በዓለ እረፍቱ ለአቡነ ተክለሃይማኖት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከበረ

በዓለ እረፍቱ ለአቡነ ተክለሃይማኖት በደማቅ ሥነ ሥርዓት ተከበረ

በስዊድንና እካንድናቪያን ሀገሮች ሀገረ ስብከት በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በዓለ እረፍቱ ለአቡነ ተክለሃይማኖት ነሐሴ 18 እና 19/2011 ዓ.ም በድማቅ ሥነ ሥርዓት ተከበረ። በበዓሉ ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የተገኙ ሲሆን ሌሎችም ከ አውሮጳ ከተለያዩ አድባራት የተጋበዙ ሊቃውንትም በበዓሉ ተገኝተዋል ።

ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ከበዓሉ ቀደም ብለው ሄልሲንኪ የገቡ ሲሆን ከፊንላንድ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሊዮ ጋር የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርትሲያን ለቤተ ክርስቲያናችን እስካሁን ላደረገችውና እያደረገች ላለው ትብብር አመስግነዋል። ወደፊትም ለአስፈላጊው አገልግሎት ሁሉ እንዲተባበሩ ጥሪ ከማቅረባቸው በተጨማሪም የጋራ በሆኑ አገልግሎቶች ተባብሮ መሥራትን በተመለከተ በማንሳት ውይይት አድርገዋል ።

በማያያዝም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ ቀድሞው አንድነቱ መመልሱን በማንሳት ከዚህ በኋላ መለያየት የማይኖር መሆኑን ብፁዕነታቸው ያስረዱ ሲሆን በፊንላንድም ለሁለት ተከፍለው የነበሩት ምእመናን በአንዲት አጥቢያ ማለትም በሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ሥር ተሰባስበው አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉንም አብራርተዋል ።

ሊቀጳጳስ አቡነ ሊዮም በቅዱስ ሲኖዶሱ ወደ አንድነት መመለሱን በማንሳት መደስታቸውን በመግለጥ ወደፊትም በማንኛውም አገልግሎት በመተጋገዝ እንደሚቀጥሉ ገልጠዋል ። በሌላ መልኩ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሕዝበ ክርስቲያኑ ተጠናክሮ የራሳችን ቤተ ክርስቲያን መግዛት እንደሚገባ በአጽንዖት ያሳሰቡ ሲሆን በዚሁ አገር ተወልደው የሚያድጉ ልጆች ሃይማኖታቸውን ቋንቋቸውን እና ባህላቸውን ማወቅ እንዲችሉ የምታደርገው ቤተ ክርስቲያን ናት ብለዋል ። እንዲሁም ሕዝበ ክርስቲያኑ የተገኘውን የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት በሚገባ አጥብቆ ሊንከባከበው ይገባልም ሲሉ አጽንዖት ሰጥተዋል ።


በተያያዘ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ለመጀመሪያ ጊዜ በፊንላንድ ተወልደው ካደጉ ልጆች መካከል ዲ.ን ያዕቆብ ሳሙኤል ማዕረገ ክህነተ ዲቁና ተቀበለ።

ዲ.ን ያዕቆብ ሳሙኤል ማዕረገ ክህነተ
ዲ.ን ያዕቆብ ሳሙኤል ማዕረገ ክህነተ

ከብፁዕ አቡነ ኤልያስ የስዊድንና ስካንዲናቭያን ሀገሮች ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በዓለ እረፍቱ ለአቡነ ተክለሃይማኖት በሚከበርበት ዕለት ነሐሴ 18/2011 ዓ.ም በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖትቤተ ክርስቲያን ክህነተ ዲቁናን ተቀብሏል ። ሌሎችም ለተመሳሳይ ክብር ሊበቁ የሚችሉ ብዙ ልጆች መንፈሳዊውን ትምህርት በመማር ላይ እንደሚገኙ ታውቋል ። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ መንፈሳዊው ትምህርት እንዲሁም በሰንበት ት/ቤት አስገብተው ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ በዚሁ አጋጣሚ ለማስታወስ እንወዳለን ። ለዲያቆን ያዕቆብ ሳሙኤል እንኳን ለዚህ ታላቅ ክብር አበቃህ እያልን ክብረ ክህነትህን ጠብቀህ በአገልግሎት እንድትበረታ ዝግጅት ክፍላችን በጎ ምኞቱን ይገልጣል።

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *