ሥርዓተ ዕለተ ስቅለት

ሥርዓተ ዕለተ ስቅለት

ዕለተ ዓርብ ነግህ

ዕለተ ዓርብ የአዳምን ነጻነት ለመመለስ የአዳምን ዕዳ በደል አምላካችን የተሸከመበት ዕለት የኀዘን ዕለት የድኅነት ዕለትም ነው፡፡ በዚሁ ዕለት ሁሉም ነገር እንደተለመደው ይከናወናል:: መሪው እዝል ይመራል ሕዝቡ ይከተላል አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሀሉ ወጸቢሖ ተማከሩ ሊቃነ ካህናት፤ ሲነጋም ሊቃነ ከህናት ተማከሩ የሚለው ዜማ በመሪ በተመሪ በሕዝብ ተሰጥዎ ይከናወናል፡፡ ምንባቡም ስግደቱም ድጓውም እንደ አለፈው ይቀጥላል፡፡
በሦስት ሰዓት

ሥዕለ ስቅለቱ መስቀሉ ወንጌሉ መብራቱ ጽንሐሑ በመቅደሱ በር ላይ ይዘጋጃል ዲያቆኑ በቃለ ማኅዘኒ በሚያሳዝን ቃል ግፍኦሙ እግዚኦ ለእለ ይገፍኡኒ ይላል፡፡ ካህናቱም ምእመናኑም በዜማ እየተቀበሉ ይሰግዳሉ፡፡ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ፡፡ በየመሀሉ የሰዓቱ ድጓ ይቃኛል፡፡
ስድስት ሰዓት

የዕለቱ መሪ እዝል ይመራል፡፡ ሦስቱ ካህናት ጽንሐሑን ይዘው ከርቤ እያጠኑ ዲያቆናት መብራት እያበሩ ለመስቀልከ ንስግድ እያሉ ያዜማሉ ምእመናን ዜማውን እየተቀበሉ ይሰግዳሉ፡ ከዚያም ዲያቆኑ ቀነውኒ እደውየ ወእገርየ የሚለውን ምስባክ ሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ በየመሀሉ ድጓው ይዜማል፡፡ከዚህ ቀጥሎ ምእመናን ይቀመጣሉ ሦስቱ ካህናት ጥቁር ልብስ ለብሰው በሚያሳዝን ዜማ አምንስቲቲ ሙኪርያ አንቲ ፋሲልያሱ ፤ጌታዬ ሆይ ስለ እኔ ሞትህ ወዮ እኔ ልሙትልህ እያሉ ሦስት ጊዜ ያዜማሉ፡፡ ሕዝቡ ይቀበላል በዚያው አያይዘው ተዘከረነ እግዚኦ በውስተ መንግሥትከ እያሉ በዜማ ይጸልያሉ ሕዝቡ ይቆማል ሥርዓተ ስግደቱም ይከናወናል፡፡

በዘጠኝ ሰዓት

ሌላው እንደተለመደው ሆኖ ኦ ዘጥዕመ ሞተ በሥጋ ሦስት ጊዜ ካህናቱ በዜማ ይሉታል ምእመናንም ይቀበላሉ፡፡ ምስባክ ተሰብኮ አራቱ ወንጌላት ይነበባሉ ስግደት እንደተለመደው ነው፡፡ በሦስት ሰዓት፣ በስድስት ሰዓት፣ በዘጠኝ ሰዓት፣ ወንጌላቱ ተነበው እንዳለቁ ለምእመናን ትምህርተ ወንጌል ይሰጣል፡፡ ይህ ግን እንደ ቋሚ ሥርዓት ሳይሆን እንደ ሁኔታው አመቺነት ነው፡፡

አሥራ አንድ ሰዓት

ካህናት በአራቱ መዕዘን ቁመው አራት መቶ እግዚኦታ ያደርሳሉ፤ ዕለቱን የሚመለከቱ መዝሙራት ተመርጠው ይነበባሉ፡፡ ንሴብሖ እየተባለ ቤተ መቅደሱን በመዞር በከበሮ በጽናጽል በሕማሙ ያዳነን እግዚአብሔር ይመሰገናል፡፡ ዑደት የሚደረገው ሥነ ስቅለቱን በመያዝ ነው፡፡ ምእመናንም በካህናቱ በወይራ ቅጠልም ቸብ ቸብ ይደረጋሉ የመከራው ተሳታፊዎች መሆናቸውን ለመግለጥ ነው፡፡ ወይራ ጽኑዕ ነው የተቀበልከው መከራም ጽኑዕ ነው እኛም ይህን መከራ ለመቀበል ዝግጁ ነን ለማለት ነው፡፡ እንዲሁም ምእመናን በካህናቱ በታዘዙት መሠረትም ሰግደታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡

ከዚያ በኋላ በካህኑ ኑዛዜ ምእመናን ወደ የቤታቸው ይሰናበታሉ፡፡ መስቀል መሳለም አሁንም የለም የቻለ ከሐሙስ ጀምሮ አሊያም ከዓርብ ማታ ጀምሮ እስከ ዕለተ ትንሣኤው ድረስ ያከፍላል /ይጾማል/ የተጀመረውም በዕለተ ስቅለቱ በሐዋርያትና በእመቤታችን እንደሆነ አበው ያሰተምራሉ፡፡

Share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *