አዲሱ ዓመት (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው)

አዲሱ ዓመት (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው)

አዲሱ ዓመት

ልጆቼ! አዲሱ ዓመት የደስታ የሰላምና የጤና እንዲኾንላችሁ ትሻላችሁን? እንኪያስ ገና ከጅመሩ በስካር፣ በዘፈን፣ በገቢረ ኀጢአት ለማሳለፍ አታቅዱ፡፡ የአዲሱ ዓመት የመጀመሪያውን ዕለት ብቻ ሳይኾን እያንዳንዱን ቀን በገቢረ ኀጢአት አትጀምሩት፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ፣ ምግባር ትሩፋት በመሥራት አሐዱ በሉ እንጂ፡፡ ዕለታት ክፉዎች ወይም ጥሩዎች የሚኾኑት በተፈጥሮአቸው እንደዚያ ኾነው አይደለም፡፡ ዕለቱን ክፉ ወይም ደግ እንዲኾን የምናደርገው እኛው ነን፡፡ የአምናው ማክሰኞ ከዘንድሮ ማክሰኞ የተለየ አይደለም፡፡ የተለየ የሚያደርገው የእኛ ብርታት ወይም ስንፍና ብቻ ነው፡፡

የጽድቅን ሥራ የምንሠራበት ከኾነ አዲሱ ቀን ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመት ለእኛ መልካም ነው፡፡ ኀጢአት የምንሠራበት ከኾነ ግን ቀኑ ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመትም ክፉና መከራ የመላበት ይኾንብናል፡፡ አዲሱን ዓመት በበጐ ሥራ የምንጀምረው ከኾነ በዓመቱ በምናደርገው ማንኛውም ክንውን ላይ በጐ ተጽዕኖ ያሳድርብናል፡፡ በትግሃ ሌሊት፣ በቀዊም፣ በጾም በጸሎት እንድንበረታ ስንቅ ይኾነናል፡፡ በስካር፣ በዘፈን፣ በኀዘን የምንጀምረው ከኾነ ግን ዓመቱ ሙሉ እንዲህ የተጐሳቈለ ዓመትን እናሳልፋለን፡፡ ሕይወታችንን በከንቱ እንገፋለን፡፡ ዲያብሎስም ይህን ጥንቅቅ አድረጐ ስለሚያውቅ ዓመቱን በገቢረ ኀጢአት እንድንጀምረው እየቀሰቀሰ ነው፡፡ ፈቃዳችንን አጥፍቶ፣ ዓይነ ልቡናችንን አሳውሮ በዘፈን፣ በስካር፣ በዋይታ እንድንጀምረው በተለያየ መንገድ እየለፈፈ ነው፡፡

ሰነፍ ሰው “ቀኑ ክፉ ወይም መልካም የሚኾነው በእኔ ምክንያት አይደለም” ብሎ ያምናል፡፡ እንዲህ በማመኑም ክፉ ነው ብሎ በሚያስበው ቀን ገቢረ ጽድቅ መሥራት እንደሚቻል አያስብም፡፡ ቢያደርግም ትርጕም እንደሌለው አድርጐ ይቈጥሯል፡፡ የጽድቅ ሥራ ለመሥራት በተመቻቸለት ቀንም ልል ዘሊል ከመኾኑ የተነሣ ምግባር ትሩፋት ለመሥራት አይሽቀዳደምም፡፡ ስንፍናው ምን ዓይነት ጉዳት እንደሚያመጣበት አይረዳም፡፡ ድኅነቱን ሳይፈጽም ዕድሜውን ኹሉ በከንቱ ይገፋል፡፡ እንዲህ ያለ የሥጋም የነፍስም ጕዳት እንደሚያገኘው ዲያብሎስ ዓይነ ልቡናውን ስለሚያሳውርበት ከአጋንንት ወጥመድ ለመሸሽ ዓቅምን ያጣል፡፡
ዲያብሎስም ዕለት ዕለት ይህን እንዳንገነዘብ በተለያየ ማጥመጃ መንገዶች እኛን ለመጣል ይሯሯጣል፡፡ አንዱ መንገድም ስለ ክርስትና ሕይወታችን ግድ እንዳይኖረን ማድረግ ነው፡፡ በዚህም ክርስቲያናዊ ተፈጥሮአችንን ያሳጣናል፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ በገቢር እንድንሰድብ ያደርገናል፡፡ ነፍሳችንን በቆሸሸ ስፍራ ተወሽቃ እንድትቀር ያደርጋታል፡፡

የምወዳችሁ ልጆቼ! እኛ ግን ይህን ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ በዓለም ላይ ከኀጢአት በቀር ክፉ ነገር እንደሌለ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ ከምግባር ከትሩፋት በቀርም መልካም ነገር እንደሌለ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ በዚህም ዘወትር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን ልንኖር እንዲገባን ማወቅ መረዳት ይገባናል፡፡
መጠጥ ደስታን አያመጣም፤ ደስታን የሚያመጣው ጸሎት ነው፡፡ ደስታን የምናገነኘው ቃለ እግዚአብሔርን ከመስማት እንጂ ከስካር አይደለም፡፡ ስካር የነፍስ መታወክን ያመጣል፤ ቃሉን መስማት ግን ተመስጦን ያመጣል፡፡ ስካር ሁካታን ያመጣል፤ ቃሉን መስማት ግን ሁካታን ያርቃል፡፡ ስካር ዓይነ ልቡና እንዲጨልም ያደርጋል፤ ቃለ እግዚአብሔር ግን የጨለመው ዓይነ ልቡናችን ብሩህ እንዲኾን ያደርጋል፡፡ ስካር የኀጢአት ጓዝ ይዞ ይመጣል፤ ቃለ እግዚአብሔር ግን አዲስ የሚመጡትን ብቻ ሳይኾን የነበሩትንም ያስወግዳል፡፡
ልጆቼ! የዚህን ዓለም ደስታ ንቆ ሰማያዊ ደስታን እንደ መሻት ያለ ጥበብ ምንም የለም ብዬ እነግራችኋለሁ፡፡ ይህን ገንዘብ የምናደርግ ከኾነ፣ ለሰማያዊ ሕይታችን ቅድሚያን የምንሰጥ ከኾነ የዚህ ዓለም ዝባዝንኬ ቢቀርም አይከፋንም፡፡ አንድ ሰው ባለጸጋ ስለኾነ ቅናት አይይዘንም፡፡ ምንም ምድራዊ ሀብት ባይኖረንም ድኾች እንደኾንን አናስብም፡፡ ባለ ጸጋውን ክርስቶስ የያዘ ሰውስ እንዴት ድኻ ይባላል? በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ በዓል ማድረግ ማለትም ይኸው ነው፡፡

እግዚአብሔር የሚወዳችሁ አንድም እግዚአብሔርን የምትወዱት ሆይ! አንድ ክርስቲያን በዓልን ሲያከብር ሳምንትን ወይም ወርን ወይም ዓመትን ጠብቆ መኾን የለበትም፡፡ ከክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ጋር እንደሚስማማ አድርጐ ዕለት ዕለት በዓል ሊያደርግ ይገቧል እንጂ፡፡ ከክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ጋር የሚስማማ በዓል ማለትስ ምን ማለት ነው? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምን እንደሚለን አብረን እናድምጠው፡- “በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም” (1ኛ ቆሮ.5፡8)፡፡ ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ ያደረገ ሰው ዕለት ዕለት በዓልን ያከብራል፡፡ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት የተጠበቀለት ነው፡፡ ከሰማያዊው ማዕድና መጠጥ ተካፍሎ ሐሴት ያደርጋል፡፡ በዚህ ምድር ላይ የሚደረጉ ጊዜያዊ ክንውኖች ስለቀረበት የኾነ ነገር እንደቀረበት አያስብም፤ እርሱ ያገኘው ከዚህ በእጅጉ የሚልቅ ነውና፡፡ ነፍሱን ከሚያቆሽሹ ገቢረ ኀጢአቶች ራሱን ይጠብቃል፡፡
በገቢረ ኀጢአት ተሰማርተን ሳለ ሺሕ ጊዜ በዓላትን ብናከብር ግን እንዳከበርን ልንቈጥረው አይገባንም፡፡ ያከበርነው የበዓል ቀን (በዓል ማለት ደስታ ማለት ነው) ሳይኾን የኀዘን ቀን ነውና፡፡ ነፍሴ በኀጢአት ቀንበር ተይዛ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሳለች የደስታን ቀን ባከብር ለእኔ ምን ጥቅም ያመጣልኛል?

እግዚአብሔር የሚወዳችሁ እናንተም የምትወዱት ልጆቼ! አዲሱ ዓመት የእውነት አዲስ ዓመት እንዲኾንላችሁ ካሻችሁ ነፍሳችሁን ከኀጢአት ቀንበር አላቋት እንጂ ድጋሜ በኀጢአት ሸክም አትጫኗት፡፡ አሮጌው ዓመት እንዳለቀ ስታዩ እግዚአብሔርን አመስግኑት፡፡ ወደሌላ ዘመን አሸጋግሯቸዋልና እግዚአብሔርን አመስግኑት፡፡ ልቡናችሁንም ውቀሱት፡፡ በዕሜአችሁ ስንት ጊዜ እያለፈ እንደ ኾነ እያሰባችሁም ራሳችሁን እንዲህ ብላችሁ ጠይቁት፡- “ቀናት እየሮጡ ነው፡፡ ዓመታቱም እየነጐዱ ነው፡፡ የዕድሜዬ መንገድም እየተጋመሰ ነው፡፡ ታዲያ ምን በጐ ምግባር ያዝኩ? ከዚህ ምድር የማልፍበት ቀን እየቀረበ ነው፡፡ ታዲያ ምን የጽድቅ ሥራ ሠራሁ? በዚህ ዕድሜዬ መሥራት የነበረብኝ ምግባር ትሩፋት ዕድሜዬ ሲገፋ ማድረግ አልችልም፡፡ ታዲያ ዕድሜዬ ሲገፋ ማድረግ የማልችላቸውም የጽድቅ ሥራዎች (ፆም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ አገልግሎት፣… ዕድሜ ሲገፋ ይከብዳሉና) እንዳቅሜ እያደረግኩ ነውን?”

ተወዳጆች ሆይ! አዲስ ዓመት ሲመጣ እነዚህን ነገሮች በጥንቃቄ ልናስብባቸው ይገባናል፡፡ ይህን እያደረግንም ስለ ቀጣዩ ዓመት እናስብ፡፡ ይህን የምናደርግ ከኾነ “ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፤ ዓመቶቻቸውም በችኰላ” አይባልብንም (መዝ.78፡3)፡፡ ዕለት ዕለት በዓልን እናድርግ ብዬ የገለጥኩላችሁም ይኸው ነው፡፡ የእኛ በዓል ዘወትር መኾን ይገባዋል፡፡ የክርስቲያኖች በዓል በዓመታትና በቀናት ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በሳምንት፣ በወር፣ በዓመት የሚከበሩ በዓላት እንዲኖሩ ማድረጓ ዘወትር ከዚሁ ልንርቅ እንደማይገባ ማሳሰቧ እንጂ ሌላ አይደለምና፡፡ ይህን በዓል በየዕለቱ ማድረግም ለኹሉም ይቻላል፤ ለድኻውም ለባለጸጋውም ይቻላል፡፡ በዓልን ለማድረግ (የጽድቅ ሥራን ሠርቶ ሐሴት ለማድረግ) የሚያስፈልገው ቅን ልቡና እንጂ ገንዘብ አይደለምና፡፡

ወዳጄ ሆይ! ገንዘብ የለህምን? ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርግ፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘብ የምታደርግ ከኾነ ገንዘብ ካላቸው በላይ ባለጠጋ ነህ፡፡ “እንዴት?” ትለኝ ይኾናል፡፡ እኔም እንዲህ ብዬ እመልስልሃለሁ፡- የእነዚያ (የባለጠጐቹ) ገንዘብ ያልቃል፡፡ ያንተ ግን ብል አይበላውም፡፡ ጊዜ አይለውጠዉም፡፡ አያልቅም፡፡ ወደ ሰማያት፣ ወደ ሰማየ ሰማያት፣ ወደ ምድር፣ ወደ አየራት፣ ወደ እንስሳቱ ዓይነት፣ ብዙ የብዙ ብዙ ወደሚኾኑት ዕፅዋት፣ ወደ ደቂቀ አዳም በጠቅላላው፣ ወደ መላዕክት፣ ወደ መላዕክት አለቆች፣ ወደ ኀይላት ተመልከት፡፡ እነዚህ ኹሉ የአምላክህ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ የእነዚህን አምላክና መጋቢ ባሪያ መኾን ድኻ መኾን አይደለምና ድኻ አይደለህም ብዬ እነግርሃለሁ፡፡

ተወዳጆች ሆይ! ቀናትን ቈጥሮ በዓል ማድረግ የክርስቲያን ግብር አይደለም፤ የአሕዛብ ግብር እንጂ፡፡ እንዴት? የክርስቲያኖች ተፈጥሮ በቀንና በወር የተገደበ አይደለምና፡፡ አገራችን ሰማይ ነው፡፡ ግብራችን ሰማያዊ ነው፡፡ ኅብረታችንም ከሰማያውያን መላዕክት ጋር ነው፡፡ በዚያ መዓልት ለሌሊት ስፍራውን አይለቅም፡፡ ሌሊትም በተራው ለመዓልት አይለቅም፡፡ እዚያ ኹሌ መዓልት ነው፡፡ እዚያ ኹል ጊዜ ብርሃን ነው፡፡ ስለዚህ “ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ” እንደተባልን ኹል ጊዜ ማሰብ ያለብን ይህንን ነው (ቈላስ.3፡1)፡፡ ክርስቲያናዊ ተፈጥሮአችን ከዚህ ምድራዊ አቈጣጠር በላይ ነው፡፡ በንጽህና በቅድስና እየኖርን ዘወትር በዓልን የምናከብር ከኾነም የዚሁ ዓለም ሌሊት ለእኛ ሌሊት አይደለም፤ መዓልት ነው እንጂ፡፡ ዘመናችንን በሙሉ በገቢረ ኀጢአት፣ በስካር፣ በዘፈን የምናሳልፈው ከኾነ ግን መዓልቱ ለእኛ መዓልት አይደለም፤ ሌሊት ነው እንጂ፡፡ ፀሐይዋ ብትወጣም ልቡናችን ገና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይኖራልና ቀን እንደወጣ አይቈጠርም፡፡

#ሰማዕትነት_አያምለጣችሁ_መጽሐፍ ገጽ 13-19

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *