የ2009 ዓ.ም. የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ ልደት ተከበረ

by ግንኙነት ክፍል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ 24 ቀን የሚውለውን የጻድቁ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን በዓለ ልደት ታኅሣሥ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ቲኩሪላ በሚገኘው የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከበረ። በዓሉ ታኅሣሥ 21 ቀን 2009 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ፣ የደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ ሕጻናት፣ ከሄልሲንኪና እና ከተለያዩ ከተሞች የመጡ ምእመናን እና ምእመናት እንዲሁም በፊንላንድ የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እና ምዕመናን በተገኙበት ተከብሯል።
በዓሉ ዓርብ ምሽት በጸሎት ከተጀመረ በኋላ የአቡነ ተክለ ሃይማኖትን ገድል እየተተረጎመ ትምህርት ተሰጥቷል። በመቀጠልም ከሌሊቱ 6፡45 ጀምሮ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ማኅሌት እና ስብሐተ እግዚአብሔር ደርሷል። ቅዳሜ ጠዋት ሥርዓተ ቅዳሴው ከተከናወነ በኋላ፤ በዲ/ን ዶ/ር ሰሎሞን አበበ «ከሕፃናትና ከሚጠቡ ልጆች አፍ ምስጋናን አዘጋጀህ» በሚል ርዕስ ሰፊ ትምህርት ተሰጥቷል። ከዚያ በማስቀጠልም ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ በካህናት እና በምእመናን ታጅቦ ዑደት ካደረገ በኋላ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና በደብሩ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን ያሬዳዊ ወረብ ቀርቧል። በመጨረሻም ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ በካህናት አባቶች ተሰጥቶ ታቦት ሕጉ ወደ መንበረ ክብሩ ተመልሷል።
በአገልግሎት ለተራዱ በፊንላንድ የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት አገልጋዮች፣ እንዲሁም ለበዓሉ መሳካት በእውቀታቸው ፣በጉልበታቸው ፣ በገንዘባቸው አስተዋጽኦ ላበረከቱ ምእመናን እና ምእመናት ምስጋና ቀርቦ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።
ልደተ ተክለ ሃይማኖት 2009
Recommended Posts
በፊንላንድ ዩቫስኲላ ከተማ የቅዱስ ዑራኤል ጽዋዕ ማኅበር ተመሠረተ።
March 11, 2023