የጠቅላላ ጉባኤ ዜና

የጠቅላላ ጉባኤ ዜና
[CBC country="fi" show="y"]

የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤ/ክ ሁለተኛውን ክፍል የጠቅላላ ጉባኤ አከናወነ፡፡
በኢ.ኦ.ተ. ቤ.ክ በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ኅዳር 3 ቀን 2009ዓ.ም ኦሎንኩላ ቫንሃ ኪርኮ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት – ምሽቱ 3፡00 ሰዓት ባካሄደው በዚሁ ሁለተኛ ክፍል ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በዋናነት የሂሳብ እና የኦዲት ሪፖርቶች፣ የቀጣይ ዓመት እቅዶች እና የደብሩን ዋና ጸሐፊ የማጽደቅ ጉዳዮች ለውይይት ቀርበዋል፡፡

ጠቅላላ ጉባኤው በደብሩ አስተዳዳሪ በመጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ በጸሎት ከተጀመረ በኋላ፣ በአጠቃላይ 6 አጀንዳዎችን ተመልክቷል፡፡ በመጀመሪያ ተከታትለው የቀረቡት ፤ የባለፈው ዓመት የሂሳብ እና የኦዲት ሪፖርቶች ሲሆኑ፣ በሪፖርቶቹም የተከናወኑ ተግባራት፣ የታዩ በጎ ጎኖች እና ተግዳሮቶች ቀርበዋል፡፡ ሪፖርቶቹንም ተከትሎ ከጉባዔው አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን ለቀረቡ ጥያቄዎችም ከአቅራቢዎቹ ምላሽ ተሰጥቶባቸው ሪፖርቶቹ ጸድቀዋል፡፡

ሪፖርቶቹን ተከትሎ የተከናወነው መርሃ-ግብር የደብሩን ዋና ጸሐፊ ማጽደቅ ሲሆን፣ የአጀንዳው ጭብጥም ቃለ አዋዲውን በማጣቀስ በአስተዳዳሪው አማካኝነት ለጉባዔው ቀርቧል። የዋና ጸሐፊውን አመራረጥ ሂደት አስመልክቶ ከጉባዔው ጥያቄዎች ቀርበው የነበሩ ሲሆን ፣ ለተነሱት ጥያቄዎችም ከደብሩ አስተዳዳሪ ቃለ ዓዋዲው በሚፈቅደው መሠረት እና ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር የተሻለ አማራጭ መሆኑን የሚገልጽ ምላሽ ተሰጥቶ ድምጽ የመስጠት ሂደት ተከናውኗል፡፡ በውጤቱም ዲ.ን. አለምነው ሺፈራው በአብላጫ ድምጽ የደብሩ ዋና ጸሐፊ ሆነው ተሰይመዋል፡፡

ቀጥሎ የታየው አጀንዳ ቤተ ክርስቲያንን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ የሰበካ ጉባኤ እና የኦዲት እና ቁጥጥር ክፍል አባላትን ለጉባዔው የማስተዋወቅ ተግባር ሲሆን፣ አባላቱን እና የተሰጣቸውን የሥራ ድርሻ ጉባኤው እንዲያውቀው ተደርጓል፡፡ በዚህም መሰረት ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ቤተ ክርስቲያንን በኃላፊነት የሚያገለግሉት ምእመናን ለጉባኤው እንደሚከተለው ተዋውቀዋል፡፡

1. ዲ.ን. አለምነው ሺፈራው ዋና ጸሐፊ
2. አቶ አማኑኤል ከበደ ም/ል ሊቀመንበርና የስብከተ ወንጌል ሓላፊ
3. አቶ ዳዊት ሰለሞን የሰንብት ት/ቤት ሓላፊ
4. አቶ ዘረዐያዕቆብ መንገሻ የመረጃና ግኑኝነት ክፍል ሓላፊ
5. አቶ ይልማ ዘርዓይ የልማት ክፍል ሓላፊ
6. ወ/ሮ መሰረት ገ/መድህን የሂሳብ እና ንብረት ክፍል ሓላፊ
7. ወ/ሪት መዓዛ ሲሳይ ገንዘብ ያዥ
8. አቶ ታዬ ነጋሽ የኦዲትና ቁጥጥር ክፍል አባል
9. አቶ ግዛት ቸኮል የኦዲትና ቁጥጥር ክፍል አባል
10. ወ/ሪት ፌቨን ትዕግስቱ የኦዲትና ቁጥጥር ክፍል አባል

በማስከተልም ለጉባኤው የቀረበው እ.ኤ.አ የ2017 የሥራ እና የበጀት ዕቅድ ሲሆን፣ በዕቅዱም በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ስር ያሉ ንዑሳን ክፍላት እና የሕንጻ አስሪ ኮሚቴ ዝርዝር የሥራ እና የበጀት ዕቅዶች ለጉባኤው ቀርበዋል፡፡ ከዕቅዱም ጋር ተያይዞ፣ የስልታዊ ዕቅድ ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኗን የሂሳብ አያያዝ ዘመናዊ ለማድረግ ያካሄደውን የዳሰሳ ጥናት ለጉባኤው አቅርቧል፡፡ ጥናቱም የተለያዩ ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ አማራጮችን ፣ የሂሳብ አሰራር ሂደቱን ዘመናዊ ማድረግ የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች እና ዘመናዊ ባለማድረግ ሊታጡ የሚችሉ ጥቅሞችን በማካተት ለጉባኤው ቀርቧል፡፡ በመቀጠልም ከጠቅላላ ጉባዔው እ.ኤ.አ የ2017 የሥራ እና የበጀት ዕቅድ እና የስልታዊ ዕቅድ ኮሚቴ ባቀረበው ጥናት ላይ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች የቀረቡ ሲሆን፣ ለቀረቡት ጥያቄዎችም ከአቅራቢዎቹ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው፣ የሥራ እና የበጀት ዕቅዱን በማጽደቅ አጀንዳው ተፈጽሟል፡፡

በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያንን ላገለገሉ ለቀድሞ የሰበካ ጉባኤ እና የኦዲትና ቁጥጥር ክፍል አባላት፣ እንዲሁም በግል ተነሳሽነት ቤተ ክርስቲያኗን በትጋት ላገለገሉ አንድ ምእመን የምስክር ወረቀት በመስጠት ጉባኤው በጸሎት ተፈጽሟል፡፡

[/CBC]
share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *