ልዩ የሕጻናትና አዳጊዎች መርሐ ግብር ተካሄደ

ልዩ የሕጻናትና አዳጊዎች መርሐ ግብር ተካሄደ

“ልጆቻችሁንም አስተምሩአቸው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም ስትነሣም አጫውቱአቸው” ዘዳ. ፲፩፥፲፱ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ምክንያት በማድረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮጳ ሀገረ ስብከት በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በሰንበት ትምህርት ቤት ክፍል የሕፃናትና አዳጊዎች ንዑስ ክፍል አዘጋጅነት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የልደትና የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ እሑድ ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. (January 28, 2018) ከሰዓት በኋላ ልዩ የሕጻናት እና የአዳጊ ልጆች መርሐ ግብር ተካሄደ።

 

በመርሐ ግብሩ መጀመሪያ ላይ ከሰንበት ትምህርት ቤት ክፍል በተላለፈው መልእክት ሕፃናትና አዳጊዎች ልጆች የነገ የቤተ ክርስቲያናችን ተረካቢዎች በመሆናቸው ለእነርሱ ትኩረትን፣ ፍቅርንና ጊዜን ሰጥተን ማስተማር የሚጠበቅብን መሆኑን እና መልካም ምሳሌ መሆን ከሁሉም ምእመናን የሚጠበቅ መሆኑ ተገልጿል። ለዚህ ታላቅ ዓላማ ሕፃናትና አዳጊዎችን ለማስተማር በቅርቡ በማኅበረ ቅዱሳን የተተኪ ትውልድ ክፍል ሥርዓተ ትምህርት መዘጋጀቱንና ይህንን ሥርዓተ ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ በማስተማር በኩል ፍላጎትና ተሰጥኦ ያላቸው ምእመናን የሕፃናትና አዳጊዎች ንዑስ ክፍልን እንዲተባበሩ  ጥሪ የተላለፈ ሲሆን፤ ሥርዓተ ትምህርቱን ላዘጋጁት በማኅበረ ቅዱሳን አውሮፖ ማዕከል ለተተኪ ትውልድ ክፍል ታላቅ ምሥጋና ቀርቧል። በተጨማሪም ወላጆች ልጆቻቸውን ሃይማኖታቸውን ቋንቋቸውንና ባሕላቸውን እንዲያስተምሯቸው መልእክት ተላልፏል።

 

ይህን መሰል ልዩ መርሐ ግብር ለልጆች ሲዘጋጅ ዘንድሮ ለ4ኛ ሲሆን፤ በዕለቱ ሙሉ መርሐ ግብሩ የቀረበው በሕፃናትና አዳጊ ልጆች ነበር።

ይኸውም በልጆቹ የቀረቡት፦

  •     የጌታን ልደትና ጥምቀትን የሚያስተምር ሥነ-ጽሑፍ
  •     መዝሙራት
  •     የአብነት ትምህርት (መልእክተ ዮሐንስ እና በግዕዝ ውዳሴ ማርያየገና
  •     የጥያቄና መልስ
  •     ወረብ ናቸው።

በዘንድሮ ዓመት ለልጆች የተሰጠው የገና በረከት የነበረው የቅዱስ ላሊበላ (ቤተ ጊዮርጊስ) ስዕልና ስለ ቅዱስ ላሊበላ አጭር ታሪክ  ሲሆን የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ በቤተ ክርስቲያኗ ስም የተዘጋጀውን የገና በረከት በዕለቱ በመርሐ ግብሩ ላይ ለተገኙ 57 ልጆች ሰጥተዋል፤ ልጆቹም ሰብአ ሰገልን ምሳሌ በማድረግ ለቤተ ክርስቲያን መባዕ እጣን ጧፍና የመሳሰሉትን ይዘው መጥተው ለቤተ ክርስቲያን ሰጥተዋል።

 

የቤተ ክርስቲያኗ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ “የአባቶችን መልእክት” “ተተኪ ትውልድ የሌላት ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን አትባልም”  የሚለውን አባባል መነሻ በማድረግ፣ ተተኪ ትውልድ ላይ ትኩረት ሰጥተን ማስተማር አለብን፤ ይልቁንም በውጪ አገር የምንኖር ኢትዮጵያ በመንፈሳዊ የልጆች አስተዳደግ ላይ ያለን መንፈሳዊ ጥንካሬ ሀገር ቤት ከነበረን በሁለት እጥፍ በመንፈሳዊነት ጠንክረን መገኘት አለብን የሚል መልእክትን አስተላልፈዋል። አያይዘውም፣ በዚህ ትውልድ ያለውን ተጽእኖ ተቋቁመን በትክክል ካስተማርናቸው ቀሪው ዘመን ወርቃማ ጊዜ እንደሚሆን ነገር ግነ ፤ ዛሬ ልጆቻችንን በትክክል ካላስተማርን የሚቀጥለው ትውልድ የጠፋ ትውልድ እንደሚሆንና ተተኪውን ትውልድ ለማስተማር ቤተሰብ፣ ማኅበረሰቡና ቤተ ክርስቲያን ሐላፊነት አለባቸው  ብለዋል። በመጨረሻም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያን ሳያቋርጡ እንዲያመጧቸው አጥብቀው መልእክታቸውን አስተላልፈው  የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።

ሕጻናት የጌታ ልደት 2010

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *