በቫሳ ለመጀመሪያ ጊዜ የቅዳሴና የሥርዐተ ጥምቀት አገልግሎት ተሰጠ
by ግንኙነት ክፍል
በቫሳና አካባቢው ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች እሑድ ነሐሴ 8 2008 ዓ.ም. ከሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ወደ ስፍራው በተጓዙ አገልጋዮች አማካኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ የቅዳሴና የሥርዓተ ጥምቀት አገልግሎት ተከናውኗል፡፡ በዕለቱ በተካሄደው መንፈሳዊ አገልግሎት በአካባቢው የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች የተሳተፉ ሲሆን ለሰባት ሕጻናትም ሥርዓተ ጥምቀት ተፈፅሟል፡፡
ቫሳ ውስጥ መንፈሳዊ አገልግሎት በመደበኛ የሰንበት ጉባኤ አማካኘነት ላለፉት አራት ዓመታት ይሰጥ እንደነበርና፣ የቅዳሴ አገልግሎት ለማግኘት ግን ሕዝበ ክርስቲያኑ ወደ ሄልሲንኪ በመጓዝ ወይም በሁለት ወር አንድ ጊዜ በግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሚዘጋጅ መንፈሳዊ አገልግሎት ይሳተፍ እንደነበር በአገልግሎቱ ላይ የተገኙ ምእመን ገልጸዋል፡፡
በአግልግሎቱ ላይ የተሳተፉ የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በተለይ ሕጻናትን ክርስትና ለማስነሳት ሁኔታዎች የተመቻቹ እንዳልነበሩ በማስታወስ በከተማቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያናችን አገልጋዮች አማካኝነት በተሰጠው የቅዳሴና ትምህርት አገልግሎት መደሰታቸውን ገልፀው ፣ አገልግሎቱ ቀጣይነት እንዲኖረውም አያይዘው ጠይቀዋል፡፡
የተጀመረውን አገልግሎት ለማስቀጠል ይረዳ ዘንድ በዕለቱ ሦስት ምእመናን ያሉበት አስተባባሪ ኮሜቴ የተመረጠ ሲሆን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑን በማስተባበር፣ ለአገልግሎት የሚሆን ቦታ በማስፈቀድና በአጠቃላይ አገልግሎቱ የሚቀጥልበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት እንደሚሰራ ታውቋል፡፡
ለመንፈሳዊ አገልግሎቱ ከሄልሲንኪ ወደ ቫሳ ተጉዘው የነበሩት የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ስለ ሁኔታው በሰጡት አስተያየት፣ በቫሳ በነበረው መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ሕዝቡ ያሳየውን ተሳትፎና በቫሳ የፊኒሽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ያደረገውን ትብብር አድንቀው ፣ በከተማው የተመሠረተው የቅዱስ ገብርኤል ጽዋ ማኅበር፣ በዓመታዊ የቅዱስ ገብርኤል ክብረ በዓላት ላይ የቅዳሴ መርሃ ግብር ያዘጋጅ ዘንድ የአካባቢውን ሕዝበ ክርስቲያን ማሕበሩን ማጠናከር እንደሚገባው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም በሄልሲንኪ የሚኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት አጥቢያ ምእመናን እንደ ከዚህ ቀደሙ ማኅበራትን በማጠናከር ረገድ የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
አስተዳዳሪው አክለው እንደገለጹት፣ በቀጣይነትም በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላት በሚኖሩባቸው ትላልቅ የፊንላንድ ከተሞች ተመሳሳይ መንፈሳዊ አገልግሎት ለመስጠት መታሰቡና በጽዋ ማኅበርነት በማደራጀት ወደ ፊት ራሳቸውን ችለው ወደ ቤተ ክርስቲያንነት የሚያድጉበትን ሁኔታ የማመቻቸት ሥራ ለመሥራት መታሰቡን ገልጸዋል፡፡
ከሄልሲንኪ ውጪ በቱርኩ የቅዱስ ሚካኤል ጽዋ ማኅበር እንዳለና በዓመት ሁለት ጊዜ የቅዱስ ሚካኤልን ዓመታዊ ክብረ በዓላትን ምክንያት በማድረግ የቅዳሴና የትምህርተ ወንጌል አገልግሎት እንደሚያዘጋጅ ይታወቃል፡፡
Recommended Posts
ማኅሌተ ጽጌ ወደ ፊንላንድኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ
October 04, 2023
ሀገረ ስብከቱ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ጠቅላላ ጉባኤውን አጠናቀቀ
September 03, 2023
በፊንላንድ ሀገር የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ቡራኬ ተከናወነ !
September 03, 2023