በፊንላንድ ሄልሲንኪ ታላቅ የአንድነት እና ሰላም ጉባኤ ተካሄደ

በፊንላንድ ሄልሲንኪ ታላቅ የአንድነት እና ሰላም ጉባኤ ተካሄደ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰሜን ምዕራብ አውሮፓ ሀገረ ስብከት ውስጥ በሚገኘው በፊንላንድ የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ከመስከረም 12 – 13 ቀን 2011 ዓ.ም ታላቅ የአንድነት እና ሰላም ጉባኤ ተካሄደ። በጉባኤው ላይም የአውሮፓ አኅጉረ ስብከት ሊቃነ ጳጳሳት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ቀዳማዊ እና ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ፣ ጥሪ የተደረገላቸው ካህናት፤ ከመላው ፊንላንድ የተሰባሰቡ ምዕመናን እና የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች  ተገኝተዋል። ጉባኤው ቅዳሜ መስከረም 12 ቀን 2011 ጠዋት በሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት እየተመራ በጸሎተ ቅዳሴ ተጀምሯል።

የአንድነት ጉባኤውን ለማድረግ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም በቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር መከፋፈል ምክንያት ለሁለት ተከፍለው የነበሩትን በፊንላንድ የሚኖሩ ምዕመናን አንድ መሆናቸውን ለማብሰር እና ይህንን ላደረገ አምላካችንም ምሥጋና ለማቅረብ እንደሆነ የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ አስረድተዋል። በፊንላንድ ውስጥ በሀገር ቤት ቅዱስ ሲኖዶስ ሲተዳደር የነበረው የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን እና በውጭው ሲኖዶስ በነበረው አስተዳደር ሥር ደግሞ የመድኃኔዓለም ማኅበር እንደነበረ ይታወቃል።

ጸሎተ ቅዳሴው እንደተፈጸመ በመላው ፊላንድ የሚገኙ ምዕመናን በአንድነት ሆነው እስከ አሁን በነበረው መከፋፈል ብፁዓን አባቶቻችን በማሳዘናችን ይቅርታ አድርጉልን ብለው ሁሉም ካህናት ዲያቆናት እና ምእመናን ከብፁዓን አባቶች እግረ መስቀል ሥር በመውደቅ ጠይቀው፤ ሊቃነ ጳጳሳቱም እግዚአብሔር ምሕረት እንዲሰጥ ጸሎት አድርገው የሕዝቡን ይቅርታ ተቀብለዋል። የአውሮፓ አኅጉረ ስብከት ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ዲዮናስዮስ ባስተላለፉት መልእክት ለቤተ ክርስቲያን አንድ መሆን ሲተጉ ለነበሩ ሁሉ ታላቅ ምስጋና በማቅረብ በፊንላን ያሉ ምዕመናንም አንድነታቸው አጽንተው አገልግሎታቸው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል። የአውሮፓ እና አፍሪካ አኅጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ቀዳማዊም በሰጡት ሰፋ ያለ ትምህርትና መመሪያም፤ ከዛሬ ጀምሮ በፊንላንድ ያሉ ምዕመና በአንድነት ሆነው በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት እንዲገለገሉ መመሪያ አስተላለፈዋል። ብፁዕነታቸው ከዚህ በፊት ለአገልግሎት በተለያየ ጊዜ ወደ ፊንላንድ መመላለሳቸውን አውስተው፤ በፊንላንድ ካህናትና ምዕመናን ሁሉ ተባብረው የሚገለገሉበት ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በአስቸኳይ እንዲገዙ እና አገልግሎታቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ አደራቸውን አስተላለፈዋል።

እሑድ መስከረም 13 ቀን 2011 ዓ.ም. በቀጠለው የጉባኤው ክፍልም ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የቤተ ክርስቲያንን አስተዳደር አንድ መሆን በጉባኤው ለተጋበዙ እንግዶች እና ምዕመናን በድጋሜ አብስረዋል። ብፁዕነታቸው ምዕመናንንም በአንድነት ሆናችሁ ለምትበልጠዋ ጸጋ ቅኑ፣ ትጉ በማለት የመገልገያ ሕንፃውን በቶሎው እንዲገዛ እና ሕጻናትን ማስተማር ላይም ትኩረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል። በዕለቱም ከተለያዩ ቤተ እምነቶች የተጋበዙ እንግዶች የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላለፈዋል። በተለይ በዓለም አቢያተ ክርስቲያናት የአፍሪካ አስተዳደር ሐላፊ ዶ/ር ንጉሡ በአባቶች መለያየት ምክንያት የነበረውን አስቸጋሪ ጊዜ ጠቅሰው ሁሉም አልፎ ለአንድነቱ እንኳን በቃችሁ ብለዋል ።ዶ/ር ንጉሡ በአባቶች መካከል የነበረውን ልዩነት ለማስወገድ እና ሰላም ለማምጣት አስታራቂ ኮሚቴ አባል በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ይታወሳል ። የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን ወክለው የተገኙት ቄስ ቴሙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር አንድ መሆን በዓለም ላይ ላሉ ክርስቲያኖች መጠንከር ታላቅ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል። ለዚህ አንድነት ማስታወሻ ይሆን ዘንድ ከፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የተላከውን ስጦታም ለደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ አሚን ቀሲስ ለማ አስረክበዋል።

በጉባኤው ላይ የደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያንም እስከ አሁን መከፋፈላችንን ችለው በሁለቱም ሲኖዶሶች ሥር ለነበሩት ሁሉ የመገልገያ ቦታ በመስጠት ድጋፍ እያደረጉልን ላሉት የፊንላንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እና የሶፊያ የባሕል ማዕከል የማስታወሻ ስጦታን አበርከተዋል።

በተያያዘ ዜና በዚሁ ጉባኤ ላይ የተገኙት ሊቃነ ጳጳሳት የደብሩን አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ለማ በሱፍቃድን “መልአከ አሚን” የሚል የማዕረግ ስም እንደሰጧቸው ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ቀዳማዊ ለጉባኤው አብስረዋል።እንዲሁም ሊቃነ ጳጳሳቱ ደብሩን ሰንበት ት/ቤት “ፅጌ ሃይማኖት “በሚል ስም ሰይመዋል።

Sep 21-23 2018 ድረስ የተዘጋጀው የሰላምና አንድነት ጉባኤ


ዲ.ዓለምነው ሽፈራው

 

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *