ቀዳሚት ሥዑር

ቀዳሚት ሥዑር

በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሠ መቃብር አድሮ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሚት ሥዑር » ትሰኛለች፡፡ ቀዳሚት ሥዑር የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ሚጾምባት ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ። አልቀመሱም ፡፡ አምላካቸው በመቃብር ስላደረ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም ውለዋል።

ከቅዱሳን ሐዋርያት ሲወርድ ሲወራረድ በመጣው ትውፊት መሠረት ቅዱሳን ሐዋርያት በማዘን በመጾምና በመጸለይ ዕለቷ እንዳከበሯት የተዋሕዶ ልጆች የተቻላቸው ከዓርብ ጀምረው የሚያከፍሉ /የሚጾሙ/ ለሁለት ቀን እህል ውኃ ሳይቀምሱ ያድራሉ ያልተቻላቸው ደግሞ ዓርብ ማታ ቀምሰው ቅዳሜን በመጾም/ በማክፈል ትንሣኤን ያከብራሉ፡፡

ለምን ቄጠማ ይታደላል?

በዚህ ዕለት ከሰኞ ከሆሣዕና ማግሥት ጀምረው እስከ ስቅለተ ዓርብ ድረስ በስግደት እና በጾም ያሳለፉ ምእመናን በዕለተ ቅዳሜ በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ፡፡ የጠዋቱ ጸሎት ሲፈጸም ካህናቱ «ገብረ ሰላመ በመስቀሉ፡-በመስቀሉ ሰላምን መሠረተ» የምሥራች እያሉ በቤተ ክርስቲያን ለተሰበሰቡት ምእመናን ቄጠማ ይታደላል ቄጠማው የምሥራች ምልክት ነው፡፡ ቄጠማው የምሥራች ምልክት ተደርጐ የተወሰደው በኖህ ዘመን ከተፈጸመው ታሪክ ጋር በማያያዝ ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን በጻድቁ ኖኅ ዘመን የነበሩ ሕዝቦች ከሕገ እግዚአብሔር ውጪ ሆነው እጅግ የሚያሳዝን ኃጢአት በሠሩ ጊዜ በንፍር ውኃ ተጥለቅልቀው ጠፍተዋል።በወቅቱ ጻድቁ ኖኅ ወደ መርከብ ይዞአቸው ከገባው እንስሳት መካከል የውኃውን መጉደል ለመረዳት ርግብን በመርከብ መስኮት አሾልኮ ይለቃታል፤ እርሷም ውኃው ጎደለ ስትል ቄጠማ በአፍዋ ይዛ ትመለሳለች፡፡ ዘፍ.9-1-29፡፡ ኖኅም በዚህ ቄጠማ የውኃውን መድረቅ ተረድቶ ተደስቷል፡፡

«ቄጠማ»፣ ለጥፋት ውኃ መድረቅ የምሥራች ማብሠሪያ እንደሆነ አሁንም በክርስቶስ ሞት ሞተ ነፍስ ከሰው ልጆች ተወገደ ስትል ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ቄጠማ ታድላለች፡፡ ምእመናንም የምሥራች ተምሳሌት የሆነውን ቄጠማ በግንባራቸው ያስሩታል፡፡

የተዋሕዶ ልጆች ሁሉ ከጨለማ ወደ ብርሃን ፥ዋዕየ ሲኦል /የሲኦል ቃጠሎ/ ወደ ልምላሜ ገነት ጥንተ ማደሪቸው መመለሳቸውን በዚህ መልክ እየገለጡ በዓለ ትንሣኤን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ያከብራሉ፡፡

መልካም የትንሣኤ በዓል ይሁንልን ።

Source : www.eotc-mkidusan.org

share

Comments

  1. Amen kale hiweten yasemalen

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *