የእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን መገለጫዎች

የእውነተኛዋ ቤተ ክርስቲያን መገለጫዎች

በቀሲስ ብርሃኑ ጎበና

ቤት የሚለው ቃል ወገን፤ ነገድ፤ ዘር፤ ትውልድ፤ ጉባኤ፤ ማኅበር ማለት እንደሆነ አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ላይ ጠቅሰዋል፡፡(ኪ.ወ.ክ ገጽ 268) የያዕቆብ ወገን ቤተ ያዕቆብ (ቤተ እስራኤል)፤የዳዊት ወገን ቤተ ዳዊት እንዲባል በመንፈሳዊና በምሥጥራዊ ልደት ከክርስቶስ የተወለዱ ምእመናንም ቤተ ክርስቲያን ይባላሉ፤ ቤተ ክርስቶስ (የክርስቶስ ወገን) እንደ ማለት ነው፡፡ ዳሩ ግን በዘመናችን ስምና ግብር ለየቅል ሆነው በተቃራኒ ያሉት ወገኖች ሳይቀሩ ስሙን መጠሪያ አድርገው አናስተውላለን፤ ዘመናችን አማናዊቱ ቤተ ክርስቲያን ስምዋን ወስደው በሚጠሩ አስመሳዮች የተወረረችበት ወቅት በመሆኑ እውነተኛዋን ለይቶ ማወቅ ግድ ይላል፡፡

እንዲት ቤተ ክርስቲያንን ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ የሚያሰኛት በ381 ዓ.ም በቁስጥንጥንያ የተሰበሰቡት 150 ኤጲስ ቆጶሳት (ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን) በቀኖና ሃይማኖታቸው ላይ እንደገለጡት አንዲት(one ) ቅድስት (Holy) የሁሉና በሁሉ ያለች(universal ) እና ሐዋርያዊ ውርስ (Apostolic succession) ያላት ስትሆን ብቻ ነው ከእነዚህ ከአራቱ አንዱን ያጎደለች የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ልትሆን አትችልም አይደለችምም፡፡

እንደ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመሥጥሮ ቤተ ክርስቲያን ማለት “እግዚአብሔር ግዕዛን ካላቸው ፍጥረታት ጋር ያለው ግንኙነት ነው ይላሉ፡፡ ከዚህም የተነሣ የቤተ ክርስቲያንን ዕድሜ በሦስት ይከፍሉታል፥ አንደኛ የመጀመሪያዪቱ ቤተ ክርስቲያን ሰው ከመፈጠሩ በፊት በዓለመ መላእክት የነበረችው የመላእክት አንድነት ናት፤በሊቃውንት አመሥጥሮ ሁለተኛዋ የቤተ ክርስቲያን ዕድሜ ከአቤል ጀምሮ እስከ ሐዲስ ኪዳን መግቢያ ድረስ የነበሩ ደጋግ ሰዎች አንድነት ነው፤ ሦስተኛዪቱ እና የመጨረሻዪቱ ግን በክርስቶስ ደም የተመሠረተችው የክርስቲያኖች አንድነት ናት፡፡ እርስዋም የጸጋና የጽድቅ ምንጭ ናት ከላይ የተወሱት ሁለቱ ግን ምሳሌነት ብቻ ነበራቸው፡፡” (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ ገጽ 12) ከላይ እንደተገለጸው ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በሚከተሉት ነጥቦች እርስዋን መስለው በዙሪያዋ ከከበብዋት ትለያለች፡-

አንዲት –

እውነተኛ የወይን ግንድ እኔ ነኝ እንዳለ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የባሕርይ አምላክነት ያመኑ ክርስቲያኖችም በእርሱ ላይ የበቀሉ ቅርንጫፎች ናቸውና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሊሆኑ ይገባል፡፡ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አለምንም . . . አንተ አባት ሆይ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ . . . እኛም አንድ እንደሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ” ዮሐንስ ወንጌል 17 ፥ 20 – 23፡፡ ከሚለው የጌታ አነጋገር የምንረዳው ይህን አንድነት ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም “ለአንዱ ተስፋችሁ እንደ መጠራታችሁ መጠን አንድ አካልና አንድ መንፈስ ትሆኑ ዘንድ እማልዳችኃለሁ፥ ጌታ አንድ ነው ሃይማኖትም አንዲት ናት ጥምቀትም አንዲት ናት” ኤፌሶን 4 ፥ 4 – 5። በማለት ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ እንዲት መሆንዋን አስገንዝቡዋል፡፡ስለሆነም ቤተ ክርስቲያን በእብነ በረድ ትሠራ በጭቃ፤ በሀገር ቤት ትመስረት በውጭ ሀገር እምነትዋ ሥርዓትዋ አንድ ነው፡፡

ቅድስት-

ክርስቶስ በቅዱስ ደሙ መሥርቷታል፤ አንጽቷታል፤ ቀድሷታልና ቤተ ክርስቲያን ቅድስት ናት ኤፌሶን 5 ፥ 26፡፡የቤተ ክርስቲያን ቅድስና የተገኘው ቅድስና የባሕርይ ገንዘቡ ከሆነው ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ ወደ እርስዋ የገቡ ርኩሳን ይቀደሳሉ እንጂ በውስጥዋ ያሉ ሰዎች በኃጢአት በክህደት ቢረክሱ እርስዋ አትረክስም፡፡ ዳሩ ግን እኔ ቅዱስ እንደሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ባለው መሠረት በእርሱ ያመኑ በቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የተጠለሉ ሁሉ ቅድስናን ገንዘብ ሊያደርጉ ይገባል፡፡

የሁሉና በሁሉ ያለች –

በደመ ክርስቶስ የተመሠረተችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዚህ ወገን ናት የዚህ ወገን አይደለችም የማትባል በዘር፣ በቋንቋ፣ በጎጥና በቀለም እንዲሁም በቦታ የማትከፋፈል የሁሉና በሁሉ ያለች ናት፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የሁሉም መሆንዋን እንዲህ ሲል ገልጾታል“አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ገላቲያን 3 ፥ 28፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን

ሐዋርያዊት-

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን የመሠረተው በሐዋርያት መሠረትነት ላይ ነው “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ አንተ ብጹዕ ነህ . . . እኔም እልሃለሁ አንተ ዐለት ነህ በዚይች ዐለት ላይም ቤተ ክርስቲያኔን አሠራታለሁ የሲዖል በሮችም አይበረታቱባትም፡፡ የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሃለሁ በምድር የምታስረው በሰማይ የታሰረ ይሆናል በምድርም የምትፈታው በሰማይ የተፈታ ይሆናል”ማቴዎስ 16 ፥ 15፡፡

ከትንሣኤው በኃላም “ሰላም ለእናንተ ይሁን አብ እኔን እንደላከኝ እንዲሁ እኔ እናንተን እልካችኃለሁ ይህንንም ብሎ እፍ አለባቸውና እንዲህም አላቸው መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኃቸው ይሰረይላቸዋል ይቅር ያላላችኃቸው ግን አይሰረይላቸውም” ዮሐንስ ወንጌል 20 ፥ 22፡፡

ከላይ በተገለጸው መሰረት ቤተ ክርስቲያንን የመምራትና የማስተዳደር ስልጣንን ሐዋርያት ከጌታ ተቀብለዋል፡፡ቅዱስ ጳውሎስም “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሄርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” የሐዋሪያት ሥራ 20 ፥ 28፡፡ በማለት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ልትመራ እንደሚገባ አስገንዝቦናል ሲኖዶስ ማለት የጳጳሳት ጉባኤ መሆኑን ልብ ይልዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያን ዘክርስቶስ በቅዱስ ሲኖዶስ መመራት የጀመረችው ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ ለመሆኑ ምሥክሩ መጽሐፍ ቅዱስ ነው፡፡ የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተደረገበትን ምክንያት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ግብረ ሐዋርያትን በገለጸበት ጽሑፉ ላይ እንዲህ ተርኮታል፡- አንዳንዶችም ከይሁዳ ወረዱና፥ እንደ ሙሴ ስርዓት ካልተገረዛችሁ ትድኑ ዘንድ አትችሉም ብለው ወንድሞችን ያስተምሩ ነበር፡፡ በእነርሱና በጳውሎስ በበርናባስም መካከል ብዙ ጥልና ክርክር በሆነ ግዜ ስለዚህ ክርክር ጳውሎስና በርናባስ ከእነርሱም አንዳንዶች ሌሎች ሰዎች ወደ ሐዋርያት ወደ ቀሳውስቱም ወደ ኢየሩሳሌምም ይወጡ ዘንድ ተቆረጠ። . . .በሐዋርያት ያደረ ቅዱስ መንፈስ በቅዱስ ጳውሎስም ያደረ ሆኖ ሳለ ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ ሌሎች ሰዎችን ጨምረው ለምን? ወደ ሐዋርያት መሄድ አስፈለጋቸው? የሚለው መጠይቅና መልሰ የቤተ ክርስቲያን እርከናዊ መዋቅር ከዘመነ ሐዋርያት ጀምሮ የነበረ መሆኑን ያስገነዝበናል ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ለተዋቀረው የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የተገዙ መሆናቸውን ያሳያል ምክንያቱም ሐዋርያት ቤተ ክርስቲያንን ይጠብቁና ያስተዳድሩ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ የሾማቸው ናቸውና። ስለዚህ ለመጀመሪያዋ ቤተ ክርስቲያን የመጨረሻው ወሳኝ አካል እነርሱ ነበሩ ይህ ሐዋርያዊ ውርስ ባላት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንም የመጨረሻው ውሳኔ ሰጪ አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ለዚህም ነው ሲኖዶሳዊት ያልሆነች ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት አይደለችም የምንለው፡፡

ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደ ምንረዳው የመጀመሪያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በኢየሩሳሌም ኤጲስ ቆጶስ በሐዋርያው በቅዱስ ያዕቆብ ሊቀ መንበርነት ከ49 – 50 ዓ.ም ባለው ግዜ የተካሄደው ከላይ በተገለጸው መሠረት ከአሕዛብ ወገን ክርስትናን በተቀበሉና ከአይሁድ ወገን ክርስትናን በተቀበሉት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ለዚያ እልባት ለመስጠት ነበር ሐዋርያትም ግራ ቀኙን አድምጠው የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥተዋል።ሐዋርያትና ቀሳውስት ወንድሞችም በአንጾኪያና በሶርያ በኪልቅያም ለሚኖሩ ከአሕዛብ ወገን ለሆኑ ወንድሞች ሰላምታ ያቀርባሉ፡፡ ያላዘዝናቸው ሰዎች ከእኛ ወጥተው ትገረዙ ዘንድና ሕግን ትጠብቁ ዘንድ ይገባችኃል ብለው ልባችሁን እያወኩ በቃል እንዳናወጡአችሁ ስለ ሰማን ስለ ጌታችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነፍሳችውን ከሰጡት ከምንወዳቸው ከበርናባስና ከጳውሎስ ጋር የተመረጡትን ሰዎች ወደ እናንተ እንልክ ዘንድ በአንድ ልብ ሆነን ፈቀድን፡፡ራሳቸውም ደግሞ በቃላቸው ያንኑ ይነግሩአችሁ ዘንድ ይሁዳንና ሲላስን ልከናል፡፡ ለጣዖት ከተሠዋ ከደምም ከታነቀም ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ ጤና ይስጣችሁ፡፡ ” የሐዋርያት ሥራ 15 ፥ 22 – 29፡፡

ቤተ ክርስቲያን ከምድረ ፍልስጤም ወደ ሌሎቹ የሮማ ግዛቶች ግዛትዋን እያሰፋች በመጣች ግዜም መዋቅርዋ፤ ሐዋርያዊ ሠንሰለቱ እንደተጠበቀ ነበር፤ ከቤተ አይሁድም ከቤተ አሕዛብም የመጡ ከሐዋርያት የሰሙ ከሐዋርያት የተማሩ ሐዋርያውያን አባቶች በሐዋርያት መንበር እየተተኩ ሠንሰለቱ ሳይበጠስ ቀጥሉዋል እንደ ኤሬኒዮስ ናኤጲፋንዮስ አገላለጽ በቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ላይ ከቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥሎ ደቀ መዝሙሩ የነበረው ሊኖስ ሲሆን (የዚህ አባት ስም በ2ኛ ጢሞቲዎስ 4 ፥ 21 ላይ ተጠቅሱዋል) አውሳብዮስ ግን የቅዱስ ጴጥሮስ ወራሴ መንበር ቀሌምንጦስ ነው ይላል፡፡ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ላይ ቅዱስ ማርቆስ አሰተምሮ ያሳመነው፣ ያጠመቀውና በክህነት የወለደው ጫማ ሰሪ የነበረው አናንያስ ነበር የተሰየመው ፤ የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፖሊካርፕ እንዲሁም ሌሎችም ከሐዋርያት በቀጥታ ቤተ ክርስቲያንን የማስተዳደር ስልጣንን ተቀብለዋል፡፡

ሐዋርያውያን አባቶች የተባሉት ደግሞ ደቀ መዛሙርታቸውን በእነርሱ እግር እየተኩ ሐዋርያዊ ውርስ እስከ ዘመናችን ደርስዋል፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያዊት ናት የምንለው በሐዋርያው በቅዱስ ፊልጶስ አማካይነት በ34ዓ.ም ጥምቀትን ተቀበለች፥ በኃላም በአራተኛው ምዕተ ዓመት በሲኖዶስ ሕግ በቅዱስ ማርቆስ መንበር ሥር የተዋቀረች በመሆኑ ነው፡፡ የራስዋ መንበር ባለቤት የሆነችውም ከእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያን በዓመጽ ተገንጥላ ሳይሆን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት በሥርዓቱ ነው፡፡ ለዚህም አባቶቻችን አያሌ ዘመናት በትእግስት የእስክንድርያ ቤተ ክርስቲያንን ደጅ ጠንተዋል፡፡ይህም የሐዋርያዊ ውርስ ሠንሰለቱ እንዲጠበቅ የከፈሉት መሥዋዕትነት ነው፡፡

ይህ ሐዋርያዊ ውርስ በውጭው ዓለም በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም በተቋቋሙት ዓብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ዘንድ ተጠብቆ ሊኖር ግድ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በሐዋርያት የተዋቀረ ሐዋርያዊ ውርስ ነው ስለሆነም ግዜ ፈቅዶላቸው በመንበሩ ላይ ከተሰየሙት ግለሰቦች ጥሩነትና መጥፎነት አንጻር የምንገባበትና የምንወጣበት አይደለም፡፡ ትውልድ ያልፋል ትውልድ ይተካል ቤተ ክርስቲያን ግን ዘላለማዊት ናት፡፡

ወስብሀት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *