ዜና ጠቅላላ ጉባኤ

ዜና ጠቅላላ ጉባኤ
[CBC country="fi" show="y"]

የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን በቃለ ዓዋዲውና በመተዳደሪያ ደንቡ መሠረት በየዓመቱ የሚያከናውነውን ጠቅላላ ጉባዔ ነሐሴ 29 2008 ዓ.ም.(September 4, 2016) ሄልሲንኪ በሚገኘው ኦሉንኩላ ቫንሀ ኪርኮ ከቀኑ 10:00 ጀምሮ አካሔደ :: ጉባኤው በደብሩ አስተዳዳሪ በመጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ በፀሎት የተክፈተ ሲሆን፣ አስቀድሞ በተላከው የጠቅላላ ጉባዔ መጥሪያ ላይ በተገለጸው መሠረት ሶስት ዓበይት አጀንዳዎች የተካሔዱ ሲሆን፣ እነርሱም 1ኛ የ2008 ዓ.ም የዕቅድ አፈፃፀም ሪፓርት (ዘገባ) ማቅረብ፣ 2ኛ ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚያገለግል እስትራቴጂክ ( ስልታዊ )  ረቂቅ እቅድን ተወያይቶ ማፅደቅ ፣ 3ኛ ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ የሰበካ ጉባዔ አባላትን ምርጫ ማካሄድ ነበሩ፡፡ በመጀመሪያ የ2008 ዓ.ም የእቅድ አፈፃፀም ሪፓርት በደብሩ አስተዳዳሪ በመጋቢ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ቀርቧል ።ሪፓርቱ የደብሩን ጽ/ቤት እና ዘጠኝ አበይት የአገልግሎት ክፍሎችን የአገልግሎት አፈፃፀም ያካተተ ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ከዕቅድ ውጪ የተፈጸሙ እና በአጠቃላይ አገልግሎት ላይ ያጋጠሙ ችግሮችና የተወሰዱ መፍትሔዎች በሪፖርቱ ተካተው ቀርበዋል:: በመቀጠልም ከጉባኤው አስተያየቶችና ጥያቄዎች ቀርበው የነበሩ ሲሆን፣ ለቀረቡት ጥያቄዋችም በደብሩ አስተዳዳሪና በነባር የሰበካ ጉባዔ አባላት ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔውም ሪፖርቱን አድምጦ ተቀብሎታል፡፡ በማያያዝም  ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚያገለግል እስትራቴጂክ ( ስልታዊ ) ዕቅድ ረቂቅ ፣ ከ3 ወር በፊት በተቋቋመውና አምስት አባላት ባሉት የእስትራቴጂክ ኮሚቴ ተወካይ ለጉባዔው ቀርቧል፡፡ የኮሚቴው ተወካይ ለጉባዔው እንደገልጹት፣ ኮሚቴው እቅዱን ሲያወጣ ለምእመኑ የዳሰሳ መጠይቅ በማዘጋጀት ከምእመኑ የተሰጠውን አስተያየትና ጥቆማ እንደ አንድ ግብአት በመጠቀም ለቀጣዩ ሁለት ዓመታት ደብሩ ሊመራበት የሚገባውን ስልታዊ ዕቅድ ረቂቅ ማዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡ ስልታዊ ዕቅዱ በስምንት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ሲሆን የፋይናንስ እስትራቴጂክ ዕቅድ ለሚቀጥለው ጊዜ እንድሚቀርብ አሳውቀዋል፡፡ ዕቅዱ ከቀረበ በኋላ ከጉባዔው በርከት ያሉ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን፣ ለተነሱ ጥያቄዎችም በኮሚቴው ተወካይ ምላሽ ተሰጥቷል፡፡ በስተመጨረሻም የተሰጡትን አስተያየቶች በመቀበል ስልታዊ እቅዱ ጸድቋል::

በመጨረሻም ለቀጣይ ሁለት ዓመታት የሚያገለግሉ አዲስ የሰበካ ጉባዔ አባላትን መምረጥ የነበረ ሲሆን፣ ይህንኑ ጉዳይ ያስፈጽም ዘንድ ቀደም ተብሎ የተዋቀረውና ሦስት አባላት ያሉት የሰበካ ጉባዔ አስመራጭ ኮሚቴ፣ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ከካህናት አንድ እጩ ከምእመናን አስር እጩዎችን ለምርጫ አቅርቧል፡፡ ኮሚቴው እጩዎችን ስለአቀረበበት የአሠራር ሂደት አጠር ያለ ማብራሪያ በመስጠት እጩዋቹን ለጉባዔው በማስተዋወቅ ፣ ግልጽ እና ሥርዓት ባለው መልኩ ስድስት አባላትን በካርድ አስመርጧል፡፡በነበረውም  የድምጽ አሰጣጥ ሂደትም ባገኙት ድምጽ መሠረት ስድስቱ አባላት ተመርጠዋል እነሱም አቶ ይልማ ዘርአይ ፣ አቶ ዘርያዕቆብ መንገሻ ፣ አቶ ዳዊት ሰሎሞ ፣ አቶ አማኑኤል ከበደ ፣ ወ/ሮ መሰረት ገ/መድህንወ ወ/ሪ መአዛ ሲሳይ ሲሆኑ ቀሪዎቹ እጩዎች ደግሞ በተጠባባቂነት ተይዘዋል። በምርጫው ውጤት መሠረትም ስድስቱ  ተመራጮች ለሚቀጥሉት ሁሉት ዓመታት የደብሩ የሰበካ ጉባኤ አባላት ሆነው ያገለግላሉ::  የምርጫውን ውጤት ለማጸደቅም  ወደ ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት እንደሚላክ የታወቀ ሲሆን፣ የአስመራጭ ኮሚቴውም የርክክቡን ሥራ ከአስፈጸመ በኋላ ለሰበካ ጉባዔ ሪፖርት በማቅረብ ሥራውን ያጠናቅቃል፡፡ በጉባዔው መጨረሻም ለነባሩና ለአዲሱ የሰበካ ጉባዔ አባላት ጸሎት ተደርጓውል፡፡ በመጨረሻም የመላው አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሙሴ ጸሎተ ምህላ እንዲደረግ ያስተላለፉትን በደብሩ አስተዳዳሪ በመጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ አማካኝነት  ለጉባኤው ተሳታፊዎች ከተገለጠ በኋላ  በጸሎት ተዘግቷል፡፡ ቀጣዩ ሁለተኛው ክፍል ጠቅላላ ጉባዔ ከአንድ ወር በኋላ የሒሳብ ሪፖርት፣  እና የ2009 ዓ.ም ዕቅድን በማካተት እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡

[/CBC]
share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *