የትንሣኤና የእመቤታችን የድንግል ማርያም የልደት በዓል ልዩ መርሐ ግብር በደማቅ ሁኔታ ተካሄደ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሀገረ ስብከት በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በደብሩ ሰንበት ትምህርት ቤት የሕፃናትና አዳጊዎች ንዑስ ክፍል የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የትንሣኤ በዓልና የእናታችን የቅድስት ድንግል ማርያምን የልደት በዓልን ምክንያት በማድረግ ሚያዝያ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. (May 7, 2017) ልዩ የሕፃናት እና የአዳጊ ልጆች መርሐ ግብር ተካሄደ።
በመርሐ ግብሩ መጀመሪያ ላይ ከሕፃናት እና አዳጊዎች ንዑስ ክፍል በተላለፈው መልእክት ሕፃናትና አዳጊ ልጆች የነገ የቤተ ክርስቲያናችን ተረካቢዎች በመሆናቸው ይልቁንም በውጪው ዓለም ለሚገኙ ሕፃናትና አዳጊዎች የበልጠ ትኩረት በመስጠት ሃይማኖታቸውን ፣ ቋንቋቸውን እና በጎ ባህላቸውን እንዲያውቁ እና እንዳይረሱ አጠናክሮ መሥራት የሚጠበቅ መሆኑን ተገልጿል። በተለይ ወላጆች ለልጆቻቸው መልካም ምሣሌ በመሆን ሃይማኖትን ከሥነ ምግባር ጋር እንዲያስተምሯቸው ከፍተኛ ሐላፊነት እንዳለባቸው በጉባኤው ላይ ተገልጿል። ወደፊት ሰንበት ትምህርት ቤቱ ይህን መሰል ልዩ መርሐ ግብር ለማዘጋጀት ጥረት እንደሚያደርግም የተገለጠ ሲሆን ወላጆችም ከሰንበት ትምህርት ቤቱ ጎን በመቆም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪውን አስተላልፏል ።
የዕለቱን መርሐ ግብር ያዘጋጀው በሰንበት ትምህርት ቤቱ የሕፃናትና አዳጊ ንዑስ ክፍል ሲሆን ሙሉ መርሐ ግብሩ የቀረበው በሕፃናትና አዳጊ ልጆች ነው።
የቀረቡትም መርሐ ግብራት ፡-
- ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ሥነ-ጽሑፍ
- የተለያዩ የትንሣኤ በዓልና የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም የልደት መዝሙራት
- የትንሣኤ በዓልን በተመለከተ ሥነ-ጽሑፍ
- የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር እና ወረብ ናቸው፡፡
በመጨረሻም የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ሕፃናትና አዳጊ ልጆችን በሃይማኖት፣ በምግባር ፣ ጥሩ ምሣሌ በመሆን ኮትኩተን ማሳደግ የሁላችንም ተቀዳሚ ተግባራችን ነው ሲሉ ምክር የሰጡ ሲሆን ወደፊትም ይህንን መሰል ልዩ የሕፃናትና አዳጊ ልጆች መርሐ ግብር ማዘጋጀት እንደሚገባ አሳስበው ጉባኤው በጸሎት ተዘግቷል::
የትንሣኤና የእመቤታችን የድንግል ማርያም የልደት በዓል 2017
Recommended Posts
ማኅሌተ ጽጌ ወደ ፊንላንድኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ
October 04, 2023
ሀገረ ስብከቱ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ጠቅላላ ጉባኤውን አጠናቀቀ
September 03, 2023
በፊንላንድ ሀገር የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ቡራኬ ተከናወነ !
September 03, 2023