የአቡነ ተክለሃይማኖት የልደት በዓል በታላቅ ድምቀት ተከበረ

የአቡነ ተክለሃይማኖት የልደት በዓል በታላቅ ድምቀት ተከበረ

በየዓመቱ ታኅሣሥ 24 ቀን የሚከበረው የጻድቁ አባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖትን በዓለ ልደት ታኅሣሥ 21 ቀን 2010ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በትላቅ ድምቀት ተከብሮ ውሏል፡፡ ከኢትዮጵያ በመጡ መምህር ዲ.ዶ.ር ቴዎድሮስ በለጠ ከዋዜማው ምሽት ጀምሮ ሥርዓተ ማኅሌቱ እስኪጀመር ድረስ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን፣ የስካንድኖብያ ቤተክህነት ሊቀ ካህናትና በዴንማርክ የኮፐን ሀገን ደብረ ምሕረት አማኑኤል እና ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም አቢያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪ ቆሞስ አባ ዘሚካኤል ፣ በፊንላንድ ሄልሲንኪ የደብረ ሰላም መድኀኔዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ምእምራን ቀሲስ ዮሴፍ ፣ ካህናትና ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ ሕጻናት ፣ ከሄልሲንኪና እና ከሌሎች የፊንላንድ ከተሞች የመጡ ምእመናን እና ምእመናት በተገኙበት በተለያዩ መርሐ ግብር ተከብሯል፡፡

በዓሉን በማስመልከት በተከናወኑት መርሐ-ግብርም ፣ ትምህርት፥ ቀጥሎም ሌሊቱን በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ማኅሌት ተቆሟል፡፡ ሥርዓተ ቅዳሴው ጠዋት ከተከናወነ በኋላ ፣ በዓሉን በማስመልከት በዲን. ዶ/ር ቴዎድሮስ ትምህርት የተሰጠ ሲሆን ቀጥሎም በሊቃውንትና በደብሩ መዘምራን ያሬዳዊ ዝማሬዎች ቀርበዋል፡፡ ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ በሊቃውንቱና በደብሩ መዘምራን ታጅቦ ዑደት ካደረገ በኋላ ወደፊት ለመግዛት ለታቀደው ሕንፅ ቤተ ክርስቲያን መግዣ ይሆን ዘንድ ሕዝቡ አቅሙ በፈቀደ መልኩ ቃል እንዲገባ ቅስቀሳ ተደርጓል።
በመጨረሻም ፣ በአገልግሎት ለተራዱ በፊንላንድ የደብረ ሰላም መድኀኔዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ እንዲሁም ለበዓሉ መሳካት በዕውቀታቸው ፣በጉልበታቸው ፣ በገንዘባቸው እና በአገልግሎት አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምእመናን እና ምእመናት ምስጋና ቀርቦ በዓሉ በጸሎት ተፈጽሟል፡፡

በሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ የጻድቁ አባታችንን በዓለ ልደት፣ ፍልሰተ አጽም እና በዓለ እረፍት የንግሥ በዓላት በደማቅ ሁኔታ እንደሚከበሩ ይታወቃል።

 

የአቡነ ተክለሃይማኖት የልደት በዓል ታህሣሥ 2010

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *