የልጆችና የወላጆች ልዩ መርሐ ግብር ተካሄደ

የልጆችና የወላጆች ልዩ መርሐ ግብር ተካሄደ

በሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የተጋጀው ልዩ የልጆችና የወላጆች መርሐ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ ተካሄደ!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በስዊድንና ስካንዲናቪያን ሀገሮች ሀገረ ስብከት በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በጽጌ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው ልዩ የልጆችና የወላጆች መርሐ ግብር ቅዳሜ ሐምሌ 25/11/2012 በሰሜናዊ ሄልስንኪ በተለምዶ ሃጋ አካባቢ በሚገኘው የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ተከናውኗል። በአይነቱ ልዩ የሆነው የልጆች እና የወላጆች መርሐ ግብርን በጸሎትና ያስጀመሩት የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ ነበሩ።

በመቀጠልም መርሐ ግብሩን ያዘጋጁት በጽጌ ሃይማኖት የሰንበት ትምህርት ቤት የወላጆች ኮሚቴ የወላጆች ድጋፍ ንዑስ ክፍል አስተባባሪነት የዕለቱን መርሐ ግብር ቅደም ተከተል በስፍራው ለተገኙው ምዕመናን እና ወላጆች ካስተዋወቁ በኋላ በዕለቱ የተዘጋጀው ልዩ መርሐ ግብር ተጀምሯል። ቁጥራቸው ከሰባ በላይ የሚሆኑ ሕፃናትና ወላጆች በተካፈሉበት በዚህ መርሐ ግብር በቀዳሚነት መዝሙሮች፣ ጥቅሶች፣ ሥነ ጽሑፍ፣ ጥያቄ እና መልስ ውድድር በሕፃናቱ መካከል ተካሄዷል።
በመቀጠል ልጆች ከልጆች እና በወላጆች መካከል የተለያዩ መንፈሳ እና ስፖርታዊ ውድድሮች ተካሄደዋል።

በመጨረሻም በአይነቱ ልዩ የሆነው የልጆች እና የወላጆች ልዩ መርሐ ግብር ለተሳተፉ እና ባለፉት ወራቶች በስካይፕ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ለተከታተሉ ሕፃናት የምስክር ወረቀት በደብሩ አስተዳዳሪ በመልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ አማካኝነት ለሕፃናቱ የተበረከተ ሲሆን ወደፊትም ተመሳሳይ መርሐ ግብር እንደሚዘጋጅ ተገልጦ የዕለቱ መርሐ ግብር በጸሎት ተዘግቷል።

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *