የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የእረፍት  ክብረ በዓል  በታላቅ ድምቀት ተከበረ ።  

የጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የእረፍት  ክብረ በዓል  በታላቅ ድምቀት ተከበረ ።  
ከነሐሴ 24 ቀን እስከ 28 ፥ 2009 ዓ.ም.  ድረስ በታላቅና በልዩ ድምቀት በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሲከበር በሰነበተው በዚህ ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ ግብዣ የተደረገላቸው በአውሮፓ ከሚገኙ የአብያተ ክርስቲያናት አስተዳዳሪዎች መካከል በኖርዌይ ስታቫንገ  የደብረ ገነት መድኃኔዓለም ወኪዳነ ምሕረት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪና በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት የስካንዴኔቭያን ወረዳ ቤተ ክህነት ዋና ፀሐፊ መጋቤ ምሥጢር አባ ቴዎድሮስ አካሉ፣ በኦስትሪያ ቬና የደብረ ሲና  ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉያት ቆሞስ አባ ዘተክለሃይማኖት፣ በኖርዌ ኦስሎ የማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያም አስተዳዳሪ መልአከ ምሕረት ቀሲስ ተስፋ ሚካኤል  እንዲሁም በፊንላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አቢያተ ክርስቲያናት ሊቃውንትና ምእመናን ተገኝተዋል፡፡
ክብረ በዓሉን መነሻ በማድረግ ነሐሴ 24 ቀን 2007 ዓ·ም በሠርክ ጸሎት ተደርጎ ትምህርተ ወንጌል ከኢትዮጵያ በመጡት ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ ተሰጥቷል።
ነሐሴ 26 ቀን በክብረ በዓሉ ዋዜማ  ከምሽት ጀምሮ በተካሄደው ጉባዔ ላይ ትምህረተ ወንጌል ተሰጥቶ ገድለ ተክለሃይማኖት በደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ ተተርጉሟል፡፡ የስብከተ ወንጌሉን ጉባኤ  አያይዞ በሊቃውንቱ መሪነት የሌሊቱ ማኅሌት   ተቁሞ በማለዳው ስብሐተ ነግህ  ኪዳን ደርሶ  ሥርዓተ ቅዳሴው በልዩ ድምቀት በመጋቤ ምሥጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስ መሪነት ተከናውኗል፡፡
ነሐሴ 27 ረፋዱ ላይ ከሥርዓተ ቅዳሴው በኋላ ዲ/ን. ዶ/ር. ቴዎድሮስ በለጠ ክብረ በዓሉን አስመልክተው ”ከመልካም ሽቶ  መልካም ስም ከመወለድ ቀን የመሞት ቀን ይበልጣል” በሚል ርዕስ ትምህረተ ወንጌል ሰጥተው በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን፣ በደብሩ ሰንበት ት/ቤት መዘምራን እና በምእመናን ታጅቦ ታቦተ ሕጉ ከመንበረ ክብሩ ተነስቶ  ሕዝቡን በመባረክ  ዑደት ያደረገ ሲሆን፣ የደብሩ ሰንበት ት/ቤት መዘምራንም ለበዓሉ ያዘጋጁትን ወረብ አቅርበዋል፡፡
በበዓሉ ማሳረጊያ ላይ የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ባስተላለፉት መልዕክት የአጥቢያው ምእመናን አንድነታቸውን በማጠናከር ቤተ ክርስቲያኗ የምትገለገልበት የራሷ የሆነ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እንዲኖራት ለማስቻል ለተቋቋመው የሕንጻ አሰሪ ኮሜቴ ተገቢውን ድጋፍ እና ትብብር እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡ አያይዘውም ክብር በዓሉን በአንድነት ለማክበር የታየውን ኅብረት አድንቀው፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሌሎቹ አኃት አቢያተ ክርስቲያናት በተለየ መልኩ በባህል በቋንቋ እና በዜማ አንድ የሚያደርጋቸው መሆኑን እና በፊንላንድ የተደረገው የአገልግሎት አንድነት  ለሌሎችም ምሳሌ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡
በዚሁ በዓል ላይ መጋቤ ምሥጢር ቆምስ አባ ቴዎድሮስ  ለሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን  አስተዳዳሪ ለመጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፋቃድ ያዘጋጁትን የመስቀል ስጦታ አበርክተው ቃለ ምዕዳን እና ቡራኬ ሰጥተዋል። በበዓሉ ማብቂያ ታቦተ ሕጉ ወደ መንበር ክብሩ ከተመለሰ በኋላ በልዩ ዝማሬ  የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡
በተያያዘ ዜና  እሑድ ነሐሴ 28  ቀን በተጠራው ልዩ የስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ላይ ምእመናን ቀድመው በመገኘት በወቅታዊው የቤተክርስቲያናችን ዓቢይ ፈተና “የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ” ዙሪያ የምስል ወድምጽ ማስረጃ “አባቶቻችንን እወቁ በመናፍቃን ላይ ንቁ” በሚል መነሻ ለሁለት ሰዓታት ከአሳባዊ የምናብ ስጋት በዘለለ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ተግባራዊ ውጤት ማሳያ ቤተሙከራ የሆነውን አውሮፓን በማስቃኘት የቀረበ ሲሆን፤ የመርሐግብሩ አቅራቢ ዲ/ን ዶ/ር ቴዎድሮስ በለጠ በአውሮፓ ባላቸው ቆይታ ይህ ሦስተኛው መርሐ ግብር መሆኑን አውስተው በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ የተነሳው ቅሰታ ከአውሮፓ ምንጩ በማንሳት ዛሬ እያደረሰ ያለውን ተጽእኖ ነገ ሊያስከትል ከሚችለው ከባድ ፈተና አንጻር የሚጠበቀውን ሥጋት አመላክተው የተሐድሶ ኅቡዕ ስልጠና ማጋለጫ ቪዲዮና  የፕሮቴስታንቶች ሕብረት ስትራቴጂአዊ ሩጫ ሰነድ እቅድ ቀርቦ ከምእመናን ምን ይጠበቃል የሚል አቅጣጫ ማሳያ በመጠቆም ወደ አባቶች ማጠቃለያ ተሻግሯል።
የደብራችን አስተዳዳሪም መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በግንዛቤ ማስጨበጫው ዙሪያ ከምንም ጊዜው በላይ ምእመናን ይህን ፈተና ለማለፍ ንቁ ሆነው ራሳቸውን እንዲጠብቁ አንድነትን እንዲያጸኑ እረኛውና መንጋው ተባብረው በመናበብ መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበው በአገረ ስብከቱ ሳይቀር በቀጣይነት  ወቅታዊ ግንዛቤ ማስጨበጫዎችን በተከታታይ ማዘጋጀት ተገቢ መሆኑን አመልክተው ማጠቃለያ እንዲሰጡ ከተገኙት አባቶች ከኖርዌ ስታቫንገር ለክብረ በዓሉ ወደ ፊንላድ ከመጡትና ይህ መርሐ ግብር በአውሮፓ ኖርዌይ እንዲጀመር ምክንያት የሆኑትን መጋቤ ምሥጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስን ጋብዘዋል።
ክቡር መጋቤ ምሥጢር ቆሞስ አባ ቴዎድሮስም እንደማጠቃለያ የተቀመጡትን ነጥቦች ከአውሮፓው ነዋሪ አንጻር በተለየ አቅጣጫ ትኩረት ሰጥቶ ጉዳዩን ማየት እንደሚገባ በማስገንዘብ መንጋን የማስነጠቅ ሳይሆን ለአውሮጳው የምንደርስ ለሌላው የምንተርፍ እስከመሆን መጠንከር እንደሚገባ በቁጭት አስገንዝበዋል። በፓለቲካ ካባ የነገሠውን መለያየት፣ በሥጋዊ ኑሮ ውጥረት  የመጣብንን መንፈሳዊ ዝለት፣ በባህል ወረራ የተሸከምነውን ራስን ማጣት በማሸነፍ ፣ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን ተተኪ ልጆቻችንም የነገይቱ ቤተክርስቲያን ፈተና እንዳይሆኑ  በቁርጠኝነት ራስን በመስጠትና አስፈላጊውን ሁሉ ዋጋ በመክፈል አንድነትን ፈጥሮ ለተዋሕዶ ዘብ መቆም እንደሚገባ በተጠና ሥልት ነጥቦችን አሳይተው ማጠቃለያውን ሰጥተዋል።
በመቀጠልም በአገረ ፊንላንድ ተወልደው ያደጉ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ያሬዳዊ ዝማሬ አቅርበው ማጠቃለያውና ጸሎቱ ከኦስትሪያ ቬና በመጡት በመጋቤ ብሉያት ቆሞስ አባ ዘተክለሐይማኖት ተሰጥቶ የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሆኗል።

የአቡነ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ የእረፍት ክብረ በዓል ነሐሴ 2009 ዓ.ም.

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *