ሰባተኛ ዓመት ምሥረታና ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለሃይማኖት በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

ሰባተኛ ዓመት ምሥረታና ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለሃይማኖት በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

ሰባተኛ ዓመት ምሥረታና ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለሃይማኖት በዓል በደማቅ ሁኔታ ተከበረ

በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት የሚከበረው ፍልሰተ ዐፅሙ ለአቡነ ተክለሃይማኖት ዓመታዊ ክብረ በዓል እና የደብሩ ሰባተኛ ዓመት የምሥረታ በዓል በዘንድሮ ዓመት በተለየ ሁኔታ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ በፊንላንድ  የሄልሲንኪ ደብረ አሚን አቡነ ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ቅዳሜ ግንቦት 11 2010 ዓ.ም ተከብሮ ዋለ :: በዕለቱ ታቦተ አቡነ ተክለሃይማኖት ወደ ፊንላንድ የመጣበት እና ደብሩ እንደ አጥቢያ ቤተክርስቲያን  የተመሠረተበት ሰባተኛ ዓመት “ ሃይማኖታችንን ለልጆቻችን ዛሬ እናስተምር” በሚል መሪ ቃል በፊንላንድ ሄልሲንኪ የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ሊቀ ማእምራን ቀሲስ ዮሴፍ ምክትል አስተዳዳሪ መልአከ ሰላም ቀሲስ  አንገሶም ካህናትና ዲያቆናት የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እንዲሁም ከሄልሲንኪና ከተለያዩ  የፊንላንድ ከተሞች የመጡ ምእመናን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት  ተከብሯል::

በዋዜማዉ ዐርብ ከምሽቱ 5:30 ስብሐተ እግዚአብሔር በማድረስ እና እንዲሁም የአቡነ ተክለሃይማኖትን  ገድል በመተርጎም የተጀመረ ሲሆን ቀጥሎም በሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ማኅሌት ተቁሞ አድሯል። ጸሎተ ኪዳን እና ጸሎተ  ቅዳሴውም በሁለቱም አጥቢያ ቤተክርስቲያን ካህናት እየተመራ ተከናውኗል።

ሥርዓተ ቅዳሴው ከተጠናቀቀ በኋላ በዓሉን  አስመልክቶ ቃለ እግዚአብሔር በደብሩ አስተዳዳሪ መጋቤ ብሉይ ቀሲስ ለማ በሱፍቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ አያይዘውም በደብሩ ሰባተኛ ዓመት የምስሥረታ በዓል አከባበር ላይ አጭር ገለጻ ከሰጡ በኋላ የደብሩን አመሠራረት ታሪክ  እና ሌሎችንም መንፈሳዊ ጽሑፎችን ያካተተ ” ፍኖተ አሚን “በሚል ርዕስ  የተዘጋጀ መጽሔት  በይፋ ተመርቋል።

በመቀጠልም ታቦተ ሕጉ  ከመንበረ ክብሩ ወጥቶ በሊቃውንቱ እና በደብሩ  መዘምራን ታጅቦ ዑደት ካደረገ በኋላ የደብሩ ሕንጻ ግዢ ኮሚቴ የ2018 የ1ኛ ሲሶ ሪፖርት እና መልዕክት ቀርቧል።

በመጨረሻም ለሕንጻ ግዢ ቃል መግቢያ ሰነዱን  ያልሞሉ እንዲሞሉ የሞሉቱም በገቡት ቃል መሠረት በወቅቱ  እንዲከፍሉ መልዕክት ከተላለፈ በኋላ  ከዋዜማው ጀምሮ በአገልግሎት ለተራዱት በፊንላንድ የደብረ ሰላም መድኅኔዓለም የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት ዲያቆናት ምስጋና ቀርቦ ክብረ በዓሉ  በጸሎት ተፈጽሟል።  ታቦተ ሕጉም በዝማሬ ታጅቦ  ወደ መንበረ ክብሩ ተመልሷል።

ፍልሰተ ዐፅሙ 2018

share

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *