ስለ አቤልና ቃየን (ለሕፃናት)
by ግንኙነት ክፍል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
የተዋሕዶ ፍሬዎች፣ የሃገር ተስፋዎች እንደምን ሰነበታችኁ ልጆች? “እግዚአብሔር ይመስገን ደኅና ነን” አላችችኁ? መልካም፡፡ ትምህርት እንዴት ነው? እየጐበዛችኁ ነው አይደል? ጠንከር ብላችኁ በማጥናት ከአምናው የተሻለ ውጤት ለማምጣት እንደተዘጋጃችኁ ተስፋ አደርጋለኹ፤ በርቱ እሺ?
ዛሬ አቤል እና ቃየን ስለሚባሉ ኹለት ወንድማማቾች ታሪክ ነው ይዤላችኁ የመጣኹት፡፡ ለመስማት ዝግጁ ናችኁ አይደል? በጣም ጥሩ !!!
አዳምና ሔዋን በገነት ይኖሩ ነበር፡፡ ሲበድሉ ግን እግዚአብሔር ከገነት አስወጣቸው፡፡ ደብር ቅዱስ ወደ ተባለ ቦታም ተሰደዱ፡፡ ከዚኽ ቦታ ኾነውም የገነት ሽታ እየሸተታቸው ይኖሩ ነበር፡፡ ወደ ገነት ግን መቅረብ አልተቻላቸውም፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉም በጣም ያለቅሱና ያዝኑ ነበር፡፡
ከዚኽ በኋላ አዳም ሚስቱ ሔዋንን አወቃትና ቃየንና እኅቱን ሉድን ወለደች፡፡ ቀጥላም አቤልንና እኅቱን አቅሌማን ወለደች፡፡ ካደጉ በኋላም አቤል እረኛ ኾነ፤ ቃየን ደግሞ ገበሬ ኾነ፡፡ እረኛ ታውቃላችኁ ልጆች? ገበሬስ? እረኛ ማለት በግ፣ ከብት ወይም ፍየል የሚጠብቅ ልጅ ማለት ነው፡፡ ገበሬ ማለት ደግሞ መሬት አርሶ እኛ የምንበላውን እኽል የሚያመርት ነው፡፡ታድያ ልጆች፥ ከዕለታት በአንዱ ቀን አዳም ሚስቱን ሔዋንን ጠራትና፡- “እኅቴ ሔዋን ሆይ! ልጆቻችን እኮ አደጉ፡፡ ብናጋባቸው ምን ይመስልሻል?” አላት፡፡ እርሷም፡- “ወንድሜ አዳም ሆይ! እንዳልክ ይኹን፡፡ በሐሳብኅ እስማማለኹ እሺ” አለችው፡፡ከዚያ በኋላ “የቃየንን መንትያ ለአቤል፥ የአቤል መንትያ ደግሞ ለቃየን ትኹን” አሉ፡፡ ቃየን ግን ቀናተኛ ስለነበር “ከእኔ ጋር መንታ የኾነችው ሉድ ቆንጆ ስለኾነች ለእኔ ትኹን፡፡ የአቤል መንታ አቅሌማ ደግሞ ቆንጆ ስላልኾነች ለአቤል ትኹን” አለ፡፡ ቃየን አባቱንና እናቱን አልታዘዝም አለ፡፡ ከዚኽ በኋላ አዳም፡- “እንግዲያውስ መሥዋዕትን ሠዉና እግዚአብሔር መሥዋዕቱን የተቀበለለት ሉድን ያግባ” ብሎ መከራቸው፡፡ አቤልም በጣም ጨዋ፣ አስተዋይ፣ የዋኅና ታዛዥ ስለ ነበር እሺ ብሎ “ከእነዚኽ በጐች ንጹሕ የኾነውን ለምን አላቀርብም?” ብሎ አሰበ፡፡ ወዲያውኑም አቀረበ፡፡ ቃየን ግን ጥሩ ልጅ ስላልነበረ ከዘራው ስንዴ መርጦ ሳይኾን “እግዚአብሔር አይበላውም” ብሎ በንቀት እንክርዳድ የበዛበትን፣ ቆሻሻ የተቀላቀለበትን አቀረበ፡፡ እግዚአብሔር ግን የአቤልን መሥዋዕት ብቻ ተቀበለና የቃየንን ሳይቀበልለት ቀረ፡፡
ልጆች! ይሔኔ ቃየን በወንድሙ በአቤል ላይ በጣም ቀና፡፡ “እግዚአብሔር አቤልን እንጂ እኔን አይወደኝም” ብሎ ተቈጣ፡፡ እግዚአብሔርም ቃየንን ጠርቶ “ምነው ፊትኅ ጠቆረ? መልካም ብታደርግስ እንደ ወንድምኽ ደጉ አቤል ይበራ ነበር” አለው፡፡ ቃየን ግን በቅን ልቦና “አምላኬ ሆይ! አዎን መልካም ሥራ አልሠራኹም፤ ከእንግዲኅ ምን ማድረግ ይገባኛል?” አላለም፡፡ እንዲያውም ቁጣው እየበረታበት መጣ፡፡
ልጆች! ከዚኽ በኋላ ቃየን እያዘነ ሲሔድ ሰይጣን መንገድ ላይ አገኘውና “ቃየን ምነው እያዘንክ ትሔዳለኅሳ?” አለው፡፡ አይገርምም ልጆች! ሰይጣን ወዳጅ መስሎ የቀረበው ሊያታልለው እንጂ አዝኖለት እንዳይመስላችኁ፡፡ ከዚኽ በኋላ ቃየን “እኔ ያላዘንኩ ማን ይዘን? አባቴ አዳልቶ ቆንጆዋን እኅቴን ለአቤል ሰጠው፡፡ እግዚአብሔርም አዳልቶ መሥዋዕቴን ሳይቀበልልኝ ቀረ” ብሎ ለሰይጣኑ ነገረው፡፡ ሰይጣንም “ወንድምህን ግደለውና አንተ ቆንጆዋን አግብተኽ ትኖራለኽ” ብሎ ክፉ ምክር መከረው፡፡ ቃየንም “ለካ እንደዚኽም ይቻላል” ብሎ በሰይጣን ሐሳብ ተስማማ፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀንም ወንድሙን አቤልን ጠራውና “ና ወደ ሜዳ ሔደን እንጫወት” አለው፡፡ ከተጫወቱ በኋላ ራባቸውና ምሳ ለመብላት ተቀመጡ፡፡ ምሳቸውን ከበሉ በኋላ ውኃ ለመጠጣት አብረው ወደ ወንዝ ወረዱ፡፡ መዠመሪያ ቃየን ጠጣና አቤልን ጠጣ አለው፡፡ አቤልም ለመጠጣት ጐንበስ ሲል ቃየን ትልቅ ድንጋይ አነሣና አቤልን በድንጋይ ፈጥፍጦ ገደለው፡፡ ልጆች ሞት ለመዠመሪያ ጊዜ በሰው ልጆች የታየው ቃየን አቤልን ከገደለው በኋላ ነው፡፡
በዚኽም ጊዜ እግዚአብሔር በደመና ውስጥ ኾኖ “ቃየን ቃየን ወንድምኅ አቤል ወዴት ነው?” አለው፡፡ ቃየን ግን በትዕቢት ኾኖ “እኔ ምን አውቃለኹ፤ እኔ የወንድሜ የአቤል ጠባቂው ነኝን?” ሲል መለሰ፡፡ እግዚአብሔርም መልሶ “እንግዲኽ ጠባቂው ካልኾንኅ ስለምን ገደልከው? አኹንም ባለ ዘመን ኹሉ በምድር ኹሉ ላይ ድንጉጥና ተቅበዝባዥ ኹን” በማለት እግዚአብሔር ቃየንን ረገመው፡፡ ከዚያን ጊዜ ዠምሮ ቃየን በጣም ፈሪ፣ ሰዎችን የሚሸሽ፣ የሚጨነቅ፣ ባጠፋው ጥፋት እግዚአብሔርን የሚያፍር ኾኖ ኖረ፡፡
ልጆች! ታሪኩ ያሳዝናል አይደል? አዎ! እኛ ጥሩ ስንኾን ወላጆቻችንም ኾነ እግዚአብሔር እንደ ደጉ አቤል ይወዱናል፡፡ እንደ ቃየን ክፉ ስንኾን፣ የምንቈጣ፣ ለመማታት የምንቸኩል፣ የሰው ምክር ሳይኾን የሰይጣንን ምክር የምንሰማ ከኾነ ደግሞ ወላጆቻችን ይረግሙናል፤ አምላክም ያዝንብናል፡፡ እናንተ ግን እንደ ቃየን ሳይኾን እንደ አቤል በማስተዋል፣ በታዛዥነት፣ የተባረከ ልጅ ኾናችኁ መገኘት አለባችኁ እሺ? ጐበዞች፡፡
ልጆች! እስቲ ይኽን ጥቅስ አጥንታችኁ በቃላችኁ ለመያዝ ሞክሩ፡፡
“የኃጥአን መሥዋዕት በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነው፡፡ የቅኖች ጸሎት ግን በርሱ ዘንድ የተወደደ ነው” /መጽሐፈ ምሳሌ 16፡8/፡፡
ደኅና ኹኑ ልጆች!!!
ምንጭ http://mekrez.blogspot.fi/
Recommended Posts
ስለ እመቤታችን ልደት (ለሕፃናትና ዠማሪዎች)
December 26, 2017
ልደተ ክርስቶስ /የገና በዓል/ – ለሕጻናት
January 07, 2017
ዳግም ትንሣኤ (ለሕፃናት)
May 08, 2016