የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ እረፍት በደማቅ ሥነ ሥርዓት በሄልሲንኪ ተከበረ።

የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት በዓለ እረፍት በደማቅ ሥነ ሥርዓት በሄልሲንኪ ተከበረ።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስዊድንና ስካንድኔቪያን ሀገሮች ሀገረ ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት በዓለ እረፍት ክብረ በዓል ነሐሴ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ተከበረ። በበዓሉ ላይ የኢትዮጵያና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካህናት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና ምእመናን ተገኝተዋል።

በዓሉ ቅዳሜ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም ምሽት የጻድቁን ገድል በመተርጎም የተጀመረ ሲሆን፤ ከመንፈቀ ሌሊት ጀምሮ ማኅሌት ተቋሟል። ከማኅሌቱ በመቀጠል እሑድ ጠዋት የቅዳሴ ጸሎት ከተከናወነ በኋላ በዓሉ አስመልክቶ በደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ትምህርት ተስጥቷል። በትምህረቱም ላይ የደብሩ አስተዳዳሪ ባስተላለፉት መልእክት የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በፊንላንድ ይታነጽ ዘንድ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ምእመናን ጠንክረው በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

የደብሩ አስተዳዳሪ አያይዘውም “በየጊዜው ለቅዳሴ እና ለመሳሰሉት መንፈሳዊ አገልግሎት ለመተግበር ቦታ በማጣት ብቻ መደረግ የሚገባቸው ሃይማኖታዊ በዓላት ሳይካሄዱ እንደሚቀሩም” አስታውሰዋል።በተለይ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ሀገር ተወልደው ለሚያድጉ ልጆች ሃይማኖታቸውን :ቋንቋቸውን ባህላቸውን በአግባቡ ይዘው እንዲያድጉ ለማስቻል ምእመናን ለጉዳዩን አፅንዖት እንዲሰጥ አሳስበዋል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሕንፃ አሠሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሳሙኤል ያሬድ ባስተላለፉት መልእክት ሁሉም ምእመናን በየወሩ ለሕንጻ መግዣ የሚሆን ገንዘብ እንዲለግሱ እና እንዲሁም ለኮሜቴው ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በመጨረሻ የደብሩ የጽጌ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን ወረብ አቅርበው ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ በካህናት፣ በዲያቆናት፣ በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና በምእመናን ታጅቦ ዑደት ተደርጎ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *