የመስቀል ደመራ ለመጀመሪያ ጊዜ በሂልሲንኪ ሊከበር ነው
by ግንኙነት ክፍል
በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ የመስቀል ደመራን በዓል በሄልሲንኪ ከተማ የዮሐንስ ቤ/ክ አጠገብ በሚገኘው (korkeavuorenkatu 12) አደባባይ/ሜዳ/ ሰኞ መስከረም 16 ቀን 2009 ዓ.ም. ከ17፡30– 20፡30 ፣ የደመራ ሥነ ሥርዓት በማከናወን እንደሚያከብር ተገለጸ።
የደመራ ሥነ ሥርዓቱ የደብሩ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ መዘምራን፣ ሕጻናት፣ በሄልሲንኪና አጎራባች ከተሞች የሚገኙ ምእመናን፤ ተጋባዥ ካህናት፣ ዲያቆናት ፣ የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሓላፊዎች ፣ የከተማው ከንቲባ ጽ/ቤት እና ልዩ ልዩ ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት እንደሚከናወን ታውቋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በአይሁድ አማካኝነት ተቀብሮ ከነበረበት ቦታ የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት የሆነቸው ንግሥት ዕሌኒ ፣ ደመራ አስደምራ በዕጣኑ ጢስ ጠቋሚነት መስቀሉ የተቀበረበትን ተራራ በማወቅ፣ ጢሱ ከጠቆመበት ተራራ መስቀሉ ተቆፍሮ ወጥቶ በክብር እንዲቀመጥ እና ምእመናን እንዲፈወሱበት በማድረግ ያደረገችውን ገድል ለማዘከር ሲባል ፣ ደመራው በተደመረበት ዕለት በመስከረም 16 ቀን እንዲከበር ተደርጓል፡፡
የደመራ በዓል በዮኔስኮ በዓለም ቅርስነት በ2013 እ.ኤ.አ. የተመዘገበ በዓል ሲሆን፣ ከ 45-50 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት እምነት ተከታዮች በሚገኙባት በኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን በሚኖሩባቸው አህጉራተ ዓለም በደማቅ ሁኔታ ተከብረው ከሚውሉ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ ነው፡፡ በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ፣ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ ምእመናን፣ ተጋባዥ እንግዶችና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በተገኙበት በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት በየዓመቱ መስከረም 16 ተከብሮ የሚውል የአደባባይ በዓል ነው፡፡
Recommended Posts
ማኅሌተ ጽጌ ወደ ፊንላንድኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ
October 04, 2023
ሀገረ ስብከቱ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ጠቅላላ ጉባኤውን አጠናቀቀ
September 03, 2023
በፊንላንድ ሀገር የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ቡራኬ ተከናወነ !
September 03, 2023