የተመራቂ ተማሪዎች ልዩ መርሃግብር ተካሄደ

የተመራቂ ተማሪዎች ልዩ መርሃግብር ተካሄደ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሀገረ ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሰኔ ፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም (June 11, 2017) ዓ.ም በቀለም ትምህርታቸው ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ለተመረቁ ተማሪዎች ልዩ መርሃ ግብር ተዘጋጀ።

በመርሃ ግብሩ መጀመሪያ በደብሩ የስብከተ ወንጌል ክፍል ተጠሪ በተላለፈው መልእክት በዘንድሮ ዓመት የተጀመረው ይህ የተመራቂዎች መርሃ ግብር ወደፊት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል። በተለያዩ የትምህርት ተቋማት ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን መንፈሳዊውንም ትምህርት በሰንበት ትምህርት ቤት ተመዝግበው ሲከታተሉ የቆዩ ሲሆን ከዛሬ በኋላ ተመራቂዎቹ በእውቀታቸውና በመሳሰለው ሁሉ ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያገለግሉ ጥሪ ቀርቧል ።

መርሃ ግብሩ የተዘጋጀው በደብሩ የስብከተ ወንጌል እና የሰንበት ት/ቤት ክፍል በጋራ ሲሆን በዕለቱ በመዝሙርና ኪነ-ጥበባት ንዑስ ክፍል ሥነ-ጽሑፍ፣ በሕፃናትና አዳጊዎች ልጆች እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቱ መዘምራን የተለያዩ መዝሙራት የቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም በደብሩ አዳጊዎች ልጆች የጥያቄና መልስ መርሐ ግብር ቀርቧል።

ከተመራቂ ተማሪዎች መካከል በPHD /በዶክተሬት ድግሪ የተመረቀችዋ ተመራቂ የቀለም ትምህርቷን እና በደብሩ የቆየችበትን መንፈሳዊ አገልግሎትን በተመለከተ ለተሳታፊዎች ልምዷን ያካፈለች ሲሆን፤ ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከልም በደብሩ በቅዳሴ አገልግሎት በዲቁና እና በሰበካ ጉባኤ አባልነት ሲያገለግሉ የቆዩ መኖራቸውንም ለማወቅ ተችሏል ።

በመጨረሻም የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት ለተመረቁት በአጠቃላይ ለ14 ተመራቂዎች በደብሩ የተዘጋጀውን ስጦታ እና የማበረታቻ ሰርተፍኬት የሰጡ ሲሆን አክለውም በዚህ ዘመን ውጤታማ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ለማገልገል በመንፈሳዊው እና በቀለም/ በዘመናዊው ትምህርት የላቁ ምሁራን ጥምረት ወሳኝ መሆኑን ከጠቀሱ በኋላ የዕለቱ ተመራቂዎች በተማሩት እውቀት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች2017

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *