በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ላይ ያተኮረ ልዩ ዐውደ ጥናት በሄልሲንኪ ተካሄደ!
by ግንኙነት ክፍል
በፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን እና በሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በጋራ የተዘጋጀው ልዩ ዐውደ ጥናት ባለፈው ቅዳሜ ግንቦት 3 2011 ዓ.ም (May 11 2019) በፊንላንድ ሄልሲንኪ በሚገኘው ሶፊያ የባህል ማዕከል በርካታ ምእመናን እና ታዳሚዎች በተገኙበት ተካሄዷል ::
ለሦስተኛ ጊዜ በተዘጋጀው እና ጥንታዊቷን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስመልክቶ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ጥናታዊ ጽሑፎች በአንድ ኢትዮጵያዊ እና በሦስት ፊንላንዳውያን ሙሑራን ቀርቧል ።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ገዳማትና ገዳማዊ ሕይወት ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ጽሑፍ በቀዳሚነት በዲያቆን አረጋ ጌታነህ ቀርቦ ግንዛቤ አስጨብጧል።
ለረጅም ዓመታት የፊንላንድ ሉተራን ቤተክርስቲያን አለቃ የነበሩት ኒሎ ሆንካነን በነገረ ማርያም ዙሪያ በተለይ ማኅሌተ ጽጌን በተመለከተ ወደ ፊንላንድኛ ቋንቋ በመተርጎም ምእመናኑን ያስደመመ ጥልቅ ጽሑፋቸውን አቅርበዋል ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ዙሪያ በጀርመን ሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ ከ16 ዓመታት በላይ በምርምርና በግዕዝ መምህርነታቸው የሚታወቁት ዶክተር ማይያ ፕሪስ በዐውደ ጥናቱ ላይ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዳሴ ላይ ያተኮረ ጽሑፍ አቅርበዋል ።
በዐውደ ጥናቱ ስለ ላሊበላ ፍልፍል አቢያተ ክርስቲያናት አሠራርና ቀደም ባሉት ዓመታት የላሊበላ ከተማ ነባራዊ ሁኔታ በእንባ በታጀበ ትውስታ ታርያ ላይኔ ገለጻ ካደረጉ በኋላ ከታዳሚዎች ለጽሑፍ አቅራቢዎቹ ጥያቄዎች ቀርቦ ከመድረኩ ምላሽ ተሰጥቷል ።
በመጨረሻም የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ እንደተናገሩት በቀጣይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የዜማ መሣሪያዎች በተለይ በጣዕመ ዜማው ድምፅ የሰውን መንፈስ መቆጣጠር በሚችለው በበገና ላይ ትኩረት የሚያደርጉ ተመሳሳይነት ያላቸው ዐውደ ጥናቶችን ለማዘጋጀት ዕቅዶች እንዳሉ ተናግረዋል ።
በዕለቱም በዘማሪት ሶስና ገብረኢየሱስ የዐውደ ጥናቱን ታዳሚ ያስደመመ የበገና መዝሙሮች ቀርበዋል ።
ዐውደ ጥናቱ በፎቶ
Recommended Posts
ማኅሌተ ጽጌ ወደ ፊንላንድኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ተመረቀ
October 04, 2023
ሀገረ ስብከቱ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ጠቅላላ ጉባኤውን አጠናቀቀ
September 03, 2023
በፊንላንድ ሀገር የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት አዲስ ሕንጻ ቤተክርስቲያን ቡራኬ ተከናወነ !
September 03, 2023