ነገረ ማርያም

ነገረ ማርያም

ርዕሱን ወደተመለከተው ወደ ዋናው ትምህርት ከመግባታችን አስቀድሞ የርዕሱን ትርጉም ማወቅ ይቀድማልና ነገረ ማርያም የሚለውን ትርጉም እናያለን። ነገረ ማርያም ማለት የእመቤታችንን ነገር (ስለ እመቤታችን) የሚያወሳ ነገር ወይም ትምህርት ማለት ነው። ይህም አስቀድማ በአምላክ ሕሊና መታሰቧን፣ ትንቢት የተነገረላት፣ ምሳሌ የተመሰለላት መሆኗን፣ ልደቷን፣ እድገቷን፣ አምላክን ፀንሳ መውለዷን ዕረፍቷን፣ ትንሣኤዋን ወዘተ የሚተርክ የሚያስተምር ነው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ማርያም በሚል ስም የሚጠሩ ብዙ ሴቶች አሉ። እነዚህም በብሉይና በሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ ተጠቅሰው ይገኛሉ። እነርሱም፡-

1ኛ. የሙሴ እህት ማርያም፡- ይህች ማርያም ሙሴ በወንዝ ዳር በተጣለ ጊዜ በእርሱ ላይ የሚሆነውን ነገር ስትከታተል ነበር። ዘፀ.2፥4-8
– እስራኤል ባሕረ ኤርትራን ሲሻገሩ ከበሮ በመያዝ በመዝሙር እግዚአብሔርን አመስግናለች። ዘፀ. 15፥20-22
2ኛ. የዕዝራ የልጅ ልጅ (የዬቴር ልጅ) ማርያም 1ኛ. ዜና. 4፥17
3ኛ. የማርታና የአልዓዛር እኅት ማርያም ዮሐ. 11፥1
– ክርስቶስ ወደ ቤታቸው እየሄደ ይጎበኛቸው ያስተምራቸው ነበር።
– ቃሉን ለመስማት ትተጋ ስለነበር ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አመስግኗታል። ሉቃ. 10፥39-42
-ጌታን ሽቱ ቀባችው እግሩንም በጠጉርዋ አበሰችው። ዮሐ. 11፥2፣ ዮሐ.12፥1-8
4ኛ. መግደላዊት ማርያም
– ክርስቶስ ሰባት አጋንንትን አወጣላት። ሉቃ. 8፥2
– ከትንሣኤው በኋላ በአትክልት ቦታ ለእርሷ ለብቻዋ ታያት ተገለጠላት። ዮሐ. 20፥1-8
5ኛ. የታናሹ የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም ማር. 15፥40
6ኛ. የቀለዮጳ ሚስት ማርያም- ጌታ በተሰቀለ ጊዜ ከመስቀሉ አጠገብ ቆማ ነበር። ዮሐ. 19፥25
7ኛ. የማርቆስ እናት ማርያም ሐዋ. 12፥12
8ኛ. የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ቅድስት ድንግል ማርያም።
ከላይ የተዘረዘሩት ማርያም በሚል ስም የተጠሩ ሴቶች እንዳሉ ለማመልከት እንጂ ስለ ሁሉም ለመተረክ ተፈልጎ አይደለም። ከዚህ በኋላ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን ስለወለደች ስለቅድስት ድንግል ማርያም እንፅፋለን።

ሀ) የእመቤታችን መወለድ (ልደታ ለማርያም)
የወደቀው ሰው ከውድቀቱ ይነሳ፣ ከርኩሰቱ ይቀደስ ዘንድ አምላክ ከእርሷ እንዲወለድ የወላዲተ አምላክ የአማናዊው ፀሐይ የክርስቶስ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት ግድ ነበር። ስለዚህም ነው “እግዝእትነ ማርያም ነበረት እምቅድመ ዓለም በሕሊና አምላክ” (እመቤታችን ማርያም ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ልቡና ታስባ ትኖር ነበር) የተባለው።

በመጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ እንደምናገኘው ብዙ ሰዎች ልጅ በማጣት አዝነው እግዚአብሔርን ፀንተው በመለመን ልጅ ያውም ታላላቅ ልጆችን እንዳገኙ እናነባለን። እንዲያውም አንዳንዶቹ ካረጁና የመውለጃ ጊዜአቸው ከተላለፋቸው በኋላ ነው ልጅ የሚያገኙት። የሳራና የአብርሃም፣ የኤልሳቤጥና የካህኑ ዘካርያስ፣ የሐና እና የሕልቃና ወዘተ. ታሪክ ለዚህ ማስረጃ ይሆነናል። ዘፍ. 21፥1-8፣ ሉቃ. 1፥8-23፣ ሉቃ. 1፥57-67፣ 1ኛ ሳሙ. 1፥1-21። የእመቤታችን እናት ሐና እና አባቷ ኢያቄም ከላይ እንዳየናቸው ሁሉ መካን ሆነው ይኖሩ ነበር። በኋላ ግን ለሳራና አብርሃም ይስሐቅን፣ ለኤልሳቤጥና ዘካርያስ መጥምቀ መለኮት ዮሐንስን፣ ለሐና እና ለሕልቃና ሳሙኤልን የሰጣቸው እግዚአብሔር ለሐና እና ለኢያቄምም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ሰጣቸው።

እመቤታችን ነሐሴ 7 ቀን ተፀነሰች። ገና በማሕፀን ሳለችም አንድ ዓይነ ስውር ዘመዷ ኤልሳቤጥ ፀነሰች ቢሏት ዳስሼ ካላረጋገጥኩ አላምንም ብላ የሐናን ሆድ ነክታ መፅነሷን ስታረጋግጥ በአድናቆት እጇን ዓይኗ ላይ ብታደርገው በሐና ማሕፀን ያለችው የአምላክ እናት ናትና የዓይነ ስውሯ ዓይን በራላት። የሞተ ሰው ይዘው ሲሄዱ የሐና ጥላ በሙቱ ላይ ሲያርፍ የሞተው ሰው ተነስቷል። ከዚህ በኋላ ግንቦት 1 ቀን በሊባኖስ ተራራ ተወለደች። የእመቤታችን የዘር ሐረግ በአባቷ ከነገደ ይሁዳ በእናቷ ደግሞ ከነገደ አሮን ነው።

ለ) እመቤታችን ወደ ቤተ መቅደስ መግባት (በአታ ለማርያም)

በአታ ለማርያም ማለት የማርያም ወደ ቤተ መቅደስ መግባት ማለት ነው። እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከእናት ከአባቷ ጋር አብራ የኖረችው ለሦስት ዓመታት ብቻ ነው። የብፅዓት ልጅ ናትና ሦስት ዓመት ሲሆናት እናትና አቧቷ በስእለታቸው መሠረት ለእግዚአብሔር ቤት ለመስጠት ወደ ቤተመቅደስ ወሰዷት። በጊዜው የነበረው ሊቀ ካህን ዘካርያስ ነበርና ወደ ዘካርያስ አቀረቧት። እርሱም ምን እንደሚያደርግ ግራ ገብቶት ሳለ የእግዚአብሔር መልአክ ቅዱስ ፋኑኤል ፅዋአ ሰማያዊ ኅብስት ሰማያዊ ይዞ ወረደ። ዘካርያስ፣ ካህናቱ ኢያቄምና ሐና ወደ መልአኩ ቢቀርቡ እርሱ ግን ራቃቸው የመጣው ለእነርሱ አይደለምና። እመቤታችንን ብቻዋን ሲተዋት ግን መልአኩ ወርዶ በክንፎቹ ጋርዶ መግቧት አርጓል። ዘካርያስም የሆነውን ሁሉ አይቶ ፈቃደ እግዚአበሔር መሆኑን ተረድቶ ከቤተ መቅደስ አስገብቷታል።

እመቤታችን በቤተመቅደስ የኖረችው ለአሥራ ሁለት ዓመት ሲሆን ከዚህ በኋላ አይሁድ ቤተመቅደሳችንን ታረክሳለችና ትውጣ ብለው ቢያምፁ ዘካርያስ አይሁድ እንዲህ አሉ ምን ላድርግ አላት። እመቤታችንም እኔ ምን አውቃለሁ አለችው። ወደ እግዚአብሔር ቢያመለክት ከነገደ ይሁዳ ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን ወንዶች በትር ሰብስበህ ከቤተመቅደስ አስገብተህ ጸልይበት እኔም ምልክት እሰጥሀለሁ አለው። ዘካርያስም እንደተባለው በትር ላይ “ዮሴፍ ሆይ ማርያምን ጠብቃት” የሚል ምልክት ሰጠው ዕጣ ቢጣል ለዮሴፍ ወጣ ርግብም በዮሴፍ ራስ ላይ አረፈች። በእነዚህ ሁሉ ምልክቶች ተረድቶ ካህኑ ዘካርያስ እመቤታችንን ለዮሴፍ ሰጣት። ይህ ሁሉ የሆነው በጥበበ እግዚአብሔር ነው። በብሉይ ኪዳን ህግ አንዲት ሴት ያለ ባል የፀነሰች እንደሆነ በድንጋይ ተወግራ በእሳት ተቃጥላ ትገደል ነበርና እመቤታችን ይህ ሞት እንዳያገኛት በእጮኛ ስም ለዮሴፍ ተሰጠች። እመቤታችን በሄሮድስ ምክንያት የሚደርስባት ስደትና መከራ አለና ረዳቷና ጠባቂዋ እንዲሆን ለዮሴፍ በእጮኝነት ስም ተሰጠች። ኃይል አርያማዊት አለመሆኗ ከአዳም ዘር የተገኘች ሰው መሆኗ ይገለጥ ይታወቅ ዘንድ ለዮሴፍ በእጮኝነት ስም ተሰጠች።

ሐ) አምላክን መውለዷ

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ለማሕደረ ሥሉስ ቅዱስ አስቀድማ ተመርጣለችና እግዚአብሔር አብ ለአፅንኦ (ለማፅናት) እግዚአብሔር ወልድ ለተሰብኦ (ሰው ለመሆን) እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ለአንፅሖ (ሊያነፃት) አድረውባታል። በተለይ እግዚአብሔር ወልድ በተለየ አካሉ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ ረቂቁ መለኮት ግዙፉን ሥጋ ተዋሐደ አምላክ ሰው ሰውም አምላካ ሆነ። እመቤታችን ደግሞ ይህ ታላቅ ምስጢር የተከናወነባት ሙዳየ ምሥጢር ሆነች። ይህ ምሥጢር በእመቤታችን ማሕፀን ሲከወን በፍፁም ድንግልና ነው። ይህም ማለት እመቤታችን ከመፅሷ በፊት፣ በፀነሰችም ጊዜ፣ ከፀነሰችም በኋላ እንዲሁም ከመውለዷ በፊት በወለደችም ጊዜ ከወለደችም በኋላ “ወትረ ድንግል” ሁሌም ፍፁም ድንግል ናት። ሕዝ.44፥1-4፣ ኢሳ.7፥14።

የፀሐይ ብርሃን በመስታወት ሲገባ ተመልሶም ሲወጣ የሰው መልክ በመስታወት ውስጥ ሲታይ መስታወቱን እንደማይሰብረውና በመስታወቱ ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ እንደማይታይ እመቤችንም ጌታን ፀንሳ ስትወልድ ማሕተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም በፍፁም ድንግልና ፀንሳ በፍፁም ወልዳዋለች በዚህ ክብሯም ከአንስተ ዓለም ሁሉ ትለያለች። ሌሎች ሴቶች አንዱ ብቻ ይኖራቸዋል እንጂ ሁለቱንም አስተባብረው መያዝ አይቻላቸውም። ይህም ማለት ድናግል የሆኑ ሴቶች በመውለድ የሚገኘው እናትነት ሊኖራቸው አይችልም፤ እንዲሁም በመውለድ እናት የሆኑ ሴቶች ደናግል ተብለው ሊጠሩ አይችሉም፤ ደናግል ሴቶች እያጠቡም ወተትም የላቸውም። እመቤታችን ግን እናነትን ከድንግልና ሐሊብን (ወተትን) ከድንግልና ጋር አስተባብራ የያዘች ናትና ከሴቶች ሁሉ የተለየች ናት። ሌሎች ሴቶች ቢወልዱ ነቢያትን፣ ሐዋርያትን፣ ፃድቃንን፣ ሰማዕታትን ነው እመቤታችን ግን ለእነዚህ ሁሉ አምላካቸው የሆነውን ክርስቶስን ወልዳለችና ክብሯ ልዩ ነው ከሴቶች ሁሉም የተለየች ናት።

መ) ዕረፍታ ለማርያም (የእመቤታችን ዕረፍት)

እመቤታችን በዚህ ዓለም የኖረችበት ዕድሜ 64 ዓመት ነው። ይኸውም 3 ዓመት በእናት በአቧቷ ቤት፣ 12 ዓመት በቤተ መቅደስ፣ 34 ዓመት በቤተ ዮሴፍ፣ 15 ዓመት በቤተ ዮሐንስ ኖራለች። ከዚህ በኋላ ከእርሷ አስቀድሞ የማይሞተው ልጇ ሞትን ይሽረው ዘንድ ሞቷልና እመቤታችንም ጥር 21 ቀን አረፈች። “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የአፅብ ለኵሉ” (ሞት ለሰው (ለሟች) ሁሉ ይገባል የተገባ ነው የማርያም ሞት ግን ለሁሉ ያስደንቃል) እንዳለው ሊቁ የእመቤታችን ሞት አስደናቂ ነው። አምላክ በማሕፀንዋ የተሸከመች፣ ሙታንን የሚያነሳ ልጅ ያላት እና ለሕዝቡ ሁሉ መድኃኒት የሆነውን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ ማንኛውም ሰው ሞተች። ሊቀብሯት ይዘዋት ሲሄዱም አይሁድ አይተው ከዚህ በፊት ልጇን ሞተ ተነሳ እያሉ ከተማችንን አወኩ አሁንም እናቱን ሞተች ተነሳች ሊሉ አይደለምን ብለው የእመቤታችንን ሥጋ ሊያቃጥሉ መጡ ከመካከላቸውም ታውፋንያ የሚባል አንድ ሰው የእመቤታችንን የአልጋዋን ሸንኮር ይዞ ወደ መሬት ሊጥልና ሊያቃጥል ሲል ሁለቱም እጆቹ ተቀሰፉ ለማስተማር የተደረገ ተአምር ነውና በኋላ በእመቤታችን አማካኝነት ሁለቱም እጆቹ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ሆነዋል። የእመቤታችን ሥጋም በገነት በእፀ ሕይወት ሥር የተመለከተው ዮሐንስ ወንጌላዊው ብቻ ነበርና ሌሎች ሐዋርያት እኛ የእመቤታችንን ሁኔታ ሳናይ አግኝተን ሳንቀብራት ብለው ሱባኤ ያዙ። ሁለተኛውን ሱባኤ እንዳገባደዱ የእመቤታችንን ሥጋ ሰጣቸው። ይህም ማለት ነሐሴ 14 ማለት ነው እነሱም የእመቤታችንን ስጋ በክብር ቀበሩ። የእመቤታችንን ሥጋ አግኝተው ሲቀብሩ በመካከላቸው ቶማስ አልነበረም። ሆኖም ግን በሦስተኛው ቀን ማለትም ነሐሴ 16 ቀን ተነስታ ስታርግ ቶማስ ከሀገረ ስብከቱ በደመና ተጭኖ ሲመጣ ተገናኙ። እሱም ቀድሞ የልጅሽን ትንሳኤ አሁን ደግሞ ያንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ ብሎ በመንፈሳዊ ቅናት ተበሳጨ። እመቤታችንም የእርሷን ትንሣኤ ሌሎች ሐዋርያት እንዳላዩ ነግራና ምልክት ይሆነውም ዘንድ የተገነዘችበትን ሰበን ሰጥታ መነሳቷን ለሌሎቹ ሐዋርያት እንዲያበስር ነግራው አረገች። ሐዋርያትም በዓመቱ ቶማስ ትንሣኤዋን አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በመንፈሳዊ ቅናት ሱባኤ ቢገቡ ትንሣኤዋን ነሐሴ 16 ቀን ማየት ችለዋል። ስለሆነም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞታ ፈርሳ በስብሳ አልቀረችም እንደ ልጇ ተነስታ አርጋለች።

ልመናዋ ክብሯ በሁላችን ይደርብን
የእመቤታችን አማላጅነት
ለሁላችን ይደረግልን
አሜን

source: http://www.sturaelmb.org/

share

Comments

  1. yisfazer kebede : February 6, 2018 at 5:25 pm

    ቃለ ህይወት ያሰማለን

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *