋና ሕይወት ይዘናልን? ደቀ መዛሙርቱ ልብሳቸውን እንዳነጠፉለት በንስሐ የነጻ ሕይወታችንን ልናቀርብ ተዘጋጅተናልን? ለምለም የዘንባባ ዝንጣፊን የመሰለ ደምቆ የሚታይ ምግባር በእጃችን አለን?
የእግዚአብሔርን ፍቅርና ርኅራኄ
ጌታችን በኢየሩሳሌም ደጅ ሲቀርብ ከተማይቱን አይቶ ማልቀሱ ለሰው ያለውን ፍጹም ፍቅርና ርህራሄ ያሳየናል። ለሰላም የመጣ አምላክ ነውና ሰላሙን ባለመቀበል ልባቸውን የሚያጸኑ ብዙዎች በኢየሩሳሌም እንዳሉ አይቶአልና ከኀዘኑ የተነሳ የከበረ ዕንባውን አፍስሷል። የካህናት አለቆችና ጻፎች የሚያመሰግኑ ሕፃናትን ድምጽ ላለመስማት ጆሮአቸውን በመድፈን፥ ኋላም ዝም አሰኝልን በማለት በገሃድ ጥላቻቸውን ገልጠዋል። እርሱ የፍቅርና የርህራሄ አምላክ ነውና ልባቸውን አይቶ ስለእነርሱ እንባውን አፈሰሰ። የርህራሄው ጥልቅነት የሚደንቀው ከዕንባው በላይ የከበረ ደሙን በፍጹም ፍቅር ስለ ሁሉ ሊያፈሰ በታላቅ ትህትና በመካከላቸው መገኘቱ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን ፍጹም ትህትና፣ ፍቅርና ርኅራኄ የተሞላ የምስጋና ሕይወት ያድለን ዘንድ፤ መጪውንም ሳምንት በሰላም አሳልፎ ለብርሃነ ትንሣኤው እንዲያደርሰን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን። አነሳስቶ ላስጀመረን አስጀምሮ ላስፈጸመን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይሁን፤
ለዘለዓለሙ አሜን!

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *