ከሲኖዶሳዊ አንድነቱ በኋላ የመጀመሪያው የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓል በፊንላንድ ሄልሲንኪ ከተማ በጋራ ተከበረ

ከሲኖዶሳዊ አንድነቱ በኋላ የመጀመሪያው የጥምቀት እና የቃና ዘገሊላ በዓል በፊንላንድ ሄልሲንኪ ከተማ በጋራ ተከበረ

ከሲኖዶሳዊ ዕርቅና ሰላም በኋላ የመጀመሪያው በዓለ ጥምቀት በሰሜን አውሮፓ በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ÷ ጥር 11 ቀን 2011 ዓ.ም በጋራ ተከበረ፡፡ የበዓሉ የአከባበር ሥነ ሥርዐት እና ጸሎተ ቅዳሴው በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያ አስተዳዳሪ ÷ በመልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱ ፈቃድ እየተመራ ÷ከተለያዩ የፊንላንድ ከተሞች የመጡ ኦርቶዶክሳውያን በተገኙበት በጸሎተ ቅዳሴና በትምህርተ ወንጌል በድምቀት ተከብሯል፡፡ በተዘጋጀው የባሕረ ጥምቀት ሥፍራ ስብሐተ እግዚአብሔር ደርሶ፣በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ዕለቱን የሚያዘክር ወረብ ቀርቦና ከኢትዮጵያ በመጡት መምህር ÷በዲያቆን ታደሰ ወርቁ በዓሉን የተመለከተ ትምህርት ከተሰጠ በኋላ የበዓሉ ፍጻሜ መሆኑ ተዘግቧል፡፡

ከዚሁ ጋራ በተያያዘ ዜና ÷የፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ጽጌ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት የወላጆች ኮሚቴ ጥር 12 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሕጻናትና ለአዳጊ ወጣቶች ልዩ ‹‹የስጦታ መስጠት›› መርሐ ግብር ማዘጋጀቱም ተዘግቧል፡፡ የመርሐ ግብሩም ዓላማ ሕጻናቱና አዳጊ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን በዝርወት ዓለም በአውሮጳ ሲኖሩ÷ሃይማኖታቸውን፣ሥርዐታቸውንና ትውፊታቸውን አውቀው እንዲጠብቁ ለማድረግ የተዘጋጀ መርሐ ግብር መሆኑን በዕለቱ ተገልጧ፡፡ በመርሐ ግብሩም ላይ ሕጻናቱና አዳጊ ወጣቶቹ ለቤተ ክርስቲያናቸው የዕጣንና የጧፍ መባ ያቀረቡ ሲሆን፤የመንፈሳዊ ዕውቀት ማዕከል የሆነችውም ቤተ ክርስቲያናቸውም መንፈሳዊ ዕውቀቶቻቸውን የሚያበለጽጉበትን ልዮ ልዮ ስጦታዎችን አበርክታላቸዋለች፡፡ሕጻናቱና አዳጊ ወጣቶቹም በዝግጅቱ ላይ ለወላጆቻቸው የተማሩትን የአብነት ትምህርት፣ መነባንብና ወረብ እጅግ አስደማሚ በሆነ ቤተ ክርስቲያናዊ ለዛ ያቀረቡ ሲሆን፤እርስ በእርሳቸውም የጥያቄና መልስ ውድድር አድርገዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ደግሞ ሰለ ኦርቶዶክሳዊ ቤተ ስብእ አኗኗ፣ፈተናና መፍትሔ ትምህርት በዲያቆን ታደሰ ወርቁ መሰጠቱ ታውቋል፡፡መምህሩም በትምህርታቸው በተለይ ወላጆች ልጆቻቸውን በሚገባ በሃይማኖት ኮትኩተው ለማሳደግ መጀመሪያ ወላጆች ለዚሁ ብቁና ዝግጁ መሆን እንደሚገባቸው አበክረው መክረዋል። የፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ በሆኑት÷ በመልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱ ፊቃድ ለሕጻናቱና አዳጊ ወጣቶቹ በሳምንት ሁለት ቀን የአብነት ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ሲታወቅ፤ በተዘጋጀው ሥርዐተ ትምህርት መሠረት ደግሞ ፤በየሳምንቱ እሑድ እንደሚማሩ በዘገባው ተመልክቷል፡፡

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *