የሆሣዕና በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

የሆሣዕና በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ሚያዚያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም. የሆሣዕና በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ። በዕለቱም በየዓመቱ እንደሚከናወነው ሁሉ ቅዳሴ ሥርዓቱ በተለየ ሁኔታ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀኖና መሠረት ከተከናወነ በኋላ በቀሲስ ዶክተር አምሳሉ ተፈራ ስለ ሆሣዕና በዓል አጠር ያለ ትምህርት ተሰጥቷል፡፡

የሆሣዕና በዓል ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያ ላይ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ አዕሩግም ሕፃናትም ‹‹ ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ፣ በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው ፣ሆሣዕና በአርያም›› እያሉ ጌታችንን በክብር መቀበላቸው የሚታወስበት በዓል መሆኑን፤ ‹ሆሣዕና› የሚለው ቃል ‹ሆሼዕናህ› ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የተወሰደ ሲሆን ፣ ትርጕሙም ‹ እባክህ አሁን አድን › ማለት እንደሆነ እና ‹‹አቤቱ እባክህ አሁን አድን፤አቤቱ እባክህ አሁን አቅና ፡፡ በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩከ ነው፤ ›› ተብሎ እንደ ተጻፈ አስተምረዋል፡፡

በተጨማሪም በነቢዩ ዘካርያስ ፡ – ‹‹ እነሆ ንጉሥሽ ጻድቅና አዳኝ ነው ፤ ትሑትም ኾኖ በአህያዪቱ ግልገል/ውርንጫ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል ፤ ›› ተብሎ የተነገረው ትንቢት መፈፀሙ (ዘካ. ፱፥፱፤ ማቴ. __፥፬፤ ጌታችን በአህያ ጀርባ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ የሰላም ንጉሥ መኾኑን እንደሚያመለክት ፡፡ እስራኤል ዘመነ ምሕረት ሲኾንላቸው አባቶቻቸው በአህያ ጀርባ ተቀምጠው ይታዩ እንነበረ እና ጌታም እውነተኛ ሰላምን ይዤላችሁ መጣሁ ሲለን በአህያ ላይ። ተቀምጦ ወደ ቤተ መቅደስ መሄዱን ፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ ዘመናት ሳይሽሩት ጠብቃ አሁን ላለው ትውልድ ወደፊትም ለሚመጣ እስከ ዓለም ፍጻሜ የምታቆይ መሆኗ አስረድተዋል።

በቅዳሴው ማጠቃለያም ጸሎተ ፍትሐት፤ እና የዘንባባ ማደል ሥነ ሥርዓት ተከናውኖ በደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ሕጻናት ዕለቱን የሚያወሳ ያሬዳዊ መዝሙሮች ቀርበው የዕለቱ መርሀ ግብር ፍጻሜ ሆኖአል።

የሆሣዕና በዓል 2009 ዓ.ም.

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *