የመስቀል ደመራ በዓል ለሁለተኛ ጊዜ በሄልሲንኪ ተከበረ

የመስቀል ደመራ በዓል ለሁለተኛ ጊዜ በሄልሲንኪ ተከበረ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በፊንላንድ ሄልሲንኪደብረ አሚን አቡነተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በሄልሲንኪ ከተማ ቅዱስ ዮሐንስ ቤተክርስቲያን አደባባይ የመስቀል ደመራ በዓል ለሁለተኛ ጊዜ ተከበረ። ከባለፈው ዓመት በተለየ መልኩ የደመራ አዘጋጅ ኮሚቴ ተመርጦ ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎ መስከረም 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ከ 17፡30 – 20፡30 በተካሄደው የደመራ ሥነ ሥርዓት ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ በፊንላንድ የሚገኙ የኢትዮጵያውያን እና ኤርትራውያን ምእመናን እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የልዩ ልዩ ቤተ እምነት መሪዎች ፡ የመንግሥት እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ሓላፊዎችና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በበዓሉ ተገኝተዋል፡፡

በደብሩ ካህናትና ዲያቆናት መሪነት ዕለቱን የሚያዘክር ስብሐተ እግዚአብሔር ከደረሰ  በኋላም በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን በዓሉን የሚመለከት ወረብ ቀርቧል፡፡ በመቀጠልም የደብሩ ሰንበት ት/ቤት ለዕለቱ የተዘጋጀውን ወረብ ያቀረቡ ሲሆን በተጨማሪም ለበዓሉ ያዘጋጇቸውን ሌሎች መዝሙራት አቅርበዋል፡፡ የደብሩ ሕጻናት እና አዳጊዎችም በተመደበላቸው ሰዓት በዓሉን በማስመልከት ሰለ መስቀሉ ሥነ ጽሑፍ እና መዝሙራትን ያቀረቡ ሲሆን፣ በበዓሉ ላይ የተገኙ የሀገሪቱን ነዋሪዎችን ታሳቢ በማድረግ ካቀረቧችው መዝሙራት ውስጥ የተወሰኑትን መዝሙራት ትርጉም በፊንላንድኛ ቋንቋ ዘምረዋል።

ደመራው ከመለኮሱ አስቀድሞ፣ ስለ በዓሉ አጠር ያለ ትምህርተ ወንጌል በደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ ባስተላለፉት መልእክትም በፊንላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ምእመናን እንዲሁም የሀገሪቱም ዜጎች የደመራ በዓልን በጋራ ለማክበር መሰባሰባቸውን አድንቀው ወደፊትም ይህ አይነቱ በጎ ምሳሌ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡አያይዘውም በደብሩ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ለመግዛት /ለመሥራት ደብሩ የሕንጻ ግዢ ኮሚቴ አዋቅሮ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው የሁሉም ርብርብ እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቀበዋል ። ስለ መስቀል በዓል ታሪክ እና ስለ ደብሩ ነባራዊ ሁኔታም በተመለከተ በፊንላንድኛ ቋንቋ ጭምር የተዘጋጀ ጽሑፍም ለሕዝቡ ታድሏል ::
በዕለቱ ከተጋበዙት እንግዶች መካከል ከፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የመጡት ቄስ ቴሙ ቶይቮነን የመስቀል ደመራ በዓልን አከባበር ሥርዓትን አድንቀው ወደፊትም በማንኛውም አገልግሎታችሁ እኛም የበኩላችንን አስተዋጸኦ እናበረክታለን ያሉ ሲሆን ፤ሌሎችም የሀገሪቱ ዜጎች እንደተናገሩት ይህ የመስቀል ደመራ በዓል በዚህ መልኩ በሀገራችን በአደባባይ መከበሩ ለሀገራችን የሚያበረክተው አስተዋጻኦ ቀላል አይደለም ብለዋል።

በመቀጠልም በካህናቱና በተጋባዥ የክብር እንግዶች አማካኝነት ደመራው የተለኮሰ ሲሆን፣ ሕዝበ ክርስቲያኑም ደመራውን ከበው በዝማሬና በእልልታ እግዚአብሔርን በማመስገን በዓሉን አድምቀውት አምሽተዋል፡፡በመጨረሻም የደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፈቃድ በዓሉን በተሳካ ሁኔታ ለማክበር አስተዋጽኦ ላደረጉት፣ የደመራ በዓል አዘጋጅ ኮሚቴ፣ ለከተማ መስተዳድሮች፣ ለኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ካህናት እና ምእመናን፣ ለፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በተለያዩ አገልግሎቶች ለተሳተፉ ምእመናን ምስጋና አቅርበው የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል፡፡

 

 

የመስቀል ደመራ በዓል 2017

share

Comments

  1. Leametu beselam yaderesen kezim yebelete endenesera endnakebera Amelake yirdan kefetena hulu yitbeken

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *