ዕለተ ሐሙስ

ዕለተ ሐሙስ

ይህ ዕለት በቤተ ክርስቲያን የተለያዩ ስያሜዎች ያሏቸው በርካታ ድርጊቶች የተፈጸሙበት ዕለት ነው፡፡

ሕፅበተ እግር 

ጌታችን በዚህ ዕለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ወንጌሉ እንዲህ ይላል ‹‹እራትም ሲበሉ ዲያብሎስ በስምዖን ልጅ በአስቆሮቱ በይሁዳ ልብ አሳልፎ እንዲሰጠው ዐሳብ ካገባ በኋላ ኢየሱስ ከራት ተነሣ፤ ልብሱንም አኖረ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤ በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ የደቀመዛሙርቱን እግር አጠበ፡፡›› ዮሐ.13፥1-10

የምስጢር ቀን ይባላል
ከሰባቱ ምስጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷልና፡፡ ይኸውም «ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፡፡ እንካችሁ ብሉ» ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ «ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱም ጠጡ» በማለት፤ እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱ ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምስጢር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ፣ ለደቀመዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡

ጸሎተ ሐሙስ ይባላል
የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ፣ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው እስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡(ማቴ.26፤36-46፣ ዮሐ.17)

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ይባላል
ምክንያቱም መሥዋዕተ ኦሪት ማለትም በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ፣ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ «ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፡፡ ከእርሱ ጠጡ» በማለቱ ይታወቃል (ዮሐ 6) ኪዳን ማለት በሁለት ወገን መካከል የሚደረግ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት ጌታችን ለአዳምና ለልጆቹ ሁሉ ዘለዓለማዊውን ቃል ኪዳን በራሱ ደም የፈጸመበት ዕለት ስለሆነ የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ ተባለ፡፡

የነጻነት ሐሙስ ይባላል፡፡
ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ የሰው ልጅ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር «ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታዉ የሚያደርገውን አያውቅምና ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ» በማለት(ዮሐ. 05.05)፤ ከባርነት የወጣንበት ልጆች የተባልንበትን ቀን የምናስብበት በመሆኑ ሊቃውንቱ የነጻነት ሐሙስ አሉት፡፡

እያንዳንዱ ክርስቲያንም ከኃጢአት ባርነት ርቆ፣ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያወዳጀውን መልካም ሥራ በመሥራት ሕይወቱን መምራት ይኖርባታል፡፡ ባሮች አልላችሁም ተብለናልና፡፡

ለብርሃነ ትንሣኤው አምላካችን በሰላም ያድርሰን፡፡
ይቆየን፡፡

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *