በሶፊያ ባህል ማዕከል ልዩ ዐውደ ጥናት ተካሄደ

በሶፊያ ባህል ማዕከል ልዩ ዐውደ ጥናት ተካሄደ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፊንላንድ ሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እና በፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሶፊያ ባህል ማዕከል ትብብር ቅዳሜ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በሶፊያ የባህል ማዕከል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትን እና የቅዱስ ያሬድን ዜማ በሚመለከት ልዩ ዐውደ ጥናት ተካሄደ፡፡ በዐውደ ጥናቱም ላይ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ለማ በሱፈቃድ፣ የአጥቢያው ምእመናን፣ የፊንሽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባቶች እና የሀገሪቱ ዜጎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

በመጀመሪያ ገዳማዊ ሕይወት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሚል ርዕስ የገዳማዊ ሕይወት አጀማመር፣ ያበረከተው አስተዋጽዖ እና ወቅታዊ ፈተናዎች (ችግሮች) በሚመለከት የተዘጋጀ ጥናታዊ ጽሑፍ በዲያቆን ዶክተር ሰሎሞን አበበ ተዘጋጅቶ  ቀርቧል።  ኢትዮጵያ ክርስትናን በኢትዮጵያዊው ጃንደረባ አማካኝነት እንደተቀበለች  እና በንጉሥ ኢዛና ዘመነ መንግሥት በ340 ዓ.ም አካባቢ ክርስትና የኢትዮጵያ ብሄራዊ ሃይማኖት እንደሆነ በጥናቱ ላይ ቀርቧል፡፡ ገዳማዊ ሕይወትም ክርስትናን ተከትሎ በ4ኛው እና በ6ተኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ ወደ ኢትዮዽያ በገቡ 9ኙ ቅዳሳን ገዳማዊ ሕይወት እንደተመሠረተ እና  እነዚህ አባቶች ስለ መሠረቷቸው ገዳማት፤ የእነርሱን አርአያ በመከተል የኢትዮጵያዊያን አባቶችም ታላላቅ ገዳማትን እንደመሠረቱና በየዘመኑ ከሚነሱ ነገሥታት እና ወራሪ ሃይሎች ያጋጠማቸውን ችግር ተቁዋቁመው ገዳማዊ ሕይወትን ጠብቀው እንዳቆዩልን ተገልጿል። በጥናቱ ላይ  የገዳማዊ ሰው አለባበሱ፣ አመጋገቡ፣ የጸሎት ሰዓት፣የሚጸለዩ ጸሎቶች፣በአጠቃላይ ሕይወቱ ምን እንደሚመስል በአጭሩ ቀርቧል፡፡  እንዲሁም የገዳም የአስተዳደር ተዋረድ፣ የገዳም ሕይወት የሥራ ክፍፍልም ተብራርቷል። ጥናት አቅራቢው  ገዳማት ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  ኅብረተሰብን በማስተማር፣ የሀገርን ቅርስ ጠብቆ በማቆየት፣ ክርስትናን በሥራ በመስበክ እና በማስተማር፣ ሀገር አቀፍ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ አስታራቂ፣ የቱሪስት መስህብ በመሆን ያበረከቱትን አስተዋጽዖ ከገለጹ በኋላ ገዳማት ያለባቸው ወቅታዊ ችግሮች በአጭሩ ዳስሰው ጽሑፋቸውን አጠናቀዋል።

በመቀጠልም ጥናታዊ ጽሑፋቸውን ያቀረቡት ቀሲስ ዶክተር  አምሳሉ ተፈራ የቅዱስ ያሬድን ዜማ በሚመለከት ሲሆን፣ በጥናታዊ ጽሑፉ መግቢያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ታሪክ፣ አስተዳደር እና ቤተ ክርስቲያኗ ለዓለም እና ለአፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ኅብረት ያደረገችውን አስተዋጽኦ  አቅርበው፥ ቤተ ክርስቲያኗን በሚመለከት ባቀረቡት አኀዛዊ መግለጫም ከ45 ሚሊዮን በላይ ምእመናን፣ 400 ሺህ ካህናት እና ዲያቆናት ፥35000 አብያተ ክርስቲያናት፣ 2000 ገዳማት፣ በሀገር ውስጥ 48 እንዲሁም በውጪ ሀገር 13 በአጠቃላይ 61 ሀገረ ስብከቶች እንዳሏት ተጠቅሷል፡፡

የቅዱስ ያሬድን ሥራዎች በተመለከተም፣ በአፄ ገብረ መስቀል የአክሱም ዘመነ መንግሥት  (እ.ኤ.አ 534 – 548) ቅዱስ ያሬድ ዜማን በመድረሱ በምልክት የተጻፈ ዜማን በመጠቀም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን ቀደምት እና ብቸኛ ቤተክርስቲያን እንደሚያደርጋት ተጠቅሷል፡፡በታሪከ ነገሥት እንደተጻፈውም ቅዱስ ያሬድ ከአፄ ገብረ መስቀል እና ከአባ አረጋዊ ጋር ወደ ደቡብ ጎንደር በመጓዝ ዝማሬ እና መዋስዕትን ያስተምር እንደነበር በቀረበው ጽሑፍ ላይ ተገልጿል፡፡

ቅዱስ ያሬድ ያበረከታቸውን ዋና ዋና አስተዋጽኦዎች በሚመለከትም ቅዱስ ያሬድ ዜማ ከመድረሱ በፊት ቤተ ክርስቲያኗ ስትጠቀምበት የነበረው ውርድ ንባብ እንደነበር እና ዜማ በመድረሱም ማህኅሌታዊ ያሬድ በመባል እንደሚጠራ የተገለጸ ሲሆን፣ ከገነት በመጡ ወፎች አማካኝነትም ግዕዝ፣ ዕዝል እና አራራይ ዜማዎችን እንደደረሰ እንዲሁም ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬ እና መዋስዕት የተባሉ አምስት መጸሐፍትን እንደጻፈ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም የዓመቱን የምሥጋና መዝሙሮች በወቅት፣ በሰንበታት እና በክብረ በዓላት ከፋፍሎ ማዘጋጀቱ፤ የዓቢይ ጾም ሳምንታትን መሰየሙ እንዲሁም የቅኔ መሥራች መሆኑ ቅዱስ ያሬድ ካበረከታቸው አስተዋጽኦዎች ውስጥ ለአብነት እንደሚጠቀሱ በጥናታዊ ጹሑፍ ተጠቅሷል፡፡ ለቅዱስ ያሬድ መታሰቢያም ገዳማት እና አብያተ ክርስቲያናት በስሙ እንደተሰየሙለት እና በየዓመቱ ግንቦት 11 እንደሚዘከር ተገልጿል፡፡

ጥናታዊ ጽሑፎቹ ከቀረቡ በኋላ ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ቀርበው፣ በተጠየቁት ጥያቄዎች ላይ በአቅራቢዎቹ ማብራሪያና ምላሽ ተሰጥቶ  ዐውደ ጥናቱ ተጠናቋል፡፡

በዕለቱ የደብሩ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እና ሕጻናት ያሬዳዊ ዜማ ለጉባኤው አቅርበዋል። ተሳታፊዎችም በመዝሙር እንደተደሰቱ ገልጸው የተዘመሩትን መዝሙራት እና የአዘማመር ስልቱን በማንሳት ጥያቄዎችን አንስተው በጥናት አቅራቢዎች እንዲሁ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።  ወደፊትም ተመሳሳይ ዐውደ ጥናት እንደሚቀርብ ለማወቅ ተችሏል።

የሶፊያ ባህል ማዕከል ልዩ ዐውደ ጥናት 2009ዓ.ም.

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *