የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊው በዓል በቱርኩ -ፊላንድ በድምቀት ተከበረ!

የቅዱስ ሚካኤል ዓመታዊው በዓል በቱርኩ -ፊላንድ በድምቀት ተከበረ!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ዘንድ  በየዓመቱ ሰኔ 12 ቀን  የሚከበረው   ዓመታዊው የቅዱስ ሚካኤል ክብረ  በዓል በቱርኩ- ፊላንድ  ሰኔ 10/2009 ዓ .ም በደመቀ ሁኔታ  ተከበረ።

በዘንድሮ ዓመት  ከሌላው ጊዜ በተለየ መልኩ በርካታ ምእመናን ወደ ቱርኩ ተጉዘው በዓሉን ያከበሩ ሲሆን ፣ ከመቼውም ጊዜ  በበለጠ መልኩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሐዶ  እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አቢያተ ክርስቲያናት  ካህናት እና ምእመናን በጋራ በተገኙበት በማኅሌትና  በቅዳሴ ከማለዳው  የተጀመረው ክብረ በዓል ቀኑን ሙሉ ቀጥሎ  ከቅዳሴው ፍፃሜ በኋላም  ትምህርትና  እና ልዩ ልዩ መንፈሳዊ  ዝግጅቶች ቀርበዋል ።

በፊላንድ  ሄልሲንኪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን የደብረ አሚን አቡነ  ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን    አስተዳዳሪ  መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ እና በፊላንድ  ሄልሲንኪ የኤርትራ  ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ቤተክርስቲያን የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ም/አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ቀሲስ አንገሶም  በበዓሉ ለተገኙት ምእመናን ትምህርት እና ምክር የሰጡ ሲሆን በዲያቆን ዶክተር ሰሎሞን አበበም ወቅቱን የተመለከተ ትምህርት ተሰጥቷል።

የደብረ አሚን  አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን  ሰንበት ት/ቤት መዘምራን ለዕለቱ ያዘጋጁትን ወረብ ሲያቀርቡ የቱርኩ የቅዱስ ሚካኤል ማኅበር መዘምራንም እንዲሁ መንፈሳዊ መዝሙሮችን  አቅርበዋል።

በበዓሉ ላይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አቢያተ ክርስቲያናት  ካህናትና ዲያቆናት  በጋራ  በዓሉን በተመለከተ መንፈሳዊ ዝማሬ ያቀረቡ ሲሆን   በተጨማሪም በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት የሕፃናት ክፍል የተዘጋጀ መዝሙር እና መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ጥያቄና  መልስም ለምእመናን  ቀርቧል።

በቱርኩ -ፊንላንድ የቅዱስ ሚካኤል  ማኅበር በኢትዮጵያውያን እና በኤርትራውናን የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ምእመናን  በአንድነት ተመሥርቶ መንፈሳዊ አገልግሎቱን  እያከናወነ የሚገኝ በመልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ስም የተመሠረት  መንፈሳዊ ማኅበር  መሆኑ ይታወቃል።

   ማርታ  በላይ

                                                                                              ከቱርኩ ቅዱስ ሚካኤል ማኅበር

የቱርኩ ቅዱስ ሚካኤል በዓል ሰኔ 2009ዓ.ም.

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *